በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ከነበሩ የተለያዩ ምርቶች 2 ሚሊዮን 814 ሺህ 094 ብር ለመንግስት ገቢ ሆኗል
ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የደቡብ ክልል ባለፉት 10 ወራት በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በተገኙ 23 ሺህ 297 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡
ቢሮው ባለፉት 10 ወራት ባደረገው የውጭ ኢንስፔክሽን በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በተገኙ 23 ሺህ 297 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡
የቢሮው የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቸርነት ፍቃዱ እንደገለጹት፤ ቢሮው ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በህገወጥ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እንዲሁም ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመው በ16 ሺህ 935 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ፣ በ1 ሺህ 819 የንግድ ድርጅቶች ላይ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በ4 ሺህ 543 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማገድ እርምጃ በመውሰድ በድምሩ 23 ሺህ 297 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዶ ወደ ህጋዊው የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በ10 ወራት በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 113 ኩንታል የስኳር ምርት፣ 21 ሺህ 682 ሊትር የፓልም ዘይት፣ 920 ሊትር ቤንዚን፣ 75 ኩንታል ስንዴ ፣192 ኩንታል ጤፍ፣ 46 ኩንታል አቮካዶ እንዲሁም 1 ሺህ 300 ሊትር ነጭ ጋዝ ከቅጣት የተገኘ ገቢ 450 ሺህ 580 ብር፤ 2 ሚሊዮን 363 ሺህ 514 ብር ከምርት ሽያጭ በድምሩ 2 ሚሊዮን 814 ሺህ 094 ብር ለመንግስት ገቢ ሆኗል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በቀጣይ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚሰሩ ማስታወቃቸውን ከደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡



