“የቅባት እህሎችን በስፋት ማምረት ለዘይት ዋጋ አስተዋጽዖ አለው”፡-የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

0
1771

ማክሰኞ ሚያዚያ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “የቅባት እህሎችን በስፋት ማምረት የዘይት ምርት ዋጋን ለማረጋጋት አስተዋጽዖ አለው” ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

ቋሚ ኮሚቴው በኮከብ ቃና የዘይት ፋብሪካ ሰሞኑን የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት፤ የቅባት እህሎችን በአገር ውስጥ በስፋት ማምረት ለዘይት ምርት የዋጋ መረጋጋት የተሻለ አስተዋፅዖ እንዳለው አመላክቷል፡፡

ፋብሪካው የዘይት ምርት ለሕብረተሰቡ በስፋት የማቅረብ አቅም ያለው ቢሆንም፤ ባጋጠመው የግብዓት ዕጥረት ምክንያት በዓቅሙ ልክ ማምረት እንዳልቻለ ቋሚ ኮሚቴው ከተደረገለት ገለጻ መረዳቱም ተገልጿል፡፡

ፋብሪካው የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ፤ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራቱን፣ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡

ይሁን እንጂ የዘርፉን ምርታማነት አሁን ካለበት በተሻለ ለማሳደግ ግብዓት ሊያቀርቡ ከሚችሉ ድርጅቶች እና አርሶ-አደሮች ጋር በበለጠ ቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፤ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ድርጅቱ በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓቱም ሆነ በምርት ጥራት ደረጃው ላይ ቁጥጥር በማድረግ፤ የጀመረውን የገበያ ማረጋጋት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው በግብረ-መልሱ አሳስቧል፡፡

የኮከብ ቃና የዘይት ፋብሪካ የአስተዳደር ዳይሬክተር ሚካኤል ካሳ እንዳስረዱት፤ በቀን 165 ቶን ዘይት የሚያጣራው ይህ ፋብሪካ በዓመት አንዴ የሚያገኘው የቅባት እህል፣ ከሦስት ወር በላይ የሚያሠራው ባለመሆኑ፤ መሥራት ካለበት ከሃያ በመቶ በታች እየሠራ ይገኛል።

ድፍድፍ ዘይት ከውጭ በማስገባት እና በስፋት በማምረት፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመንግስት ሠራተኞች፣ ለሸማች ማኅበራት እንዲሁም ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ምርቱን በማድረስ፤ የተከሰተውን የዘይት ዕጥረት ችግር ለመቅረፍ የተሻለ መሠራቱን ዳይሬክተሩ አያይዘው አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የቅባት እህሎች በሚመረቱባቸው ቦታዎች ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት፣ መንግስት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እና የባንኮች ድጋፍም እንደሚያስፈልጋቸው መተቆማቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here