እስካሁን ድረስም 8 ሰዎች ሞታቸው ተረጋግጧል ተብሏል
ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በህወሃት ቡድን ቁጥጥር ሥር በሚገኘው አበርገሌ ወረዳ 012 ቀበሌ (ፅላሪ ጀርገብ ) የእብድ ዉሻ በሽታና ወባ መከሰቱ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሥር የሚተዳደሩ ሦስት ወረዳዎች (በርገሌ፣ ጻግጅ እና ዝቅዋላ) እስከ አሁን ድርስ በህወሃት ሀይል ቁጥጥር ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት፣ ህዝብ ለከፍተኛ ረሃብ፣ በእርዛት እና በድርቅ ከመጠቃቱም በላይ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በርገሌ ወረዳ ከፍተኛ ደረጃ ሊባል በሚችል ሁኔታ የእብድ ውሻ በሽታ፣ ወባ እና ከፍተኛ የምግብ እጥረት፣ ከፍተኛ ተቅማጥና ትውከት ምልክቶች የሚያሣይ ገዳይ ወረርሽኝ መከሰቱን መምሪያው ገልጿል።
በዚህም ምክንያት እስካሁን 8 ሰዎች ሞታቸውን የተረጋገጠ ሪፖርት ለመምሪያው መድረሱንም ጨምሮ አስታውቋል።
ይሄንንም ተከትሎ የባለሙያ እገዛና የህክምና ምላሽ ለመስጠት አካባቢዎቹ ሙሉ በሙሉ በህዋሃት ቁጥጥር ሥር የወደቁ በመሆናቸው ምክንያት ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ መታደግ አልተቻለም ተብሏል።
በመሆኑም ጤና መምሪያው የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ሆነ የጤና ሚኒስቴር ከአለማቀፍ ድንበር የለሽ ህክምና ሰጪ ተቋማት ጋር በመነጋገር ለህዝቡ አፋጣኝ የጤና አገልሎት እና የወረርሽኝ አሰሳና ቁጥጥር እንድሁም የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ሲል ጠይቋል።



