መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበሩ ቦታዎች ቤተመጻሕፍት በሙሉ ወድመዋል ተባለ

በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበሩ ቦታዎች ቤተመጻሕፍት በሙሉ ወድመዋል ተባለ

በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበሩ የአፋርና አማራ ክልል ቦታዎች ቤተመጻሕፍት በሙሉ ወድመዋል ሲል የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ተቋሙ በአፋርና አማራ ክልል ሰባት ዞኖች አካሄድኩት ባለውና ለአዲስ ማለዳ በላከው የጥናት ሰነድ መሠረት፣ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች ቤተ-መጻሕፍት እና ቁሳቁሶቻቸው በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ በርካቶች አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ሲል አብራርቷል።

አገልግሎት የጀመሩትም ቢሆን የሚሰጡት አገልግሎት ከወትሮው የተጓደለ እና በቂ ያልሆነ ነው ያለው ተቋሙ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የተማሪዎች ሰነዶች፣ የቤተ-መጻሕፍት ሕንጻዎች፣ ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች፣ የተማሪዎች ሪከርድ ቢሮዎች፣ ወንበሮች፤ የመማሪያ ክፍሎች፣ ኮምፕዩተሮች፤ መረጃ ማስቀመጫ ቋቶች እንዲሁም ቤተ-ሙከራዎች በሰፊው ወድመዋል በማለት አስታውቋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል ጋይንት ወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በውስጣቸው የሚገኙት ቤተመጻሕፍት በአብዛኛው ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ፣ የወደሙት መጻሕፍት 3 ሚሊዮን ብር ያህል የሚገመት ዋጋ ነበራቸው ነው የተባለው።

የቅዱስ ላሊበላ አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁ በደረሰበት ጉዳት ቤተመጻሕፍቱን ወደነበረበት መልሶ እንደገና ለማቋቋም 1 ሚሊዮን 270 ሺሕ ብር እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አመላክቷል። በመቄት ወረዳ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ላይ በተደረገ ጥናትም ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት መድረሱ ነው የተጠቆመው።

በሰሜን ሸዋ ዞንም መጻሕፍት እንደጠፉባቸውና የጠፉትን መጻሕፍት ብዛትና ዋጋ ግምት ባስቀመጡ አብያተመጻሕፍት ላይ መጻሕፍትን ብቻ በሚመለከት 542 ሺሕ 384 ብር የሚገመት ጉዳት መድረሱን ጥናቱ ይገልጻል። በደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ያለ የጉዳት ሪፖርት ባቀረቡ የትምህርት ቤትና የሕዝብ አብያተ መጻሕፍት ላይ ከ18 ሚሊዮን 228 ሺሕ ብር በላይ የሚደርስ ንብረት እንደወደመ ተመላክቷል።

በአፋር ብሔራዊ ክልል በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም እንዲሁ በቤተ መጽሐፍት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ለአብነትም በሚሌ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ ወይም ለልዩ ኃይልና ለመከላከያ እንደ ካምፕ ሆነው እንዲያገለግሉ የተደረገ ሲሆን ይህም በአብያተመጻሕፍት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል ነው የተባለው።

በሌላ በኩል፣ በብዙ ቦታዎች የተለያዩ ሰነዶች መውደማቸውም በጥናቱ ተመላክቷል። ይህም በመበታተን፣ በመቦጫጨቅ፣ በመዝረፍ፣ በቢሮ ደረጃዎች ላይ በመበተን፣ በመስኮት በመወርወር፣ አውጥቶ ዝናብ ላይ በመጣል፣ በሰነዶች ላይ በመጸዳዳት እንዲሁም ለሽንት ቤት መጠቀሚያም በማድረግ ሰነዶች እንዲወድሙ መደረጉ ነው የተጠቀሰው።

መጻጽፎች፣ ሪፖርቶች፣ እቅዶች፣ ቃለጉባኤዎች፣ የፕሮጀክት ሰነዶች፣ ይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች፣ የሠራተኛ ፋይሎች፣ የተማሪዎች ሰነዶች፣ የታካሚ ሰነዶች፣ የታራሚዎች አያያዝ ሰነዶች፣ በፍርድ ሂደት ላይ የነበሩ ጉዳዮችን የያዙ ሰነዶች፣ የፖሊስ የምርመራ መዝገቦች፣ ቃለጉባዔዎች፣ አጀንዳዎች፣ በአጠቃላይ የፍርድ ቤት፣ የፋይናንስ፣ የገቢዎች፣ የጤና ጣብያዎችና የባህል ቱሪዝም ሰነዶች ወድመዋል ተብሏል።

ለሰነድ አያያዝ ሥራ አጋዥ የነበሩ ኮምፕዩተሮች፣ ማህተሞች፣ የወረቀት መብሻዎች፣ ስቴፕለር መምቻ፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶችም መውደማቸው ተመላክቷል።
በሰነዶች የደረሰው ጥፋት ተቋማቱን ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል የተባለ ሲሆን፣ በተለይ በኮምፕዩተር የተያዙ መረጃዎች መጥፋት ብዙ ነገሮችን እንዳወሳሰብ ጥናቱ ገልጿል።

ተቋማቱ የአብያተ መጻሕፍቱን ጉዳት ለብቻ ሪፖርት ባለማድረጋቸውና አንዳንድ ተቋማት ደግሞ የመጻሕፍት ዋጋን አጋንነው ሪፖርት ያደረጉበት ሁኔታ በመኖሩ፣ የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ለመግለጽ አስቸጋሪ መሆኑ ተገልጿል።

ሆኖም ተቋሙ ጥናት ከመካሄዱ በፊት በጎንደር ዙሪያ፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ በሚገኙ አምስት ቦታዎች፣ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 16 ሺሕ 800 የሚደርሱ መጽሐፍትን ድጋፍ ማድረጉን ገልጾ፣ አሁንም ጥናቱን መነሻ በማድረግ የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ፣ ለዐስር ትምህርት ቤት ቤተመጽሐፍትና ለአንድ ሕዝብ ቤተመጽሐፍ በዚህ ወር እናደርሳለን ሲል አሳውቋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች