ልማት ባንክ ለባለሀብቶች ያበደረው አምስት ቢሊየን ብር እንደማይመለስ ተረጋገጠ

0
439

የመንግሥት ፖሊሲ አስፈፃሚ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለተለያዩ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ከሰጣቸው ብድሮች ውስጥ አምስት ቢሊየን ብር መመለስ የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አዲስ ማለዳ ማግኘት የቻለችው ዓመታዊ ሪፖርት አመላከተ። ይህ በአገሪቷ ትላልቅ የግል ባንኮች በዓመት ከሚያስመዘግቡት ትርፍ ጋር ሦስት እጥፍ ጋር ይስተካከላል።

ከ16 ቢሊየን ብር ብድር በላይ በመበላሸቱ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ባንኩ 11 ቢሊየን ብድር መመለሱ አጠራጣሪ ደረጃ የደረሰ ሲሆን ቀሪው ግን ለመመለስ የማይቻል መሆኑን የባንኩ ሪፖርት ያመላክታል። የባንኩ የተበላሹ ብድሮች መጠን 33 ነጥብ 9 በመቶ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ የደረሰ ሲሆን ከዲስትሪክቶች መካከል ጋምቤላ ቀዳሚ መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሰረት በክልሉ ከተሰጡ ብድሮች 80 በመቶ የሚሆኑት ያልተመለሱ ሲሆን በቁጥር ወደ 2 ቢሊየን ብር ይጠጋል።

በተጨማሪም፤ በባንኩ ነቀምት ዲስትሪክት 866 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ያልተመለሰ ሲሆን የቅርንጫፉን የተበላሸ ብድር መጠን ወደ 83 ነጥብ 8 በመቶ አድርሶታል። በተመሳሳይ ከ739 ሚሊዮን ብር በላይ በባሕር ዳር ቅርንጫፍ የተሰጠ ብድር መበላሸቱን ማወቅ ተችሏል።

ለባንኩ የተበላሹ ብድሮች መጨመር እንደ ዋነኛ ምክንያት የተገለፁት ብድር ወስደው አደጋ ላይ ለወደቁ ፕሮጀክቶች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የአንዳንድ ተበዳሪዎች ብድራቸውን ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ ደካማ የሥራ አመራር በባንኩ ውስጥ መኖሩ፣ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ወቅት ወደ ትግበራ አለመግባታቸው እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው።

በተጨማሪ ከ68 በመቶ በላይ የተበላሹ ብድሮች አምራቹ ዘርፍ ውስጥ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተስጥቶ የነበረ ሲሆን በቁጥር 11 ቢሊየን ብር ወስደው አለመመለሳቸው ታውቋል። በተጨማሪም በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሰፋፊ እርሻ አልሚዎች ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብድር ያልተመለሰ ሲሆን 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚሆነው መመለስ የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን ማውቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል፤ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘው ልማት ባንክ 768 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ኪሳራ በ2011 በጀት ዓመት ያስመዘገበ ሲሆን ይህ ባንኩ ለማግኘት ካቀደው 878 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ትርፍ በእጅጉ ያነሰ ነው። በዓለም ዐቀፍ ፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት መሰረት የተሰናዳው የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የባንክ የባለፈው ዓመት ጠቅላላ ገቢ በ25 በመቶ አድጉ 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ቢደርስም ወጪው በ53 በመቶ አድጎ 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ሆኖ ተመዝግቧል።
ለባንኩ ኪሳራ ዋነኛ ምክንያት ብድሮች በአግባቡ አለመመለስ ሲሆን በተለይም በአግባቡ ቅድመ አዋጭነት ጥናት ሳይደረግ ብድር የወሰዱ ባለሃብቶች መመለስ አለመቻላቸው እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም የባንኩ ሠራተኛ ቁጥር ከባለፈው በጀት ዓመት ሲነፃፀር በ91 ቀንሶ 2330 ደርሷል። በሌላ በኩል የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 80 ነጥብ 5 ቢሊየን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ዕዳው 78 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ደርሷል። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ሆኖ ተመዝግቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here