ማዕከላዊን እንደ ቱሪስት

0
1454

ከዓመታት በፊት ሦስት ወራትን ሊደፍኑ ስድስት ቀናት እስከቀራቸው ድረስ በማዕከላዊ እስር ቤት በስቅየት ያሳለፉት በፍቃዱ ኃይሉ፣ ጳጉሜን 6 የተከበረውን የፍትሕ ቀን ምክንያት በማድረግ ከጳግሜን 1 እስከ 6 ለጎብኚዎች ክፍት የተደረገውን ማዕከላዊ እስር ቤት ድሮና ዘንድሮ ያስቃኙናል።

 

ያ በሥም የሚያስፈራራውን፣ ያ ሦስት ስርዓተ መንግሥታት ዜጎቻቸውን የረገጡበትን፣ ያ ሦስት ትውልዶች ፍዳቸውን ያዩበትን ማዕከላዊን ዳግም አየሁት። መጀመሪያ በፍርሐት እየራድኩ፣ በድጋሚ በኩራት እየተጀነንኩ ጎበኘሁት። መጀመሪያ በካቴና ተሸብቤ፣ በድጋሚ በካሜራ ታጅቤ ቃኘሁት። አዎ፤ ማዕከላዊን በኹለት ስሜት – በአቅመ ቢስነት እና በድል አድራጊነት ስሜት ጎብኝቼዋለሁ።

ሚያዝያ 17/2006 ከዞን 9 የጦማሪያን እና አራማጆች ስብስብ ወዳጆቼ ጋር ‘አመፅ በማነሳሳት እና በሽብር’ ወንጀል ሰበብ ተጠርጥሬ ነበር በሥም ብቻ የማውቀውን ማዕከላዊን የረገጥኩት። እዛ ጊቢ በፖሊሶች ታጅቤ የደረስኩት ከመሸ ነበር። ምዝገባ ከፈፀምኩ በኋላ እጆቼ በካቴና እንደታሰሩ በአንድ አጃቢ፣ በጨለማው ጉራንጉር ወደ አንድ ማጎሪያ እየተወሰድኩ ነው። አእምሮዬ ከቀናት በፊት ያነበበውን የሂዩማን ራይትስ ዋች ‘They Want Confession” የተሰኘ ሰቅጣጭ የማዕከላዊ የማስቃየት ታሪክ የሚያስነብብ ሪፖርት ያውጠነጥናል። ሰውነቴ በፍርሐት ዝሏል።

አጃቢው ፖሊስ “ኦነግ ነህ ወይስ ግንቦት ሰባት?” አለኝ።
“ኹለቱንም አይደለሁም” አልኩት።
“ምን አይደለህም?!” አለና ተቆጣኝ። “እናንተማ ምን አለባችሁ? እኛን እንቅልፍ ትነሳላችሁ” ብሎ እየተነጫነጨ የወሰደኝ በመተላለፊያው ውስጥ በስተቀኝ ያለውን ኹለተኛ በር ከፈተው፤ ‘ዘጠኝ ቁጥር’ እንላታለን። የታሰርኩበትን ካቴና ፈታልኝና ወደ ውስጥ ገፋ አደረገኝ። ከመተላለፊያው ውጪ ባለች አንድ ትንሽ አንፑል ጣሪያ ሥር ባለው ፍርግርግር መስኮት የምትገባው ብርሃን በበቂ ሁኔታ ክፍሉን አታሳይም። ከኋላዬ የብረቱ በር ልብ በሚተርክክ ድምፅ “ጓ” ብሎ ተዘጋ። ቆምኩኝ። በወቅቱ ውስጡ የነበሩት እስረኞች እንድረጋጋ ነግረውኝ የምተኛበትንም ቦታ አመቻቹልኝ። ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ነበሩ። “ምርመራቸውን” ጨርሰው ወይ ክስ ወይ ፍቺ እየተጠባበቁ የነበሩ እስረኞች።

