- ቴሌኮሙ ለአገልግሎቱን ከገበያ በሚያስወጣበት ወቅትም እንደ ኦፕሬተር ሃላፊነቱን የሚሸከም ይሆናል
ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ሲጠቀምበት የነበረውን የሲ.ዲ.ኤም.ኤ ኔትወርክ የደንበኞቼን ፍላጎት አላሟላልኝም በማለት በሶስት አመት ውስጥ አገልግሎቱን ከገበያ ለማስወጣት እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የገመድ አልባ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የ2ጂ እና 3ጂ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማቅረብ የሚያገለግለው ሲ.ዲ.ኤም.ኤ ፍጥነት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ተከትሎ በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና የገመድ የኢንተርኔት አገልግሎት ይተካል ሲሉ የቴሌኮሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ጨረር አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በሲ.ዲ.ኤም.ኤ የኔትወርክ መሰረተ ልማት ላይ ምንም ዓይነት ማስፋፊያ የማያደርግ መሆኑን ተከትሎ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሲ.ዲ.ኤም.ኤ ተጠቃሚዎች ከአገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ ነው በሂደት አገልግቱን ለማቆም የወሰነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማሰራጫ ማማዎችን እና መሰረተ ልማቶችን ብዙ ተጠቃሚዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች በመሰብሰብ እና በማሸጋሸግ አገልገሎቱ እስኪቋረጥ ድረስ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የቴሌኮሙ ዋና የሺያጭ ኦፊሰር ኤፍሬም አረሳኸኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአለም አገራት ላይም ሲ.ዲ.ኤም.ኤን በሌሎች ቴክሎጂዎች የመተካት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ኤፍሬም ይህንን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አገልግሎቱን በሌሎች ቀልጣፋ አገልግሎቶች ለመተካት ከአገልግሎት ለማስወጣት ስትራቴጂያዊ እቅድ ተዘጋጅቶ ከያዝነው የበጀት አመት ጀምሮ ማስወጣት ተጀምሯል።
ቴሌኮሙ ለአገልግሎቱን ከገበያ በሚያስወጣበት ወቅትም እንደ ኦፕሬተር ሃላፊነቱን የሚሸከም ይሆናል ያሉት ኤፍሬም ከሁለት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑትን አገልግሎት የመስጫ መሳሪያዎችን እጣ ፈንታን ጨምሮ የአፈፃፀም ሂደቱ ላይ ተጨማሪ ስራዎች ይሰራሉ ሲሉም ዋና የሺያጭ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ድርጅቱ የኢቪዲዮ አገልገሎት መሸጥ ያቆመ ሲሆን የሲ.ዲ.ኤም.ኤ ኔትወርክ ከአገልግሎት በሚወጣበት ግዜም ይህም አገልገሎት አብሮ ይቋረጣል።
በተያዘው ዓመት የቴሌኮሙ የኢንተርኔት ገቢ ከአጠቃላይ ገቢው 29 በመቶው ከኢንተርኔት አገልግሎት የተገኘ ሆኖ ተመዝግቧል። በዓለማፍ ደረጃም ጤነኛ የሚባለው የቴሌኮም ዕድገት የድምፅ አገልግሎቱ ሲቀንስ እና የኢንተርኔት ፍላጎቱ ሲጨምር እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ መግለፃቸው ይታወሳል።
በ2011 የበጀት አመት መጀመሪያ ላይም 50 በመቶ የሚደርስ የታሪፍ ቅናሽ ያደረገው ቴሌኮሙ 36.3 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢዎች የሰበሰበ ሲሆን 98.3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከዓለም ዐቀፍ አገልግሎት ገቢ ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥም ያልተጣራ ትርፍ 24.5 ቢሊንዮ ብር ያገኘ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸርም የ5.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ለዓመታት ያልተከፈለ 4.7 ቢሊዮን ብር ጨምሮ በአጠቃላይ 16.2 ቢሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም አስታውቋል።
እስከተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በተሰበሰው መረጃ ቴሌኮሙ ያለው ቋሚ ሠራተኞች ብዛት 15 ሺሕ 646 ሲሆኑ የሴት ሠራተኞች 28 በመቶ እንዲሁም የወንድ ሠራተኞች ቁጥር 72 በመቶውን ይዞ የቴሌኮሙን መሰረተ ልማቱን የሚጠብቁ 18 ሺሕ ቋሚ የጥበቃ ሠራተኞች አሉት።
ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012



