የአዲስ ዓመት አከባበር ድሮ እና ዘንድሮ

0
1079

እንደ አበው ተረክ አዲስ ዘመን ሲመጣ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ዓውደ ዓመት ነው። ከባዱ የኹለት ወራት ጨለማ፣ የክረምቱ ዶፍ ዝናብ፣ አስገምጋሚው መብረቅ፣ ጎርፍና የወንዞች ሙላት ግሳት መስከረም ላይ ይረጋጋሉ። የደመናው መጥቆርና የሰማዩ ልዘንብ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ ማጉረምረም ያበቃል። መስኮች ደንና ሸንተረሩ በአበቦች ፍካትና ሙላት ይታጀባል። የአእዋፋት ድምጽና ዝማሬ በየቦታው ውበት ይሆናሉ። ክረምቱ ማብቃቱን የምታበስረው የመስቀል ወፍ ከተደበቀችበት ብቅ ስትል አደይ አበባም ፍካቷን እነሆ ትላለች።

በበዓሉ ቤተሰብ ጎረቤት በያለበት በጋራ ያለውን ደግሶ አብሮ በልቶና ጠጥቶ ለዕለቱ ያደረሰውን አምላክ አመስግኖ “የከርሞ ሰው ይበለን” ብሎ የሚመራረቅበት ደግ ደጉን የሚመኝበት ወር ነው። ሴቶች ልጃገረዶች እንቁጣጣሽ ብለው በየቤቱ እየዞሩ “እንኳን አደረሳችሁ” የሚሉበት በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚከበር የዓመቱ መግቢያ አሀዱ ነው። መስከረም በተስፋ፣ በብርሃን፣ በልምላሜ በአዲስ ትልምና እሳቤ ሕይወት የሚጀመርበት የወራቶች በኩርና አውራም ነው።

በኖረውና በቆየው የአገራችን ባሕል መሰረት ሁሉም ዜጋ በአቅሙ ያለውን ደግሶ አዘጋጅቶ በደስታ፣ በሰላምና በፍቅር ይቀበለዋል። ዶሮው፤ በጉ፤ ቅርጫ ሥጋው የዘመድ አዝማዱ መሰባሰብ የጎረቤቱ ድግስና አብሮ መብላት መጠጣት፤ እንደአቅም መጠጥ በወረቀት ተጠቅልሎ ወይም ድፎ ዳቦ ይዞ ዘመድ ለመጠየቅ መሔድ የድሮው ብርቅዬ ባሕላችን ነበር። አባወራውና እማወራዎቹ የአገር ባሕል ልብስ ለብሰው፣ ልጆች ደግሞ ስጦታውን ተሸክመው፣ እናት አባት፣ አክስት፣ ታላቅ እህት፣ ወንድም ቤት ይኬድ ነበር ድሮ፤ የዛሬን አያድርገውና ሲሉ የኋሊት በትዝታ ተመልሰው ለአዲስ ማለዳ ያወጉት የስምንት ልጆች አባት የሆኑት የ78 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ተፈሪ ሰማኝ ናቸው።

ተፈሪ፣ በወንደላጤነት በኖሩበት 35 ዓመታት በዓላትን በጣም ይናፍቁ ነበር። የስምንት ልጆቻቸው እናት የሆኑት ባለቤታቸውን የሺሃረግ ለማን ያገኟቸው በ8 ብር ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ውስጥ፣ አከራዮቹ ለበዓል ቡና እንዲጠጡ ጋብዘዋቸው እዛ በታደሙበት ወቅት ነው። በወቅቱ የ14 ዓመት ልጅ የነበረችው የሺሃረግ አበሻ ቀሚስ ለብሳ፣ ታጥባ ታጥና፣ በእንሾሽላ እጆቿንና እግሮቿን አስውባ፣ ከፊት ለፊቷ ባለው ረከቦት ደምቃ ቡና ለማፍላት ተፍ ተፍ ስትል፣ “እምገባበት ጉድጓድ ጠፋኝ” ይላሉ። በእነሱ ዘመን ሴት ልጅ በበዓል እንዴት ተውባ እንደምትቀርብ ሲያስታውሱ።