ከዚያ በኋላ ባሉ ቀናት ጠዋት፣ ከሰዓት እና ማታ ወደ “ምርመራ” ክፍል እየተጠራሁ ስሰቃይ ከረምኩ፤ ውስጥ እግሬን ተገርፌያለሁ፣ ጥፊ እና እርግጫ እንደዕለት ቁርስ ምሳዬ ነበር፣ ቁጭ ብድግ ትንፋሼ እስኪያንቀኝ ድረስ እንድሠራ ተገድጃለሁ። ይህ ሁሉ የሆነው የምናገረው እውነት ውስጥ ራሴን የሚወነጅል ነገር ባለመገኘቱ ነበር። “ማነው የሚከፍላችሁ? ምንድን ነው ዓላማችሁ? ከነማን ጋር ሠራችሁ? የደበቃችሁትን ምሥጢር አውጡ” ነበር፤ “ምርመራው”። ከምርመራ ስመለስ ረደላ ሸፋ የተባለ ሌላ እስረኛ እግሮቼን በባዝሊን እያሸ ያፅናናኝ ነበር። አበበ ካሴ የተባለ እንዲሁ በጣም በስቃይ ውስጥ ያለፈ የግንቦት ሰባት ወታደር ሊያደፋፍረኝ ይሞክራል።

“እስከ ሞት ድረስ ለዓላማህ መፅናት አለብህ?” ይለኛል።
“ዓላማዬ በሕይወት መትረፍ ነው” እለዋለሁ ቆጣ ብዬ።
አጃቢ ፖሊሶቹ ለ”ምርመራ” የተጠራን አንድ እስረኛ ለመውሰድ ሲመጡ ከውጭ የተቆለፈ ክፍላችን ውስጥ ሆነን ከፖሊሶቹ እርምጃ እኩል የካቴናቸውን ‘ቅጭል፣ ቅጨል’ የሚል ድምፅ እየሰማን ማነው ተረኛ እያልን እንሳቀቃለን። በራችን በሚያስገመግም ድምፁ “ጓ!” ብሎ ሲከፈት እና ሥማችን ሲጠራ እጃችንን ለካቴና ሰጥተን መሰስ እያልን እንሔዳለን።

ማዕከላዊን እንደ እስረኛ
ማዕከላዊ ሦስት የእስረኛ ማቆያ ቦታዎች አሉት። አንደኛው እና ብዙዎች የሚፈሩት በእስረኞች ‘ሳይቤሪያ’ እየተባለ የሚጠራ ነው። በሳይቤሪያ በሮች ተዘግተው ነው የሚውሉት። የክፍሎች መተላለፊያ ውስጥ ያሉ ትንንሽ አንፑሎች ከሚሰጡት ብርሃን በቀር ምንም የለም። የፀሐይ ብርሃን እጥረት ፊታችንን እንዳያገረጣው በቀን ዐሥር ደቂቃ ፀሐይ መሞቅ ይፈቀድልን ነበር። ከዚያ ውጪ ጠዋት እና ማታ ዐሥር፣ ዐሥር ደቂቃ ለሽንት እንወጣለን። በመሐሉ ክፍላችን ውስጥ በሚቀመጠው ባልዲ ነበር የምንጠቀመው። በሳምንት አንድ ቀን፣ ለግማሽ ቀን ልብሳችንን እንድናጥብ እና ክፍል እንድናፀዳ ዕድል ይሰጠን ነበር፤ ይህ ለኛ የሠርግና ምላሽ ያህል ነበር። ቢያንስ በዚህ ቀን ለምርመራ ያለመጠራት ሰፊ ዕድል ነበር። ጠያቂ እና ጠበቃ አይፈቀድልንም ነበር። በሚፈቀድበት ጊዜም በሳምንት ወይም በኹለት ሳምንት ለአምስት ደቂቃ ያህል፣ ያውም መርማሪ ፖሊሶቹ አጠገባችን ተቀምጠው ነበር የምንጠየቀው።

በማዕከላዊ ጣውላ ቤት የሚባልም ነበር። ወለሉ ጣውላ ስለሆነ ነው ሥያሜውን ያገኘው። በሩ ተከፍቶ ስለሚውል የተሻለ ነበር። የታመሙ ወይም አባሪዎቻቸው ላይ ለመመሥከር የተሥማሙ ወንድ እስረኞች እና ሁሉም ሴት እስረኞች ጣውላ ቤት ነበር የሚታሠሩት።

