መነሻ ገጽዜናወቅታዊሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑበት ደቡብ ወሎ ዞን

ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑበት ደቡብ ወሎ ዞን

ዕሮብ ግንቦት 03/2014፤ በዞኑ መቀመጫ ደሴ ከተማ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እያቀኑ ነበር። ሆኖም በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች እንዳሉ ተማሪዎች እየተሳሳቁና እየቦረቁ ሰብሰብ ብለው የመሄዱን ነገር በሰፊው ሲከውኑት አይታይም። ከዚያ ይልቅ ሁሉም ባይሆን ብዙዎች በተሰላቸ ሞራልና ፈገግታ በራቀው ፊት ይጓዛሉ።

ለምን? ይህንን በሚመለከት አንድ ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የሥነልቦና ባለሙያ ተጠይቀው ሲያስረዱ፣ ጦርነት ካበቃ በኋላም በሰዎች ላይ የሚያሳደረው የሥነልቦና ጫና ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

በተለይ ተማሪዎች ደግሞ በለጋ አዕምሯቸው ያዩት ነገር በቀላሉ እንደማይጠፋና ከፍተኛ የሥነልቦና ቀውስ እንደሚያሳድርባቸው ይገልጻሉ። ቀደም ብሎ የተፈጠረውን ነገር በቀላሉ መርሳት ባለመቻላቸውም ይሆናል፣ ብዙዎች እንደ በፊቱ እየቦረቁና ዘና ባለ መንፈስ ሲንቀሳቀሱ የማይታዩት ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ፣ ወረቃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹትም፣ በትምህርት ቤቱ በየክፍሉ በአማካይ ከአራት ያላነሱ ተማሪዎች ከጦርነቱ በኋላ እንዳልተመለሱ ገልጸዋል። አያይዘውም አሁን የምናስተምረው ሁሉም ነገር የተሟላ ስለሆነ ሳይሆን ባለው ቁሳቁስ ማስተማር አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

መምህሩ አክለውም፣ ክፍል ውስጥ እየተማሩ የሚያስቡት በጦርነቱ ወቅት ስላዩትና ስላሳለፉት ስቃይ ነው ካሉ በኋላ፣ ችግሩ በተማሪዎች ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያስተናገደችው ባለው አስከፊ ግጭት ብሎም ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን በተነሳው ጦርነት ጉዳት ያላስተናገደ ዘርፍ እንደሌለ ይነገራል።
ሆኖም የትምህርት ዘርፉ ደግሞ የበለጠ አስከፊ ውድቀት ውስጥ እንደሚገኝና በየቦታው በሚከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል።

ለአብነትም በትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች እስከ አሁን ባለመከፈታቸው ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችና ከ48 ሺሕ በላይ መምህራን ከትምህርት ስርዓት ውጭ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ አይዘነጋም።
በአፋር፣ በአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችም በተለያዩ ተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች የተነሳ ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ በርካታ ተማሪዎች ስለመኖራቸው በትምህርት ሚኒስቴርና በክልል ትምህርት ቢሮዎች በኩል ሲገለጽ ቆይቷል። ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞም ከ7 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸው ቀደም ብሎ ተገልጿል።

ሆኖም በቅርቡ የአማራ ክልል ዩንቨርሲቲዎች ፎረም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር ይፋ በተደረገ ጥናት፣ ሕወሓት ወረራ ባደረገባቸው በስምንት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 87 ወረዳዎች እና 945 ቀበሌ አስተዳደሮች በሚገኙ 1 ሺሕ 145 የትምህርት ተቋማት ላይ ውድመትና ዘረፋ መካሄዱ ተጠቅሷል።

በዝርዝር ሲታይም 104 ቅድመ መደበኛ፣ 928 አንደኛ ደረጃ፣ 108 ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 5 የመምህራን ኮሌጆች ላይ ሕወሓት ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፣ ዘረፋም ፈፅሟል ሲል ያብራራል፤ ጥናቱ።
በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመማሪያ ሕንፃዎች፣ ቤተ-ሙከራዎች፣ መጽሐፍት፣ የትምህርት ግብዓቶች እና የትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። በድምሩ 5 ቢሊዮን 917 ሚሊዮን 953 ሺሕ 429 ብር ውድመት መድረሱን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ 3 የፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች (ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ) የከፋ ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ይህም ጉዳት በገንዘብ ሲተመን 19 ቢሊዮን 423 ሚሊዮን 611 ሺሕ 67 ብር ነው ተብሏል።

በዚህ የተነሳም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል አስቸጋሪ ሁኔታ እንደፈጠረባቸው ይነሳል። ይባስ ብሎም ተማሪዎች ወላጆቻቸውን በሞት ስላጡ እንዲሁም ወላጆች ችግር ውስጥ በመውደቃቸው ቀላል የማይባሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንዳልቻሉና ከተመለሱት ውስጥም ያቋረጡ ስለመኖራቸው ተገልጿል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጦርነቱ ያበቃ ሰሞን በጦርነቱ ሳቢያ ከ4 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውንና ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚልቁ ተማሪዎች እንዲሁም 116 ሺሕ ገደማ መምህራን ከትምህርት ገበታ ውጭ ስለመሆናቸውና ትምህርት ቤቶችን ጠግኖ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ለመመለስና ትምህርቱን ለማስቀጠል ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለጹ ይታወሳል።

በደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አሕመድ አደፋ፣ በዞኑ 1 ሺሕ 241 አንደኛ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 67 ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች በ2014 የትምህርት ዘመን 388 ሺህ 918 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎችና 102 ሺሕ 148 የኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተመዝግበው ነበር።

ሆኖም ከጦርነቱ በኋላ ተቋርጦ የቆየው ትምህርት እንደገና ሲጀመር በመማር ላይ ያሉት ቀድሞ ከተመዘገቡት ያነሰ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው፣ ከ11 ሺሕ በላይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ከ2 ሺሕ በላይ የኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ በአጠቃላይ ከ14 ሺሕ የሚልቁ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ብለዋል።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን በምን ምክንያት አቋረጡ?
በደቡብ ወሎ ዞን ትምህርታቸውን ካቋረጡ ተማሪዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ከጦርነቱ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ያልተመለሱ ናቸው ተብሏል። ይህም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ፣ ወላጆቻቸው ያላቸውን ነገር ስለተዘረፉ ማስተማር ባለመቻላቸው እንዲሁም አካባቢያቸውን ጥለው የተሰደዱ በመኖራቸው እንደሆነ ተመላክቷል።

ቀሪ 25 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ወደ ትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ በዋናነት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርቱን ስለማቋረጣቸው ነው የተነገረው።

በዞኑ በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት
ቡድን መሪው እንዳስረዱት፣ 423 ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ 140 የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት፣ 246 ትምህርት ቤቶች መካከለኛ ጉዳት እንዲሁም 37 ትምህርት ቤቶች ቀላል ጉዳት አስተናግደዋል። ከፍተኛ ጉዳት የሚባለውም፣ በከባድ መሣሪያ ተመተው የፈረሱ፣ መማሪያ ክፍላቸውና ግቢያቸው ለሞቱ የሕወሓት ታጣቂዎች የመቃብር ስፍራ የሆኑ፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተሙከራቸው የወደመ፣ መማሪያ ወንበሮች እና ሌሎች ለመማር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች የወደመባቸው ስለመሆናቸው ተገልጿል።

ጉዳት ከደረሰባቸው 14 የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በተጨማሪ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተቋምም ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት እንደተፈጸመበት ነው ለማወቅ የተቻለው። በዞኑ በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲለካም 494 ሚሊዮን 221 ሺሕ 621 ብር ይሆናል ተብሏል።

- ይከተሉን -Social Media

በተለይ ወረባቦ፣ አምባሰል፣ ደላንታ እና ወረኢሉ ወረዳዎች ከባድ ጦርነት የተካሄደባቸው መሆኑን ተከትሎ በእነዚህ ቦታዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የደረሰው ጉዳት እንዲሁም ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ነው የተገለጸው። ማኅበረሰቡ ከጦርነት በኋላ እህሉ ተወስዶ፣ በተለይ ሸጦ ለልጆቹ ማስተማሪያ የሚጠቀማቸው በጎቹ፣ ፍየሎቹና ከብቶቹ ታርደው በመበላታቸው ልጆቹን ማስተማር እንዳልቻለ ተነግሯል።

ሦስት የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችና አራት ርዕሰ መምህሮች የሞቱ ሲሆን፣ 183 የአንደኛ ደረጃና 56 የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ሥራቸውን ለቀዋል። መምህራኑ ከጦርነቱ በኋላ ወደ ማስተማር ሥራቸው ስላለመመለሳቸው እንጂ በምን ምክንያት እንዳልተመለሱ ግን በግልጽ መናገር እንደማይቻል ነው የተጠቆመው።
በተጨማሪም ለዚሁ ዘርፍ አገልግሎት የሚውሉ 28 ሞተር ሳይክሎችና 6 መኪኖችም ስለመዘረፋቸው ተገልጿል።

ችግሩን ለማቃለል የሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች
ምንም እንኳን ከችግሩ ስፋት አንጻር በፍጥነት ማስተካከል ባይቻልም፣ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ዘግይተው ከጀመሩ ትምህርት ቤቶች በስተቀር፣ ዞኑ ጦርነቱ ከቆመ ብዙም ሳይቆይ ታህሳስ 14/2014 ባልተያዙ አካባቢዎች ትምህርት አስጀምሯል። ከአንድ ሳምንት በኋላ ተይዘው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ባለው ነገር የተቻለውን ኹሉ በማድረግ በማስተማር ላይ ይገኛልም ነው የተባለው።

በዚህ ወቅትም ኹሉም ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ ይሁኑ እንጂ፣ የተመቻቸ ሁኔታ እንደሌለና የጎደለው ነገር በርካታ ስለመሆኑ፣ ጥቁር ሰሌዳቸው የተቀደደ፣ ወንበሮቻቸው የተሰባበረ በር የሌላቸውና በጥቅሉ ለመማር ምቹ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች በብዛት እንዳሉ ተመላክቷል።

