በበዓላት የታጀበችው ጳጉሜን

0
575

ኢትዮጵያን ከዓለም የተለየች ከሚያደርጓት እሴቶች አንዱ በሆነው የቀን መቁጠርያ ውስጥ ከሳምንት ባነሱ ቀናት የተዋቀረች አንዲት ወር አለች፤ ጳጉሜን። በወርሃ ጳጉሜን መጪው አዲስ ዓመት ለመቀበል ሽርጉዱ የሚደምቅበት፣ ከመንግሥት እስከ ተርታው ሕዝብ ድረስ የአከባበሩ ሁኔታ ይለያይ እንጂ ዝግጅቱ በሚገባ አለ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ደረጃ በተለይም ደግሞ በየዓመቱ የወርሃ ጳጉሜን የሚዋዥቅ የቀናት ልዩነትን መሰረት ተደርጎ በብሔራዊ ደረጃ ቀናቶች ተከብረው አልፈዋል፣ ለቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የመልካም ምኞቶች በስፋት ተስተጋብተዋል፣ ያለፈው ዓመት ሕጸጽ በይፋ ተወግዘው ተሸኝተዋል።

ይኸው ድርጊት ታዲያ በአሮሬው 2011ም አልቀረም። አምና በስድስት ቀናት የተዋቀረችው ወርሃ ጳጉሜን ከመባቻዋ ቀን ጀምሮ እስከ መገባደጃው ቀን ድረስ በበርካታ የብሔራዊ በዓላት ተከፋፍላ ነበር፤ እያንዳንዱ ቀኖቿንም ለብሔራዊ ክብረ በዓላት ገብራለች። ሰላም፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ብልጽግና፣ አገራዊ ኩራት፣ ዲሞክራሲ እና ፍትሕ ቀናት የሚባሉ ሥያሜዎች ለቀኖቿ ተሰጥቶም ነበር።

ይህን ተከትሎ ታዲያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በርካታ ግለሰቦች ሐሳቦቻቸውን ሲያስተጋቡ እና ትችታቸውንም ሲሰዝሩ ተስተውለዋል። በተለይ ደግሞ ብሔራዊ የኩራት ቀን በሚል ጳጉሜን 3/2011 በተከበረው ብሔራዊ በዓል ዙሪያ “እንዴት 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ዕዳ ያለባት አገር ትኮራለች” ሲሉ ተሳልቀዋል፤ የመወያያም ርዕስ ሆኖም ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ በአባቶቻችን ታሪክ ስንኮራ አላስፈላጊ ሥሞችን እና ቅጥያዎችን እየተሰጠን ስንፈረጅ የነበርን ሰዎች አሁን የኩራት ቀንን ለማክበር የትኛው የሞራል ልዕልና ይኖረናል ሲሉ የሞገቱም ነበሩ።

ጳጉሜን በብሔራዊ ቀናት ከፋፍሎ ማክበር ከዚህ ቀደምም የነበረና ዘላቂነቱ እና ለውጥ አምጪነቱ ግን እምብዛም የማይስተዋል የሽክርክሪት ጉዞ እንደሆነም በብዙኀኑ ዘንድ የሚተችበት ጉዳይ ነው። የዘንድሮው የጳጉሜን ንቅናቄም ዘላቂነቱ እና ለውጥ አምጪነቱ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ቢታወቅ የብዙዎች ናፍቆት ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here