“ራዕይ በሌለበት ተስፋ የለም”

0
694

አምና ከነበርንበት በባሰ ሁኔታ እንገኛለን የሚሉት ቤተልሔም ነጋሽ፣ እንደሕዝብ መሥራት የነበረብንን የቤት ሥራ ባለመሥራታችን፣ ስንጀምረው ምናልባት ስለምንመኘው ውጤት እንጂ ስለአካሔዳችንና ስለሒደቱ፣ በሒደቱም ሊገጥመን ስለሚችለው እንቅፋትና ተግዳሮት ያንንም ለማለፍ ስለሚያስፈልገን ዝግጅት ባለመምከራችን የመጣ ነው ሲሉ ምክንያታቸውን ዘርዝረዋል። በግልም ይሁን በመንግሥት በጋራ ለአፈፃፀሙ የምንተጋለት መሪ ሐሳብ ወይም ራዕይ የለንም ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል።

 

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
ርዕሴን የወሰድኩት ከጆርጅ ዋሽንግተን ተጠቃሽ አባባል ነው።

በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ሆነን ያለፈውን አንድ ዓመት ስንቃኝ፣ ዓመቱ የሆኑትን መልካም ነገሮችና በተስፋ ተሞልተን እዚህ እንድንደርስ ያደረጉንን በርካታ ክስተቶችና ውጤቶች የማሰባችንን ያህል፤ በሥጋት እንድንሞላ፣ የመጪው ዓመት ተስፋ ጥላ ያጠላ እንዲሆን ከሚያደርጉ ኹነቶች ጋርም ተፋጠን ነው። ብዙ ዜጎቻችን ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተደፍረዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ተፈናቅለዋል። አንድ ከመሆን ይልቅ መለያየትን የምንሰብክ በዝተናል። ኑሮ ውድነት ከዕለት ዕለት የዜጎቻችንን ጫንቃ መጫኑን ቀጥሏል። ዘይትና ስኳር ቀርቶ ጤፍም በኅብረት ሱቅ ሊታደለን መጠባበቅ ይዘናል። ሽንኩርት ብርቅ ሊሆንብን፣ ዘይት ከዓይናችን ሊጠፋ ያስፈራራን ጀምሯል።

ሌላው ቀርቶ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ በተቀመጥኩበት ቅጽበት ብዙ የሚያሳስቡን ጉዳዮች በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያው በመተንተን ላይ ነበሩ። በግሌ ከሁሉ በላይ ባለፈው ዓመት በዚህን ወቅት ከነበርንበት ሁኔታ በባሰ እንጂ በተሻለ ሁኔታ አለመገኘታችን ከሁሉም ልቆ ይሰማኛል። አዲስ ዓመት ነውና ስላለፈውም ስለሚመጣውም ልንነጋገር የግድ ይላል። ብንችል በሰፊው ተወያይተን፣ በአገር ደረጃ መክረን፣ ጊዜ ወስደን፣ ራዕይ ሰንቀን ልንነሳ ይገባል።

አቻምራ መገባደጃ ላይ የምናውቀው ኻያ ሰባት ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው፣ ሊቃወሙት የደፈሩ ሺዎችን እስር ቤት አጉሮ መተንፈሻ ቀዳዳ፣ ብሶት ማሰሚያ ቀዳዳን ሁሉ ደፍኖ የነበረው ኢሕአዴግ ከውስጡ በነበሩና መንገድ በፈጠሩ ለውጥ ፈላጊዎች ጭምር ተገፍቶ ሲታደስ ገና የተስፋ ጭላንጭል ታይቶ ሕዝብ አዲሱን ዓመት በታደሠ ተስፋ ሲጠባበቅ ነበር። የለውጥ አየር መጥቶ የማይታሰብ የሚመስለው ሁሉ ተችሎ፣ ከአገር ቤት እስከ ውጪ የይቅርታ አየር ሰፍኖ፣ ጭቆና ትናንት መስሎ፣ አዲስ ሕግ የተሻለ አሠራር፣ ሹመት ወዘተ አዲሱን ዓመት የጀመርንበት ከባቢ ነበር። አስደሳች፣ ተስፋ ያዘለ ወቅት ነበር።

