ሴቶች እና አዲስ ዓመት

0
690

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ከሌሎች አገሮች በተለየ በዓመት ውስጥ መልኩ ዐሥራ ሦስት ወራት አሉን፤ በድምቀት ከሚከበሩ በዓሎች መካከል አንዷ አዲስ ዓመት ናት። የአዲስ ዓመት መግቢያ ሲቃረብ ተፈጥሮ ምድሪቱ በአደይ አበባ ማሸብረቅ ትጀምራለች። ነዋሪውም አቅሙ በፈቀደ መጠን እንደ ባሕላችን ድፎ ደፍቶ፣ ቅርጫ ገብቶ፣ ጠላ ጠምቆ፣ ጠጅ ጥሎና ዶሮ ወጥ ሰርቶ ለማሳለፍ ከበዓሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ዝግጅት ይጀምራል። ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ልክ ነው ባይባልም በልማዳዊው ማኅበራዊ መዋቅር ውስጥ ባለው የሥራ ድርሻ ክፍፍል መሰረት የቤት ውስጥ ሥራ ለሴቷ የተሰጠ ኀላፊነት ነው። በመሆኑም ማንኛውንም የቤት ውስጥ ሥራ ዶሮ ወጥን ጨምሮ መሥራት ለሴቷ የተተወች ናት። ነገር ግን በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነችውን የዶሮ ወጥ ከመበላቷ በፊት መጀመሪያ አባወራ መቅመስ አለበት። ሴቷ የሠራችውን ወጥ የቱንም ያህል መብላት ብትፈልግም አባወራው ከመብላቱ በፊት የማይታሰብ ነው። በርግጥ ይህችን መሰሏ ልማድ በከተማ እየቀችረ የመጣች ብትሆንም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል በሚኖርባት የገጠሩ ማኅበረሰብ ክፍል ግን አሁንም በስፋት ትተገበራለች። በተጨማሪም ከዐሥራ ኹለቱ የዶሮ ብልቶች አንዱ የሆነውን ፈረሰኛንም የመብላት ልዩ ጥቅም ያለው ወንዱ ነው። ይህ ለምን ሆነ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ የስርአተ ጾታን እኩልነት ከግንዛቤ ውስጥ ያላገነዘበ ማኅበረሰብ የወለደው ልማድ ከሚለው የተሻለ መልስ የምናገኝለት አይመስለኝም። እናም ፈረሰኛ መብላት ወይም አለመብላት የሚለው ሐሳብ በራሱ ትልቅ ነገር ባይሆንም የልማዱ መሰረት የሆነው በጾታ እኩልነት ያለማመን እሳቤ ግን ትልቅ ስህተት ነው።

ከአዲስ ዓመት ጋር ተያይዞ ሌላው የተለመደው ነገር ወንዶች አበባ በመሳል በየቤቱ እንኳን አደረሳችሁ እያሉ በመስጠት ሴቶቹ ደግሞ አበባዬሆሽ በመጨፈር በዓሉን ማድመቃቸው ነው። ነገር ግን በስርአተ ጾታ መነጽር ካየነው የአበባዬሆሽ ጭፈራ ግጥም ከስህተት የጸዳ አይደለም። ለምሳሌ
“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው፣ ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን፣ እናቴን ጥሯት መዳኒቴን
እሷን ብታጡ መቀነቷን” የሚለው እና
“ከብረው ይቆዩን ከብረው በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሰላሳ ጥጆች አስረው ከብረው ይቆዩን ከብረው”

የሚለውን ማንሳት እንችላለን። የዚህ ግጥም አንዱ ግድፈት ወንዶች ምንም አንኳን መልካም ነገር ቢደረግላቸውም ግልፍተኛ ወይንም ተማቺ አድርጎ በተሳሳተ መንገድ መሳሉ ሲሆን ሌላው ደግሞ መክበርን ከወንድ ልጅ ጋር ብቻ ማያያዙ ነው። እናም ብዙ መልካም ወንዶች መኖራቸውን እንዲሁም ሴትም መውለድ መክበር እንደሆነ በማወቅ ግጥሞቹ መሻሻል አለባቸው። በመሆኑም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር ያገኘሁትን የተሻሻለ ግጥም በማቅረብና ዓመት ዓመት ያድርሰን በማለት ሐሳቤን እቋጫለው።

“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው አደይ አምጥቶ ጸጉሬ ሰካው
የምወዳትን የምትወደኝን እናቴን ጥሯት መዳኒቴን
እሷን ብታጡ መቀነቷን”
“ከብረው ይቆዩን ከብረው በአመት ሴትም ወንድም ልጆች ወልደው
ሰላሳ ጥጆች አስረው ከብረው ይቆዩን ከብረው”

ኪያ አሊ

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here