- ከ30 ሄክታር በላይ የለማ ሰብል ወድሟል
በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን በማረቃ እና ሎማ ወረዳዎች በሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ ነሐሴ 30 እና ጳጉሜ 3/2011 በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት የአስራ ዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዳውሮ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ ጳጉሜ 4/2011 በደረሰው አደጋ አምስት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና እርዳታ ወደ ጤና ተቋማት መላካቸውንም የዳውሮ ዞን አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለ ኃይለጊዮርጊስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቀበሌዎቹ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የደረሰው አደጋው፣ ከ30 ሄክታር በላይ የለማ ሰብል ከጥቅም ውጪ መሆንና ብዛት ያላቸው የቤት እንስሳት ህይወት እንዲያልፍም ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። ጉዳቱ የደረሳባቸውን ነዋሪዎች መልሶ ለማቋቋም የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀው ዞኑ የሟቾች የቀብር ስነስርዓት ጳጉሜ 5 ቀን በየትውልድ አካባቢያቸው መፈጸሙንም ተናግረዋል።
በተለይም ነሐሴ 30/2011 በዞኑ ኢሰራ ወረዳ ጉዛ ቀበሌ ውስጥ ምሽት አምስት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በመኖሪያ ቤታቸው ተኝተው በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት እንዳለ፣ በዚህም የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አራት መኖሪያ ቤቶች ደግሞ በናዳው መፈራረሳቸውን አመልክተዋል።
በክልሉ ነሐሴ 19/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን ዳራ ማሎ ወረዳ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። አደጋው የተከሰተው በወረዳው በተለምዶ “ጮዬ” የተባለው ዳገታማ ስፍራ መሬቱ በዝናቡ ኃይል ተቆርጦ በመንሸራተቱ መሆኑ ታውቋል።
ከዳገቱ በጭቃ ተቀላቅሎ የወረደው አፈር የሦስት አባወራዎችን ቤቶች ማስጠሙን ተከትሎ ቤት ውስጥ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከሞቱት መካከል አምስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፤ በወቅቱ ሌላ ቦታ የነበሩት የቤቱ አባወራ ብቻ ተርፈዋል። የአካል ጉዳትና የጤና መታወክ የደረሰባቸው 17 ሰዎች ደግሞ በወላይታ ሶዶ ሆስፒታልና ዋጫ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸዋል።
የጋሞ ጎፋ ዞን አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለማየሁ ማዶረ፣ በአደጋው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ክረምቱ እስኪያልፍ ድረስ ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ አካባቢ የማዛወርና መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩንም አስረድተዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012


