ፍርድ ቤቱ ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታልን በነፃ አሰናበተ

0
1090

የሸማቶች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል የቀድሞ ባለቤቶች የአክሲዮን ድርሻቸውን ለሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ድንቁ በያሳ እና ወላጅ እናታቸው ዳንሳ ጉርሙ መሸጣቸው ሕገወጥ ውሕደት ነው በሚል ከቀረበባቸው ክስ ኅዳር 28/2011 በነፃ አሰናበታቸው።
ግንቦት 26/2011 የተመሰረተው ክስ እንደሚያስረዳው ዳንሳ ጉርሙ ከፍተኛውን አክሲዮን በመያዝ ድርጅቱን የገዙ ሲሆን ይህ ውል እንደ ውህደት ይቆጠራል በሚል የባለሥጣኑ ነገረ ፈጆች አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር።

ሀያት ሆስፒታል ኅዳር 28/2011 ዓ.ም ከባለአክስዮኖቹ ጋር ባካሔደው ጠቅላላ ጉባዬ ላይ ባለአክሲዮኖቹ ኢብራሂም ናኦድ እና ልጃቸው አሕመድ ኢብራሂም ድርሻቸውን ለመሸጥ ውሳኔ አሳልፈዋል። በዚህም መሰረት ባላአክስዮኖቹ ያደረጉትን የአክስዮን ግብይት ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ነበረባቸው ሲሉ የባለሥልጣኑ ነገረ ፈጆች ክሳቸውን መመስረታቸው ይታወቃል።

ነገረ ፈጆቹ በባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ዓመታዊ ሽያጩ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የንግድ ድርጅት ውህደት ከመፈፀሙ በፊት ለባለሥልጣኑ በማሳወቅ ባለሥልጣኑ በሸማቾች መብት እንዲሁም በፍትሐዊ ገበያ ውድድር ላይ ያለውን ጫና በማጥናት ፈቃድ ባልሰጠበት ሁኔታ መዋሐድ ሕገወጥ ነው በማለት ተከራክረዋል።

የሀያት ሆስፒታል ጠበቃ ፍቅር ሞያም “ያደረግነው ግብይት ውህደት ሊባል አይችልም፣ ምክንያቱም ግብይቱ የተፈፀመው በኹለት ግለሰቦች መካከል ነው፣ በመሆኑም የተደረገው የአክስዮን ግብየት በኹለት ነጋዴዎች መካከል ስላልሆነ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ግዴታ የለብንም” ሲሉ ሞግተዋል። አክለውም ነገረ ፈጆቹ በጠየቁት መሰረት የዓመታዊ ግብይታቸውን 10 በመቶ ቅጣት መክፈል አይገባንም ሲሉ ተከራክረዋል።

የባለሥልጣኑ ነገረ ፈጆችም በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት በማንኛውም የንግድ ድርጀት ሥር የሚደረግ የእርስ በርስ ግብይት እንደ ውሕደት ይቆጠራል በማለት ይህንንም ግብይት ባለሥልጣኑ አውቆ ጥናት ካደረገበት በኋላ ነበር ፍቃድ ማግኘት የነበረባቸው ሲሉ ሞግተዋል። ስለዚህም በድጋሚ አሳውቀው ጥናት ተደርጎበት መዋሐድ አለባቸው፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ሕጉን ስለተላለፉ ቅጣት ይገባቸዋል በማለት ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም የኹለቱንም ክርክር ካዳመጠ በኋላ የአክስዮን ሽያጩ የተደረገው በግለሰቦች መካከል ነው፣ ግለሰቦቹም ነጋዴ እስካልሆኑ ድረስ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ግዴታ የለባቸውም በማለት ግለሰቦቹ ያደረጉትም ውሕደት ሊባል አይችልም በሚል መዝገቡን ዘግቷል።

ባለሥልጣኑም በበኩሉ ፍርድ ቤቱ ለሕጉ የሰጠው ትርጉም ተገቢ አይደለም፣ በንግድ ድርጀት ሥር የተካሔደ ሽያጭ እንደ ውሕደት ይቆጠራል በማለት ችሎቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንጠይቃለንም ብለዋል።

ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታል ከ2006 ጀምሮ በትምህርት እና በሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በ32 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ በአሁኑ ወቅት በ132 ሚሊዮን ካፒታል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here