‹‹ሆኖም በአንድ ጊዜ ሁሉም አይስተካከልም፣ መንግሥትና ሌሎች አካላት ድጋፍ እያደረጉ ችግሮችን ለማቃለል እየተሠራ ነው።›› ያሉት ቡድን መሪው አሕመድ አደፋ ናቸው።

በዚህም ተማሪዎች ትምህርት ሲጀመር ለ11 ትምህርት፣ ኹለትና ሦስት ደብተር ይዘው መምጣታቸውን አስታውሰው፣ ለዚህ ምላሽ ይሆን ዘንድ ኢትዮ ቴሌኮም የ3 ሚሊዮን ብር ደብተር እንዲሁም እንደ አማራ ልማት ማኅበር (አልማ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አደጋ ጊዜ ፈንድ (UNICEF) እና ሌሎች አካላት ድጋፍ ስለማድረጋቸው ገልጸዋል። መሰል ድጋፎች ባይኖሩ ኖሮ፣ አሁን በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ግማሽ ያህል በትምህርት ቤቶች ማግኘት እንደማይቻል አስረድተዋል።

የተጎዱ ትምህርት ቤቶችንም ከትምህርት ሚኒስቴርና ከትምህርት ቢሮ በጀት ተመድቦ የጥገና ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ያወሱት ቡድን መሪው፣ ትምህርት ሚኒስቴር 30 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ይዞ ቦታ መምረጡንና የክልሉ ትምህርት ቢሮ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ለጥገና በጅቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት። ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ገቢ እንዲሁም በሲቪል ማኅበራት እርዳታ የሚሠሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ስለመኖራቸውም አክለዋል።
በዚህም በተለይ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት 54 ሚሊዮን 810 ሺሕ 392 ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን፣ ድጋፉም ለተማሪዎች መማሪያነት እንዲውል ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

የሥነልቦና ጫና
እንደ ቡድን መሪው አሕመድ አደፋ ገለጻ፣ ከሁሉም በላይ በተማሪዎች ላይ የደረሰው የሥነልቦና ጫና የከፋ ነው። ሰው ሲገደል ተመልክተዋል፣ መንገድ ላይ የሞተ ሰው አስክሬን ዐይተዋል፣ ወላጆቻቸው ሊገደሉ ሲጠፈሩ ያዩ ነበር፣ ሲደፈሩ ሲገረፉ ሲሰደቡና ሲሰቃዩ የተመለከቱ በመሆናቸው፣ ይህን ሁሉ በአዕምሯቸው ይዘው ነው ለመማር የሚመጡት። ይህም በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ያለው አሉታዊ ጫና አስከፊነት ግልጽ ነው ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ይህም በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ባለሙያዎችና በመምህራን ላይም ተመሳሳይ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ‹‹እኛም ደሴ ከተማ በተያዘችበት ወቅት ቢሯችንን እየመጣን እናየው ነበር። በወቅቱ ሁሉንም ነገር እንዳልነበር አድርገው ሲያወድሙት ዳግም ሥራ እንጀምራልን የሚል እምነት አልነበረንም። አሁንም ቢሆን የሕሊና ጫናው በጣም ከባድ ነው።›› ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ በማሰብም ለመምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ለትምህርት ባለሙያዎች የሳይኮ-ሶሻል ሥልጠና እየተሰጠ ስለመሆኑ አመላክተዋል። ተማሪዎችም በሠለጠኑ መምህራን በኩል ሥልጠናው ይሰጣቸዋል ነው ያሉት።

ያቋረጡ ተማሪዎች በምን መልኩ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሊመለሱ ይችላሉ?
በዞኑ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ከ14 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሊመለሱ የሚችሉና ሊመለሱ የማይችሉ ተብለው በሁሉም ወረዳዎች የተለዩ ሲሆን፣ መመለስ የማይችሉት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ እንዲሁም ለሥራ ፍለጋ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሌላ ቦታ የሄዱ ናቸው ተብሏል።

እነዚህን ተማሪዎችም አግኝቶ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደማይቻል የተገለጸ ሲሆን፣ ፈተና ሲቃረብና በችግር ምክንያት ያቋረጡትን በቅስቀሳ እንዲሁም በመንግሥትና በሌሎች ድጋፍ ሰጭ አካላት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለመመለስ ጥረቶች ይደረጋሉ ነው የተባለው።

በአንጻሩ አሁን በመማር ላይ ከሚገኙትም ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ ስለመሆኑና ውጤታማ ስለመሆናቸው የሚነሳው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ወደፊትም ትምህርት ሊያቋርጡ የሚችሉ ተማሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋቶች ይነሳሉ።
በተጨማሪም፣ በሕወሓት ኃይሎች ለወራት በቁጥጥር ስር በነበሩት በተለይ ሰሜን ወሎ ዞን እንዲሁም ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር ከዚህ እንደሚልቅ፣ እንዲሁም በዘርፉ የደረሰው ቁሳዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ ከአማራ ብሔራዊ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ ለማግኘት ደጋግማ ብትደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች