መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየመካሪዎች ምስጋና

የመካሪዎች ምስጋና

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ የኢድ አልፈጥር በዓል በተከበረበት ወቅት ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጥሮ ብዙዎች እንዳዘኑ ተመልክተናል። የበዓሉ ታዳሚ በደስታው ቀን ወደ ረብሻ እንዲያመራ ያደረገው ምክንያት በተለያዩ ወገኖች እየተጠቀሰ ቢሆንም፣ የሚመለከተው አካል አጣርቶ በቶሎ እንዲያሳውቅ ኹሉም በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል።

አንድ ፌደራል ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ባርቆበት ነው ብጥብጡ የተፈጠረው እየተባለ መነሻው በስፋት ሲነገር ነበር። በዚህ መሠረት የፍርድ ሂደቱ ተጀምሮ ተጠርጣሪው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበታል።

በርካታ ሕፃናት ባሉበት ሀይማኖታዊ በዓል ላይ እንደዚያ ዓይነት ወላጅን ከልጅ የሚለያይ ክስተት እንዲፈጠር የሚፈልግ ይኖራል ተብሎ መገመት ቢከብድም፣ ይህን ሳያመዛዝኑ የሆነው እንዲፈጠር ያደረጉም ካሉ ምርመራው ውስጥ ተካተው ሂደቱ በሚገባ መጣራት አለበት የሚለው የብዙዎች አስተያየት ነው።

መንግሥት ስለንብረት ውድመት ይበልጥ ቆርቁሮት ወዲያው በመግለጫው ስለረብሻ ሲያትት ማኅበረሰቡን ያሳሰበው ደግሞ ከወላጆቻቸው ተለያይተው የነበሩት ህፃናት ጉዳይ ነበር። ጥቂቶች በእንዲህ ዓይነት ግርግር ውስጥ ድንገት የሚፈጠር ነገር የሚያስከትለው ትርምስ፣ ጫማን ብቻ ሳይሆን ልጅንና ራስንም ሊያስረሳ እንደሚችል ልብ ካለማለታቸው የተነሳ ከልጆቻቸው ተለይተው የነበሩትን ወላጆች ጥለው ፈረጠጡ የሚል አስተያየት መስጠታቸው ብዙዎችን አስከፍቷል።

በሌላ በኩል የተለያዩ ቤተሰቦችን ለማገናኘት ብዙዎች ሲደክሙ ታይቷል። ዘርና እምነትን ሳይለዩ ሕፃናቶቹን እንደራሳቸው ልጆች ቆጥረው በየፖሊስ ጣቢያውና በየመስጊዱ ያደረሱ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃቸውን እያሰራጩ ቤተሰብ እንዲወስዳቸው ያደረጉ በርካቶች ስለመሆናቸው በቀጣይ ቀናት ውስጥ ሲነገር ነበር።

ከእነዚህ ምስጉን ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዲት በሥራ ላይ ተሰማርታ የነበረች ትራፊክ ፖሊስ አንዲት ከቤተሰቦቿ የተለያየች ሕፃንን ታቅፋ ለማገኛነት ስትዘዋወር የተነሳው ፎቶ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ስማቸውም ሆነ ምስላቸው ሳይገኝ በርካቶች በጎ ተግባር ላይ ተሳትፈው እንደነበርም በቦታው የነበሩ ይመሰክራሉ።

ረብሻውን በተመለከተ በመንግሥት ላይ ተቆጥተው የነበሩ ግለሰቦች ድንጋይ በመወርወር የሕዝብ ንብረቶችን ሲያወድሙ ታይተዋል። የወደመው ንብረት መጠን እንደተመልካቹና እንደገማቹ ቢለያይም ያንን የፈፀሙትን ወጣቶች ለማስቆምና የበለጠ ጉዳት እንዳይከሰት ያደረጉም ግለሰቦች መኖራቸውን የተመለከትንበት አጋጣሚ ነበር። በእንዲህ ዓይነት የጥፋት ወቅት መሳተፍ ልቦናቸው ባይፈቅድላቸውም፣ እንደጠላት ላለመታየት ሲሉ ፈርተው በቡድን የሚካሄድ ጥፋትን ዝም የሚሉ በርካቶች መሆናቸው ይታመናል።

ክስተቱን ግን የተለየ የሚያደርገው የወጣቱን ተግባር ለማስቆም ማንንም ሳይፈሩ እየተሯሯጡ የተቻላቸውን ሲሞክሩ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች መታየታቸው ነው። ማንነታቸውን ለማወቅና ለመሸለም ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየሞከሩ ሲሆን፣ ለቀናት ማን እንደሆኑ ሳታወቅ ቆይቷል። ክፉ ሠሪዎችን ከመኮነን ይልቅ ደግ የሠሩን መሸለሙ ለውጥ ያመጣል ብለው ያመኑም በዚሁ መንገድ በመጓዝ ነገሮችን ለማስተካከል መሞከራቸውም ተስተውሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች