ቃና ቴሌቭዥን በአንድ ጉዳይ ኹለቴ ልከሰስ አይገባም አለ

0
866

የሸማቾች ጥበቃ እና ውድድር ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ችሎት ቃና ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሶስት ተከሳሾች አሳሳች የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ አሰራጭተዋል በሚል ቅጣት መጣሉን ተከትሎ ድርጅቶቹ ለባለስጣኑ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አሉ። አሳሳች ነው የተባለውን የጥርስ ማስታወቂያ ያዘጋጀው ቢ ሚዲያ እና አሰራጩ ቃና ‹‹ከዚህ ቀደም የብሮድካስት ባለስልጣን ማስታወቂያውን እንድናቆም ባዘዘን መሰረት አቁመናል ይህንን ጉዳይ የመመልከት ስልጣንም የብሮድካስት ባለስልጣን በመሆኑ የተወሰነው ውሳኔ አግባብነት የለውም›› ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጲያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ቃና ቴሌቪዥን ‹‹ሌሎች የጥርስ ሳሙናዎች በቂ አይደሉም ለዚህም ነው ምርጫዬ ዳቦር ኸርባል የሆነው›› በሚል አረፍተ ነገር እናት እና ልጅ የሚነጋገሩበት ማስታወቂያ በማስተላለፉ በጥናት ያልተረጋገጠ እና ለሌሎቹ ተወዳዳሪዎችም ፍትሃዊ ያልሆነ ነው በማለት ግንቦት 12/2011 በባለሥልጣኑ የእርምት እርምጃ ይወሰደልኝ ሲል አመልክቶ ነበር።

ይህንን ተከትሎም ተከሳሾቹ ጳጉሜ 4/2011 በዋለው ችሎት ‹‹የማስታወቂያ አዘጋጅ እና አሰራጮች ነን እንጂ ተወዳዳሪዎች አይደለንም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የጥርስ ሳሙና የሚያመርቱ፣ የሚያቀርቡ እና የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችን ነው እናም ልንከሰስ አይገባም›› ሲሉ ተከራክረዋል።

የዳቦር ኸርባል የጥርስ ሳሙና አስመጪ ድርጅት ባለቤትም በተመሳሳይ ‹‹ድርጅታችን ማስታወቂያ እንዲሠራለት ለባለሞያ በመክፈል አደረገ እንጂ ስለ ማስታወቂያው አሠራርም ሆነ አቀራረብ የማውቀው ነገር የለም፣ ይህ አዘጋጆቹ የሚያውቁት ነገር ነው›› በማለት ይግባኛቸውን አሰምተዋል።

የሸማቾች ጥበቃ እና ውድድር ባላሥልጣን ነገረ ፈጅም በበኩላቸው በክርክሩ ላይ የተከሰሱበት ጉዳይ ግዴታ በብሮድካስት ባለሥልጣኑ መቅረብ አለበት ሊባል አይችልም ሲሉ ተከራክረዋል። ነጋዴ አይደለንም የሚለውንም ጉዳይ በተመለከተ ይሄ በፍርድ ቤት የተነሳ ክርክር አይደለም በማለት ይግባኝ ሊባልበት እንደማይችል አስረድተዋል።

‹‹ተወዳዳሪዎች እንኳ ባይሆኑ ከአዋጁ ዓላማ አንፃር ተወዳዳሪ ባልሆኑ ነጋዴዎች ላይ ቅጣት ሊጣል እንደሚችል አዋጁ ይደነግጋል፣ ስለዚህ አዘጋጁም ሆነ አቅራቢው ያነሱት ሀሳብ በቂ አይደለም›› ያሉት አቃቤ ህጉ የማስታወቂያውን አሰሪም ‹‹ማንኛውም ማስታወቅያ አሠሪ የሚሠራለትን ማስታወቅያ አላውቅም ማለት አይችልም›› በማለት ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ቃና ቴሌቭዥን እና ቢ ሚድያ ውሳኔ በተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቢሉም የጥርስ ሳሙናው አስመጪ ግን የይግባኝ መጠየቂያው ጊዜ ካለፈ በኋላ የቀረበ አቤቱታ በመሆኑ ይግባኛቸው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ብለዋል።

ቀደም ሲልም በአስተዳደር ችሎቱ ሶስቱም ተከሳሾች ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ማስታወቂያ አሰርተዋል በሚል በተመሳሳይ ሐምሌ 12/ 2011 ካልተጣራ ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ የአምስት በመቶ ቅጣት ጥሎባቸው ነበር።

የአስተዳደር ችሎትም የኹለቱንም ወገን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 12/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here