ማኅበራዊ ሚዲያ ከዳያስፖራ እስከ አገር ውስጥ ተቃዋሚዎችና የታደሠው አመራር፣ ወደ ሥልጣን የመጡት አዲስ ዓይነት መንገድ የተከተሉ መሪ፣ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ከፍተኛ አቀባበል እየተደረገላቸው ወደ አገር የገቡ ሞት ፍርደኛ የነበሩ ከወንጀለኛ ወደ ጀግና ማዕረግ የተሸጋገሩ ብዙዎች በታሪክና በፎቶ በክስተትና በደስታ ተሞልቶ ነበር። ድሮ በመንግሥት ሥራ ምንም ፍላጎት አሳይቶ የማያውቀው ወጣት በተለይም የፖለቲካ አክቲቪዝም ላይ የተሰማራው እንደዛም ብሎ ራሱን የሚጠራው የኅብረተሰብ ክፍል ራሱን በራሱ የሾመ አማካሪ ሆኖ በማያገባው ጥልቅ ሲል የታየበትም ነበር።

ከላይ የዘረዘርኩት ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ለውጡ ሳምንታት ሲፈፀም ደስታውና ሰላሙ፣ ፈንጠዝያውና ማሞካሸቱ ጥላ ሊጥልበት፣ ቅሬታ መሰማት ሊጀምር ግን ብዙ አልቆየም። በባንዲራ ቀለም ጠቡ፣ ብሽሽቁ፣ ይሔ የእኛ ነው፣ ያኛው የናንተ ነው ፉክክሩ ተተካ። የዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ሲያልፉ፣ ከጌዲኦ ብዙ ሺዎች መፈናቀል፣ ቡራዩ አሰቃቂ ጥቃት መድረስ፣ ከሰንዳፋ መፈናቀል፣ የሲዳማ በዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ የዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል እንዲሁም በአማራ ክልልና በፌደራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የደረሰ ግድያ፣ አገር መፍረስ ያመጣል ተብሎ እስኪያሰጋ ብዙ ጥፋት ደረሰ።

በለውጡና ሊያመጣ በሚችለው ተስፋ ላይም ጥያቄ መፈጠር ጀመረ። ብዙ ተከታይ ካላቸው ግለሰቦች እስከ ፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖችም ወደ ሥርዓት አልበኝነት የሚያመራ ተግባር ላይ ሲሠማሩ፣ የመጣውን መልካም ሁኔታ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ሲታትሩ ታዩ። የአገሪቱን ሰላም በሚፈታተን መልኩም በተለያየ አካባቢዎች ሰላም መታጣት ታየ። ዝርዝሩን ብንተወው አሁን ባለንበት ሁኔታ ከላይ እንዳልኩት ሥጋት እንጂ አዲሱን ዓመት በተስፋ የምንቀበልበት ሁኔታ አይታየኝም። ሌላው ቀርቶ እስር ቤቶች ባዶ ሆኑ ብለን ያከበርነው ደስታ ሳይጠፋ ተመልሰን እገሌ ይፈታ የምንልበት ቦታ ላይ ተገኝተናል።

በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወራት የሲዳማ የራስ ዕድል በራስ የመወሰን ምርጫ ወይም ሪፈረንደም ይካሔዳል። ባጠናቀቅነው ዓመት በሐዋሳ፣ በዲላና አካባቢው ከዚህ ጋር በተያያዘ የወደመውን ንብረትና የጠፋውን የሰው ሕይወት፣ ለሥነ ልቡናና ለአካላዊ ጉዳት የተዳረጉ ዜጎችን ቁጥር ስናይ የሚቀጥለው ኅዳር ሪፈረንደምና ውጤቱ ሊያመጣ የሚችለውን መዘዝ ብንፈራ አይፈረድብንም። በግንቦት ወር አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ እንደሚደረግ ታስቦ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ስናስብ በብዙ ቦታ ያልተረጋጋ፣ ሰላም የጠፋበት ሁኔታ ባለበት በሰላም ያልፍ ይሆን የሚለው ሥጋት ያንዣብብናል።

በግሌ ይህ ሁሉ እንደሕዝብ መሥራት የነበረብንን የቤት ሥራ ባለመሥራታችን፣ ስንጀምረው ምናልባት ስለምንመኘው ውጤት እንጂ ስለአካሔዳችንና ስለሒደቱ በሒደቱም ሊገጥመን ስለሚችለው እንቅፋትና ተግዳሮት ያንንም ለማለፍ ስለሚያስፈልገን ዝግጅት ባለመምከራችን የመጣ ይመስለኛል። ይህንን ስል ለውጡን መርቶታል የተባለውን አካል ወይም ገዢውን ፓርቲ ወይም መሪውን ለመውቀስ ሳይሆን እንደሕዝብ ተሰባስበን በአግባቡ አካሔዳችንን ባለመምራታችን እየደረሰብን ያለውን ነገር ለማመላከት ነው። በእምነትም በሉት በፖለቲካና በብሔር፣ ተሰባስበን ባለንበት የየራሳችንን እንጂ የጋራ አጀንዳችንን አላየንም፤ የጋራ ራዕይ አልነበረንም። ተደማምጠን ለአንድ ዓላማ መሥራት አልቻልንም።

ሁላችንም ለአንድ አገር የምንሠራ እስከሆንን በመሪዎቻችን በኩል የጋራ፣ የሚያግባባን አጀንዳ ተፈጥሮልን፣ ጥርት ያለ ራዕይ ኖሮን ብንሔድ፣ ቢያንስ ሰላምና አብሮ ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችል ደረጃ ላይ በደረስን፤ ግን አልሆነም።

ሌላው ቀርቶ በመንግሥት ደረጃ እንኳን ላወጡት ደንብና መመሪያ የመገዛትና ለማስፈጸም የመነሳሳት እጥረት ይታያል። የማስተማሪያ ቋንቋንና ሥርዓቱን ይቀይራል ተብሎ፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው የተቀመረው የተባለለት ፍኖተ ካርታ እንኳን ተቃውሞ ስለቀረበበት መተግበሩ አዳጋች ሆኗል። በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ላይ ክልል ትምህርት ቢሮዎችና የፖለቲካ አጀንዳ አራማጆች መስማማት ባለመቻላቸው ተማሪዎች እንዲጎዱ ሆኗል። መንግሥት እንደ መንግሥት ራሱ ያወጣወን ፖሊሲና መመሪያ ለማስፈጸም ማጣፊያው ሲያጥረውና እጁ ሲጠመዘዝም ተመልክተናል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ አደገኛ አካሔድ ነው።

ጠቢባኑ እንደሚሉት የመሪ ወይም የአመራር ኹነኛ ጥበብ ኹለት ተቃራኒ የሚመስሉ ማለትም እኔ ካልኩት ውጪ አይሆንም የማለትና የሌሎችን ሐሳብ የመቀበል ዝግጁነትን ማጣመር ነው። ይኸውም አንድ መሪ ራዕይን በሚመለከት ማየት የሚፈለገው ለውጥ ላይ ብቻ ማተኮር ሲኖርበት ወደዛ ራዕይ በሚወስደው ሒደት ላይ ግን አዕምሮውን ክፍት አድርጎ የሌሎችን ሐሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት ለማለት ነው። በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች አካሔዳችንን ላይ የኛው በሌሎች ሐሳብ መነዳትን ብቻ እንጂ ራዕዩን አለቅም የሚል ሐሳብ እንደሌለው መረዳት ይችላል።

አንድ የሚያደርገን ራዕይ የለንም ስል ራሴን ሕዝቡ አካል አድርጌ ከማየው፣ መንግሥት በየዘርፉ አቅዶ ምናልባት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አቅዶ በጀት ተመድቦለት የሚሠራውን ማለቴ አይደለም። በግልም በመንግሥትም በሌላውም ያለን የተረዳነው በጋራ ለአፈፃፀሙ የምንተጋለት መሪ ሐሳብ/ ራዕይ የለንም ለማለት እንጂ። መሪዎቻችንም ያንን ራዕይ አስቀምጠውልን ቢሆን መልካም። ራዕዩን ለማስፈፀም የምንችለውን በተወጣን። “ራዕይ ያለሥራ ህልም ብቻ ነው፤ ሥራ ያለራዕይ ጊዜ ማሳለፊያ ነው። ራዕይ ከሥራ ጋር ዓለምን መለወጥ ይችላል” እንዲል አባባሉ።

አልያ አምና ዓመቱን ስንጀምረው ከዘረዘርኩት ሥጋት እንዲያንዣብብ የሚያደርጉ ኹነቶች በላይ ሳናስብ እንደመጣው ለውጥ በተስፋ የሚሞላን፣ የተሻለ ነገር የምንሆንበት ራስ ወዳጅነታችንን ትተን ስለአገራችን የወደፊት ዕጣ፣ ለልጆቻችን የተሻለ ነገ የምንሠራበት፣ ይቅር የምንባባልበት እንዲሆን ምኞቴ ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here