ይሁን እንጂ ወንድን ልጅ በሙሉ ዓይን ደፍሮ መየት፣ ያውም በቤተሰብ ፊት “ዓይን ይብላሽ” ያስብል ስለነበር፣ ለረጅም ሰዓት ተሰራርቀው ይተያዩ እንደነበርና በኋላ ግን እናትየው ዓይናቸውን ስለጣሉባቸው፣ የዓይን ናፍቆታቸውን ሳይጨርሱ መውጣታቸውን የገለጹት ተፈሪ፣ የሺን ለማግኘት በዓላትን መጠበቅ ግድ ይላቸው እንደነበር ያወሳሉ። “ጠላ ይኖራል? ቅራሬስ?” በሚል ሰበብ ከኮረዳዋ የሺ ጋር እንደሚገናኙ ገልጸው፣ ከብዙ ዓመት በኋላ የየሺ እናት በተለያዩ ታቦታት ሥም ጠላ እየጠመቁና ዳቦ እየጋገሩ ይጠሩት የነበረው ልጃቸውን ሊድሩት አስበው እንደነበር ከባለቤታቸው መረዳታቸውን አጫውተውናል።

ተፈሪ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ በዓላት በውስጣቸው ብዙ የሚሰሩት ሥራ አለ። ቤተሰብ ልጁ እንዲዳርለት ሲፈልግ፣ ብዙ ዘመድ እንዲያፈራ፣ ከዘመዱ እንዳይጋባና ባሕላዊ መስተጋብሩን እንዲያሰፋ በዓላትን ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ እንቁጣጣሽ ሲመጣ በነጭ ልብስ ባሸበረቁ ልብሶች ያሽቆጠቆጡ ልጃገረዶች በዝማሬያቸው የአዲሱን ዓመት ብስራት እያበሰሩ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የብልጽግና እንዲሆን፣ ወንዱን በአዲሱ ዓመት ንገስ ሲሉት ሴቷን የጀግና ሚስት ያደርጓቸዋል።

በአካባቢው በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችና ካህናትም ነጭ የአገር ባሕላቸውን ለብሰው፣ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የእርቅና የምርት እንዲሆን ይመርቃሉ። ሰዉም ምርቃቱን ከልብ በመነጨ ስሜት አሜን “ይሁንልን ይደረግልን” ሲል ይቀበላል። ደግሞም ይሆንለታል፤ ሲሉ ስለነበረው ባሕላዊ ወግ አጫወቱን።

መስከረም ጠባ፣ ቡሄን አልፎ ጨለማው ክረምት አብቅቶ እዮሀ አበባዬ የሚባልበት መስከረም ገብቷል። “ታዲያ ምን ዋጋ አለው ማኅበራዊ ትስስራችን ላልቶ፤ የኑሮ ውድነቱ እሳት ሆኖ ከጥንት ከጠዋቱ የምንታወቅበት አብሮ የመብላት ባሕላችን ደብዝዞ፤ መሰረታዊ ነገሮች ሰማይ በደረሱበት ሁኔታ ምኑን ከምን አድርገን ልንቀበለው ነው?” ሲሉ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት የ66 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ይናገራሉ።

ወይዘሮ እማዋይሽ ለተወሰነ ሰከንድ በሐሳብ ተዋጡ “ዓመት በዓል እምዬ እንቁጣጣሽ ድሮ ቀረች፤ ዛሬማ ምን ዓመት በአል አለ? የዛሬን አያድርገውና በየክፍለ አገሩ ለሥራ ጉዳይ የተበታተኑ ልጆቼ በበዓል ዋዜማ የቻሉት በግ፣ የቻሉት ቅቤ ሌሎቹ ዶሮ ይዘውልኝ ይመጡ ነበር። ታዲያ ለኔ ብቻ አይደለም፣ ላሰደጓቸው ጎረቤቶቻቸውም ከሰል፣ ወይ ዶሮ ይዘው ይመጡና ይመረቃሉ። ያ ደጉ ዘመን እንዲህ ነበር ሲሉ ቁዘማቸውን ቀጠሉ።

እማዋይሽ፣ የማወራው ስለድሮ ታሪክ አይደለም ይላሉ። ከሰባትና ስምንት ዓመት በፊት ልጆቼ ለሥራ ጉዳይ በሔዱባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ዶሮ ሰላሳና አርባ ብር ይገዙ ነበር። ትልቁ ልጄ ለ17 ዓመት በሹፍርና ሰርቷል። በ200 ብር 10 ዶሮ ገዝቶ ይመጣ ነበር። ለጎረቤቶቹም የቻለውን ያደርጋል። ይሔ ሾላ አካባቢ ለ50 ዓመት ስንኖር የነበረ በዓልና ወግ ነው። ለእንቁጣጣሽ ጠዋት ቡና ተፈልቶ፣ ፈንድሻ ፈንድቶ፣ ዳቦ ተቆርሶ፣ ቄጤማ ተጎዝጉዞና ጠላ ተቀድቶ ጎረቤት ተጠርቶ እንኳን አደረሰህ፣ አደረሰሽ ይባባላል። የተራራቀው ይቀራረባል፣ የተጣላው ካህን መጥቶ አስታርቆ በዓዲስ ዓመት ያለፈውን ረስቶ በአዲስ መንፈስ እንዲያሳልፍ ይወያያል፣ ይክሳል።

በርይሁን ወንደላጤ ነው። በመምህርነት ሙያ ውስጥ ያለ ሲሆን፣ ለበዓልና ለበዓል ማግስት በየወዳጆቹ ቤት እየዞረ ያሳልፍ እንደነበር ያወሳል። አሁን ግን ያንን ላለማድረግ ሩቅ ወዳሉት ቤተሰቦቹ ለመሔድ መወሰኑን ነግሮኛል። ምክንያቱ ደግሞ በሚያቃቸው ሰዎች ቤት ያለውን የኑሮ ውድነት በማየቱና ከዚህ ቀደም ያለው ዓይነት ዝግጅት እንደማይኖር በመረዳቱ፤ እነሱን ከሚያስቸግር ይክፋም ይልማም ቤተሰብ ጋር ማክበሩን የተሻለ ሆኖ አግኝቶታል።

በርይሁን በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎች ድሮ ከሚያውቃቸው በተለየ በፋሲካ በዓል ቆዝመው መመልከቱን ያወሳል። በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ተሰብስቦ መብላት ቀርቶ ቤታቸው የቀዘቀዘባቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው። “ዳቦ መድፊያ ኮባ ከ20 ብር እስከሰላሳ ብር ሲሸጥ ደንግጫለሁ። ከኹለት ዓመት በፊት ጎረቤቶቼ በ50 ብር ድፎ ዳቦ ያዘጋጁልኝ ነበር። በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ባሕላዊ ትስስራችን ነትቧል” ሲል ያክላል።

ፍቃዱ ተሰማ (ሌ/ኮ) ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የፖሊስ ሰራዊት አባል ሆነው ኢሕአዴግ እስከገባበት ጊዜ ድረስ ከተራ ፖሊስነት እስከ ሌተናል ኮነሬልነት አገራቸውን አገልግለዋል። በዚህ ጊዜም ያልሔዱበት የኢትዮጵያ ክፍሎች አልነበረም። ያንን ጊዜ ሲያስታውሱ ታዲያ ሁሌም የማይረሱት፣ “የትም ሒድ የትም በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ለበዓል የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማው አንድም የፖሊስ አባል አልነበረም። በዓሉ ገና ሦስት ቀን ሲቀረው “እኔ ጋር ካልመጣህ ወየውልህ፣ በእናቴ ጡት ይዣሃለሁ፣ የሰው አገር ሰው ከሚከፋው ልጆቼ ይከፉ” እያሉ ይጠሩን ነበር። በዛን ጊዜ እንዲህ የማይሉት ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ወገኖች (በተለምዶ ቡዳ ይባሉ የነበሩት) ብቻ ነበሩ። እነሱም ሳይፈልጉ ሳይሆን ግድ ሆኖባቸው ነው። እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ይህቺ ነበረች አሉኝ እየቆዘሙ።

ፍቃዱ፣ አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል ይላሉ። ሽፍታ እንኳን ሰላማዊ ሰው በማይነካበት አገር አራስ በበዓል ማግስት ትገደላለች። እንኳን ሊነፋፈቅ ሊጠፋፋ ይፈላለጋል። እንኳን አብሮ ሊበላ ይፈራራል። የሚከበሩና የሚደመጡ የአገር ሽማግሌዎች ሰሚ አጥተው ተንቀዋል። ኢትዮጵያ ግርማ ሞገስ ያለው ተፈሪና ተከባሪ መሪ አጥታለች። ያለፈውን የፍቅር ታሪክ ባወራህበት አፍህ ኀዘን ታንጎራጉርበታለህ ሲሉ ባሕላችንን በቅርብ እርቀት ስላጣንበት አሳዛኝ ጊዜ በኀዘን ቆዝመው ይተርካሉ።

አገራችንን ከተቀረው ዓለም ልዩ ከሚያደርጓት በርካታ መገለጫዎች መካከል አንዱ የራሷ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ ያላት፤ የ13 ወራት ባለቤት መሆኗ ነው። በተለይ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በሕዝቦቿ ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

“እንኳን አደረሰህ/ሽ! ዘመኑ የሠላም፣ የፍቅር ፣ የብልጽግና የደስታ ይሁንልህ/ሽ” መባባሉ የአዲስ ዓመት ገፀ በረከቶች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። እውነትም ገፀ በረከት ብንለው ይገልፀዋል። ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከብልፅግናና ከደስታ የበለጠ የለምና።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here