ትውስታ ዘ ማለዳ 2011

0
814

ኢትዮጵያ በ2011 በርካታ ኩነቶችን አስተናግዳለች። ከዓመቱ ውስጥ በተለይ ደግሞ የመስከረምን ያክል ብዙ ክስተቶች የተፈጸሙበት ወር አልነበረም። 2011 አንዳንዶችን በተስፋ የሞላ፤ ሌሎችን በሥጋት የዋጠ። አንዳንዶችን በተስፋና በሥጋት ዥዋዥዌ ያንከራተተ ሆኖ ሊያልፍ የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ የዓመቱን ዐበይት ኩነቶች መለስ ብሎ አስታውሷል።

መስከረም 2
በቡራዩና አካባቢው ባሉ ከተሞች በደረሰ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
መስከረም 4
ከአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በመጡ ወጣቶችና ፒያሳ አካባቢ ባሉ ወጣቶች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት አካባቢው ተረብሾ ውሏል።
መስከረም 5
በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት መግባትን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ ሥፍራዎች በኦነግ ደጋፊ ወጣቶችና በከተማው ወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጠረ።
መስከረም 7
በአዲስ አበባ ብሔር ተኮር ጥቃቶችን በመቃወም ሠልፍ ከወጡ ሰዎች መካከል አምስት ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካቶች ቆሰሉ። በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ የኹለት ሰዎች ሕይወት አለፈ።
መስከረም 21
ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባካሔደው 13ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ 11 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትንና 55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
መስከረም 25
በሐዋሳ በተካሔደው 11ኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ሊቃነ መናብርቱን መረጠ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሊቀ መንበርነት እንዲሁም ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀ መንበርነት በድጋሜ ተመረጡ።

__________________________________

ጥቅምት 3
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ ኢቢሲኒያ ባንክና ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበርን በ9.3 ሚሊዮን ብር ዕዳ ከሰሰ።
ጥቅምት 30
ከ40 በላይ የሚሆኑ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ አመራሮችና የደኅንነት አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ኅዳር 6/2011
የካፋ ዞን ምክር ቤት ባደረገው ጉባዔ የካፋ ዞን የክልልነት ጥያቄን በሙሉ ድምፅ አጸደቀ።
ኅዳር 27
በ50 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የለገሃር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ታኅሣሥ 6
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
መስከረም 30
የተለያዩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተወካዮች የጥቅማጥቅምና የደመወዝ ማስተካከያ ይደረግልን በማለት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አካባቢ ጥያቄያቸውን አቀረቡ።

__________________________________

ጥር 15
የቀድሞ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት በረከት ስምዖንና የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ጥር 28
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላፀደቃቸው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንና ለዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባልነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታጭተው የቀረቡለትን ግለሰቦች በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።
የካቲት 3
በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከማስተር ፕላን ውጪ ተገንብተዋል የተባሉ ከ12 ሺሕ በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑና ቤቶቹም መፍረስ በመጀመራቸው ውዝግብ ተነሳ።
የካቲት 27
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ13ኛው ዙር የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የዕጣ ሥነ ስርዓቱን ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች በመደረጋቸው ዕጣው ታገደ።

__________________________________

መጋቢት 1
መዳረሻውን ወደ ናይሮቢ ያደረገው ቦይንግ 737-800 ማክስ አውሮፕላን ተከስክሶ የ149 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
መጋቢት 6
በጌዴኦ ዞን ከ100 ሺሕ በላይ አዲስ ተፈናቃዮች ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ቀረበ። በአስከፊ ደረጃ ለረሃብ የተዳረጉ ተጎጂዎች ምሥል በርካቶችን አስቆጥቷል።
መጋቢት 22
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ሲንቀሳቀስ የቆየው የኦነግ ጦር፣ አዲስ አበባ ካሉ የኦነግ አመራሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማቆሙንና ከፓርቲው መነጠሉን አስታወቀ።
መጋቢት 1
የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለ አደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ምክር ቤት ተቋቋመ።
ሚያዝያ 6
ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ የገባው የኦነግ ጦር ያጋጠመው የምግብ መመረዝ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ኦነግ ጠየቀ።

__________________________________

ሚያዝያ 19
የቀደሞው ፕሬዚደንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በጀርመን በሕክምና ላይ እያሉ ድንገት አረፉ።
ግንቦት 2
በሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዋቂ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ተመሠረተ፤ አመራሮቹን መረጠ።
ግንቦት 9
በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሔደው ሠልፍ የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ተስተጋባ።
ሰኔ 15
አመሻሽ ላይ በሰዓታት ልዩነት በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አምባቸው መኮንን ን(ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም የኢታማዦር የነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን ተገደሉ። መንግሥት መፈንቅለ መንግሥት በአማራ ብሔራዊ ክልል ላይ ተካሒዷል ብሎ አወጀ።
ሰኔ 21
አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሩን ጨምሮ ከ350 በላይ አባላቱና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውን አስታወቀ፤ የፀጥታና ፍትሕ ግብረ ኀይል በበኩሉ ከ255 በላይ ተጠርጣሪዎች ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መያዛቸውን አስታወቀ።

__________________________________

ሰኔ 21
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በታይላንድ ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩት ጄኔራል አብርሃ ወልደ ማርያም (ኳርታር) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ሰኔ 22
ሦስት ዓቃቤያነ ሕግና የአዲስ አበባ ከተማ ባላደራ ምክር ቤት አባላትና ጋዜጠኞች ከሰኔ 15 የከፍተኛ መንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ፣ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ።
ሐምሌ 2 እና 4
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ሕወሓት በአንድ ቀን ልዩነት ባወጡት መግለጫ፣ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገቡ።
ሐምሌ 11
በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ክልልነትን አስመልክቶ በተነሳ ተቃውሞ ከ60 ሰው በላይ ሞተ።

__________________________________

ሐምሌ 15
የአማራ ክልል ተመስገን ጥሩነህን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ።
ሐምሌ 16
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አሕመድ ቡህ በምክትል ከንቲባነት ሾመ።
ሐምሌ 24
በኦሮሚያ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ተጠየቀ።
ሐምሌ 27
ለወላይታ ሕዝብ ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ወሕዴግ ጠየቀ።
ነሐሴ 6
በኢትዮጵያ የካሜሩን አምባሳደር በመኖሪያ ቤታቸው ሞተው ተገኙ።
ነሐሴ 15
ነባሩ የ(ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ)ኢዴፓ አመራሮች ተጥሎባቸው የነበረው ‹‹ዕገዳ›› ተነሳ።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here