መድን ድርጅት በ 200 ሚሊዮን ብር የመረጃ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ ሊያከናውን ነው

0
530

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የአገልግሎት አሰጣጡን እና የመረጃ አያያዙን ለማዘመን በ200 ሚሊዮን ብር መዋእለ ነዋይ የመረጃ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ ሊያከናውን ነው።

ድርጅቱ እየተጠቀመባቸው ያለው የመረጃ ማከማቻ እና የማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶች ከ2003 ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ እና የድርጅቱን የደንበኞች እድገት እና ቅርንጫፎች ብዛት የማይመጥኑ መሆናቸውን ተከትሎ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የተባለለትን የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የድርጀቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መሰረተ ልማቱ በአዲስ አበባ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚዘረጋ ሲሆን የኔትወርክ መቆራረጥ እና ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱ መረጃ የማከማቸት አገልግሎቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርጋል። የመረጃ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታው በዋናው መስሪያ ቤት በሶስት ንዑስ ቅርንጫፎች ላይ እንደሚከናወን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የድርጅቱን የሒሳብ እና የመድን መረጃ መያዢያ እና መተግበሪያዎችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመዱ ለማድረግ የማሻሻያ ስራዎችን ማስፋፊያው ያካትታል።

ማስፋፊያው የደንበኞችን መረጃዎችን በአግባቡ ለመያዝ የሚያግዝ ሲሆን እንደ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ተቋማት ጋር ድርጅቱ በጋራ ሊሰራ የሚችልበትን አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የማሻሻያው የመጀመሪያ ደረጃ ስራ የሆነው የኮምፒውተር መተግበሪያዎችን ማሻሻል በቀጣዮቹ 6 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን አጠቃላይ የመሰረተ ልማት ግንባታው በሁለት ዓመታት ወስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ከዘጠኝ አመታት በፊት የተሰራው የአ.ይ ሲቲ መሰረተ ልማት ለአስር አመታት እንዲያገለግል ታስቦ የነበር ሲሆን ድርጅቱ ባሰመዘገበው ፈጣን እድገት የቅርንጫፎቹ ቁጥር ከ42 አሁን ላይ ከ102 በላይ የደረሰ በመሆኑና በወቅቱ 1.1 ቢሊዮን ብር የነበረው የአረቦን ገቢ በባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ 2.9 ቢሊዮን ብር በመድረሱ ለተገልጋዮች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል ማሻሻያው ማስፈለጉን ነፃነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2011 የሰበሰበው የአረቦን ክፍያ ከባለፈው በጀት አመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የላቀ ሲሆን 1.5 ቢሊየን ብር የካሳ ክፍያ ለመክፈል አቅዶ 1.1 ቢሊየን ብር ክፍያ መክፈል ችሏል።

ከ43 አመታት በፊት 13 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በማዋሃድ የተመሰረተው ኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ1.2 ሚሊዮን ዶላር በተከፈለ ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 30 በመቶ የሚሆነውን የኢንሹራንስ ገበያን ተቆጣጥሮታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here