ሦስተኛው የእስረኞች ማቆያ የተሻለ ምቾት ያለው ስለሆነ “ሸራተን” እያልን እንጠራው ነበር። በ“ሸራተን” በሩ ክፍት ነው የሚውለው፣ ቤተሰብ ሊጠይቀን ሲመጣ ይፈቀድልናል፣ ለምርመራ አንጠራም። ቀን መተላለፊያ የሚያክለው ጊቢ ውስጥ ስንንቀሳቀስ መዋል እንችል ነበር። ጊቢ ውስጥ ቴሌቪዥንም ነበር። “ሸራተን” ወይ ተከስሰን፣ ክሳችንን ለመከታተል ቂሊንጦ እስከምንላክ፣ አልያም ተፈትተን እስከምንለቀቅ የምንቆይበት ሥፍራ ነበር። በተጨማሪም፣ “ወንጀላቸው” ቀለል ያሉ ሰዎች የሚታሰሩበት ነበር። እኔም ለ75 ቀናት በ’ሳይቤሪያ’ እና ለ9 ቀናት ‘ሸራተን’፣ በድምሩ 84 ቀናትን ማዕከላዊ አሳልፌ ከወዳጆቼ ጋር ወደ ቂሊንጦ ተልኬያለሁ።

ማዕከላዊን እንደ ቱሪስት
መንግሥት “ማሰቃየት ማቆሙን” ለማሳያነት ማዕከላዊን ሙዚዬም አደርገዋለሁ ካለ ቆይቷል። ጳጉሜን 6 እናከብረዋለን ያለውን “የፍትሕ ቀንን” አስመልክቶ ከጳጉሜን 1 እስከ 6/2011 እንዲጎበኝ ሲፈቀድ ከሮይተርስ የሚዲያ አጋሮች ጋር ታሪኬን እየተናገርኩ ጎበኘሁት። እንደበፊቱ አያስፈራም፣ አያስደነግጥም። ጣውላ ቤት ግንባታ እየተደረገበት ነው። ‘ሳይቤሪያ’ የኮሪደሩ ጣሪያ ብርሃን እንዲያስገባ ተከፍቷል፣ ክፍሎቹ የፍሎረሰንት አምፑል ተገጥሞላቸዋል። የኮሪደሩ ግድግዳዎች በስዕል አሸብርቀዋል። የውስጥ ግድግዳዎቹ ቀለም ተቀብተው ክፍሌ ውስጥ በሳንቲም ፍቄ የጻፍኩት ‘Z9’ የምትል ማስታወሻ እና ሌሎችም ድራሻቸው ጠፍቷል። ‘ሸራተን’ ከሞላ ጎደል ባለበት አለ። መንግሥት ማዕከላዊን እንዳለ ለማኖር ለምን እንዳልፈቀደ ሊገባኝ አልቻለም። ምናልባት ኢሕአዴግ የተሰደበበት ጽሑፎችን ለማጥፋት ይሆናል፣ አልያም በእንዝላልነት ሊሆን ይችላል።

የሆነ ሆኖ ማዕከላዊ ተዘግቷል። በ2010 ክሴ ተቋርጦ ለዓመታት ተይዞብኝ የነበረውን ላፕቶፔን ለማስለቀቅ ስሔድ ማዕከላዊ ሊዘጋ ተወስኖ ነበር። ያኔ ያገኘኋቸው ፖሊሶች “ማዕከላዊን አዘጋችሁት” ይሉኝ ነበር። ወደ ቂሊንጦ ስዞር ጀምሮ፣ ከተፈታሁም በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ያለማቋረጥ ስለማዕከላዊ አሰቃቂነት ከወዳጆቼ ጋር ብዙ ጽፌያለሁ። በመዘጋቱ ኮርቻለሁ። ነገር ግን ማሰቃየት ከሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች እስኪወጣ ድረስ በበቂ ሁኔታ አልኮራም። ሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች የፖለቲከኛ እስረኛ የሌለባቸው የሚሆኑበት ቀን እስኪመጣ ድረስ ኮርቼ አልኮራም።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here