ማክሰኞ ሚያዚያ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ ተከስቶ የነበረውን ግጭት አስመልክቶ የተዘጉ ሱቆች እንዲከፈቱና ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን የፋሲል ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
በዛሬው ዕለት በፋሲል ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከሦስቱም ቀበሌዎች ተደማጭነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥሪ በማድረግና ኮሚቴ በማቋቋም በደረሰው ግጭት የማረጋጋት እና የተዘጉ ሱቆችን ወደ ሥራ ማስመለስ ሥራን ለመስራት የሚያስችል ውይይት ተደርጓል።
በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሚመራው ኮሚቴው በዋነኝነት 4 ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራ የፋሲል ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳኛቸው ቢምር ገልፀዋል።
ዳኛቸው እንዳሉት በዛሬው ዕለት የተቋቋመው ኮሚቴ የተጎዱ ሰዎችን የሚያፅናና፣ የወደሙ ንብረቶችን ለይቶ ድጋፍ የሚያሰባስብ፣ የጠፋ ንብረት ካለ የሚያስመልስ እና የተዘጉ ሱቆችን የማስከፈትና ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ የኮሚቴው ዋነኛ ተግባር ነው ብለዋል።
በቀጣይም የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የነበረው ተከባብሮና ተደጋግፎ የመኖር እሴት ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ መገለፁን ከክፍለ ከተማው መንግስት ኮምዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ኹሉም የእምነት ተቋማት ፣ የከተማው ነዋሪዎች ከመንግስት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ እና በህዝቦች መካከል ግጭትን በመፍጠር እየሰሩ የሚገኙ አካላትን በመለየት በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉም ተገልጿል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






