“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
‹ቪክትም ብሌሚንግ› ይሉታል፤ በኢንግሊዘኛ። ጥቃት የደረሰበትን ሰው መኮነን እንደማለት ነው። በአማርኛ አቻ የሆነ ቃል የተቀመጠለት አይመስለኝም። ግን በጣም በብዛት በአገራችን የሚስተዋል ጉዳይ እንደመሆኑ ሁሉንም የሚያግባባን ሁሉም እኩል ሊጠቀምበት የሚገባ መጠሪያ ወይም መግለጫ ሊሆን ይገባ ነበር፤ ይገባልም።
ተጠቂ ላይ ክስ እንደማቅረብ ነው። ለምሳሌ ቤቱ የተዘረፈበትን ሰው ‹ለምን አደገኛ አጥር አያስገጠምም ነበር!› ብሎ ባለፈ ነገር ከማስቆጨት የከፋ ነው፤ ‹ደኅና ውሻ አሠልጥኖ ስላላስቀመጠ ነው!› ብሎ ሰው ላይ ከመፍረድም የሚበረታ ነው። ተጠቂ ላይ ክስ ማቅረብ ማለት፣ ቤቱ የተዘረፈበትን ሰው አስቀድሞ ነገር ለምን ቤት ኖረህ ብሎ የመክሰስ ያህል የሚደርስ ድፍረት እንደሆነ ነው፤ በበኩሌ የማምነው።
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ በተለይም በአደባባይ ወጥተው የተሰሙት ላይ ይህ ዓይነት ግብረ መልስ ይገኛል። ለምን እንዲህ ለብሳ ወጣች? ለምን ሳቀችለት? ለምን ዋሸችው? ለምን አስቀናችው? ለምን እንቢ አለችው? ብዙ ብዙ ይባላል። ይህም ለአጥፊው ጥብቅና እንደመቆም ነው። ‹አንተን እንረዳሃለን! እርሷ ነች የገፋፋችህ!› እንደማለት ነው።
ከዛም በላይ የሚያሳዝነኝና በጣም ከመለመዱ የተነሳ ጤናማ የሚመስለው ደግሞ በደል የደረሰባትን ሴት ምስል ፎቶ ለጥፎ፣ ለገዳይና ጥፋት አድራሽ ከለላ መሰጠቱ ነው። ማኅበራዊ ሚድያው ላይ ያሻንን ጊዜ አጣቅሰን ብንቃኝ፣ የገዳይ ሳይሆን የተበዳይ ምስል ነው ሲንሸራሸር የሚገኘው።
ውጪ አገር አንድን ከባድ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ምስል በዓለማቀፍ ሚድያዎች ሳይቀር ይዘዋወራል። ይህ ሰው ነገ በሕይወቱ ተለውጦና ተሻሽሎ ከእስር ሊወጣ የመቻል እድል እንዳለው ግልጽ ነው። ነገር ግን በደል ያደረሰባት ሴት ላይ የፈጸመው ጠባሳ እንደማይጠፋ ሁሉ፣ ምስሉ በይፋ መታየቱን ጥፋት በቀላል እስር የሚታለፍ እንዳልሆነ ማሳያና ማስተማሪያ መሆን ስለሚገባው ነው።
በአንጻሩ ግን በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጥቃት የደረሰባት ሴት ምስል ይወጣል፣ ማንነቷ ከቤተሰቧ ጭምር ይገለጣል። ይህ ከከንፈር መጠጣ የሚያልፍ ነገር የሚያመጣ አይደለም። ይልቁንም ንቃት በሚቀረውና ገና ብዙ ግንዛቤ በሚፈልግ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ መገለልና ሐሜታ ሲከተሏት እንዲኖሩ ያደርጋል። በዚህ የተነሳ ስንት ሴቶች መኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀዋል፤ ራሳቸውን ያጠፉትም ቁጥራቸው ቀላል አይደል።
እጠይቃለሁ! እስከ መቼ ነው አጥፊዎች መልካቸው ማንነታቸው የሚደበቀው? የለም! አጥፊዎች ቢሆኑም ወደፊት ታርመው ለሚኖራቸው ኑሮ እንጨነቃለን ተብሎ ከሆነ፣ እንግዲያው ጥቃት ለደረሰባት ሴትም ክብር ይሰጥ! እረሷም ነገ የምትለው ቀን አላትና ይታሰብላት። ጥቃቱ ከሞት ያደረሳት ሴትም የሚወዳት የሚሳሳላት ቤተሰብ አላትና፣ ለቤተሰቧ ክብር ይሰጥ!
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014


