“ዘመን ብቻውን አይለወጥ!”

0
345

በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ያለፈውን ዓመት መለስ ብሎ መቃኘት፣ ጠንካሮቹን ይዞ የደከሙበትን ለማሸነፍ አዲስ ዕቅድ ማስቀመጥ የተለመደ ነው። ይህም ለተግባራዊ እርምጃ የሚያቀርብ በመሆኑ ሊጠናከር የሚገባው ባሕል ነው። በዚህ መሠረት በአገር ዐቀፍ ደረጃ 2011 እንዴት አለፈ፤ ምን ጠንካራ ጎኖች ነበሩ፤ የትኞቹስ ደካማ ናቸው? ለ2012 አዲሱ ዓመትስ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን በተመለከተ የአዲስ ማለዳን አቋም ለመጠቆም እንወዳለን።

ከጠንካራ አገራዊ ጉዳዮች ስንነሳ “ነገርን ከሥሩ. . .” እንዲሉ ችግሮችን ከመሠረታቸው ለመፍታት የፖሊሲና የአሠራር ስርዓቶች ወሳኝ መሆናቸው ይታወቃል። ከዚህም አንጻር 2011 መንግሥት በዚህ ረገድ መልካም የሚባሉ እርምጃዎችን ወስዷል። በዚህም መንግሥት አፋኝ የሆኑ ሕጎች በሚመለከታቸው አካላት ንቁ ተሳትፎ ተሻሽለው እንዲጸድቁ አድርጓል። ከነዚህም መካከል ተጠቃሾቹ የሲቪል ማኅበረሰብ እና በቅርቡ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጆች ተጠቃሽ ሲሆኑ አሁንም በመሻሻል ሒደት ላይ ያሉ ሕጎች መኖራቸው ይታወቃል።

በዓመቱ የተደረጉ የዘመቻ ሥራዎችም ከዘማቻነት አልፈው በተደራጀና ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ሳይዘነጋ እንደ መልካም እርማጃ የሚወሰዱ ናቸው። እዚህ የደሃና ደካማ ዜጎችን ደሳሳ ጎጆዎችን ማደስ፣ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በነፃ የዩኒፎርም፣ የደብተርና ስክሪብቶዎች አቅርቦት እንዲሁም የትምህርት ክፍሎች እድሳቶች፣ የጽዳት እና የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች እንዲሁም መሰል የተደረጉ በጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ሌሎች የበጎ አድራጎት እና በጎ ፈቃደኝነት በተሳካ ሁኔታ መካሔዳቸው አይዘነጉም። አዲስ ማለዳ አጠንክራ መናገር የምትፈልገው የእነዚህን ተግባራት ቀጣይነት ማረጋገጥ ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ነው።

ሌላው የውጪ ግንኙነትን በተመለከተ ዓመቱ ከሞላ ጎደል ስኬትማ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይ በቅርቡ በሱዳን በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘውን ወታደራዊ አካል እና ሲቪል ፖለቲከኞችን በማደራደር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ኢትዮጵያ ተተኪ አልባ ሚና መጫወቷ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብሎም በአህጉር ደረጃ ያላትን ተቀባይነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ስትል አዲስ ማለዳ እማኝ ትጠቅሳለች።

የመገናኛ ብዙኀን ምኅዳር መስፋቱና በቴሌቭዥን ስርጭቶች እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደረጃም እንደ “አዲስ ወግ” ዓይነት የውይይትና ምክክር መድረኮች መካሔዳቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። መድረኮቹ ሕዝብ ሁኔታዎችን በተሻለ እንዲረዳ የሚያግዙ ናቸው። ይሁንና በቂ ናቸው ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ምሁራንና ፖለቲከኞች በብዛት የሚሳተፉባቸው በመሆናቸው ከእነርሱ አልፎ ወደታችኛው ማኅበረሰብ መውረድ ይገባል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ያልተጠቀሱ ጠንካራ ጎኖች በ2012 መንግሥት አጠናከሮ ሊቀጥልባቸው የሚገቡ ሲሆኑ በተቃራኒው ደግሞ በ2011 ለመንግሥት ትልቅ ተግዳሮት ከነበሩት መካከል ጎልቶ የወጣው የክልል መንግሥታት የፌደራል መንግሥት ተገዳዳሪ መሆን አንዱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፤ ደረጃው ይለያይ እንጂ ትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

ሌላው መነሳት የሚገባው ጉዳይ የፌደራል መንግሥት ዜጎችን ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በእኩል ዓይን ባለማየት፤ ለአንዱ ጆሮ ሰጥቶ ሌላውን በመንፈግ፤ መንግሥት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሚያደርሱበት ጫና አማካኝነት የሚያወጣቸውን መግለጫዎችና ፖሊሲዎች ወዲያውኑ የማስተባበል እንዲሁም የመቀልበስ ውልውል ውስጥ መግባቱ በግልጽ የታየበት ዓመት ሆኖ አልፏል። ለዚህም እንደአብነት በኮዮ ፈጬ የጋራ ቤቶች ዕጣ እንዳይተላለፍ ተደርጓል፤ በቅርቡም ትምህርት ሚኒስቴር አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በአንዳንድ ክልሎች ምን ዓይነት ምላሽ እንደተሰጠው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በመሆኑም ይህንን ተከትሎ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው መተማመን የተሸረሸረ እንዲሆን አድርጓል። በተለያዩ አጋጣሚዎችም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እንዲቀንስ፣ ጥርጣሬና ስጋት እንዲጨምር ሆኗል። ቀላል ሊባል የማይችል የኅብረተሰብ ክፍልም በዓመቱ መጀመሪያ የነበረው ንቃትና መነሳሳት የተቀዛቀዘበት፤ የሰነቀው ተስፋ ላይም ስጋት የነገሠበት እንዲሆን አድርጓል።

ይህ ሁኔታ በቀላል መታየት እንደሌለበት አዲስ ማለዳ አጽንዖት መስጠት ትፈልጋለች። ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው መተማመን መቀነስ የደኅንነት ስጋት እንዲያድርባቸው አድርጓል። ይህም በዚህ ከቀጠል ወደ ከባድ ችግር መውሰዱ አይቀርም።

በ2011 መንግሥት ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም በምጣኔ ሀብት በኩል ያን ያክል ትኩረት ሰጥቷል ለማለት አያስደፍርም፤ የኑሮው ውድነት አሻቅቧል፥ ሥራ አጥነት ተንሰራፋቷል።

ልንሰናበተው የቀናት ዕድሜ የቀረው 2011 የከፋው እንዲሁም ለዜጎች ሥጋት የፈጠረው መንግሥት የቀድሞ ስርዓት መምጣቱን አመላካች እንደይሆን በሚል ብዙዎችን ለሥጋት ዳርጓል።

የጅምላ እስሮች፣ ይልቁንም በአማራ ክልል ተፈጸመ የተባለውን የሰኔ 15ቱን “መፈንቅለ መንግሥት” ተከትሎ የታየው የጅምላ እስራት ተጠናክሮ ቀጥሏል። የሚያስገርመውና መንግሥትን ትዝብት ላይ የጣለው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አቧራው ተራግፎ ዳግም በሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ “መንግሥት ወደ አምባገነንነት እያመራ ይሆን?” በማለት ዜጎችን ሥጋት ላይ ጥሏል።

በአዲሱ 2012 መንግሥት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የቤትና ሕዝብና ቆጠራን እና አገራዊ ምርጫን በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ከምን ጊዜውም በተለየ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የተቋማት ጥንካሬ መገንባት ይጠበቅበታል ስትል አዲስ ማለዳ መንግሥትን አጥብቃ ታሳስባለች።

በመጨረሻም 44 ሳምንታትን ተሻግራ በየሳምንቱ ቅዳሜ ያለማቋረጥ አንባብያን እጅ ስትደርስ የቆየችው አዲስ ማለዳም፤ ያሏትን ጠንካራ ጎኖች የበለጠ አጠናክራ እንዲሁም ከስህተቶቿ ትምህርት ወስዳ በአዲሱ ዓመት 2012 ጉዞዋን ትቀጥላለች። በዚህ አዲስ ዓመት ለተደራሲዎቿ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት መረጃዎችን ታደርሳለች፤ በሳል ትንታኔዎችን ታቀርባለች፤ የምርመራ ዘገባዎችንም አጠናክራ እንደምትቀጥል በዚህ አጋጣሚ ታሳውቃለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here