ከ 380 ሚሊዮን ብር በላይ ሕገ ወጥ ደረሰኝ ሸጠዋል የተባሉ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

0
757

በሕጋዊ መልኩ ከገቢዎች ሚኒስቴር በተገኙ እና በተሰወሩ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በመጠቀም በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከኹለት ሳምንት በፊት ከ380 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀሰተኛ ደረሰኝ ሲሸጡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

በአንድ አስጎብኚ ድርጅት ስም የወጡት እነዚህ መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነውም የድርጅቱ ባለቤት ተመላሽ ለመጠየቅ ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር ባመሩበት ወቅት እሳቸው እንደማያውቋቸው በመግለፅ ለፌደራል ፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን እሱን ተከትሎ በተሰራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።

ፌደራል ፖሊስ ባደረገው ክትትል አማካኝነት በአዲስ አበባ 22ማዞሪያ አካባቢ በሚገኝ አነስተኛ የኮንቴይነር ቤት ውስጥ ኹለት ሕገወጥ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን፣ ኮምፕዩተሮችን፣ ፕሪንተር እና ሌሎችም ተያያዥ መሣሪያዎችን በኤግዚቢትነት እንደያዘም ለማወቅ ተችሏል። ከተያዙት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችም አንዱ ላይ ብቻ ከ380 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ሕገወጥ ደረሰኝ የታተመበት መረጃ መገኘቱን በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አምደሚካኤል ጌታቸው ተናግረዋል።

‹‹አንደኛው የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ላይ ግን ምንም መረጃ ያልተገኘ ሲሆን ምን አልባትም ደረሰኞቹን ከቆረጡ በኋላ መረጃው ተሰርዞ ይሆናል በሚል ወደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኀንነት ኤጀንሲ ተልኮ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎቹን ከገቢዎች ሚኒስቴር የወሰዱት ኹለት ግለሰቦች ወደ መኖሪያ አድራሻቸው በመሔድ በተደረገው ክትትልም፣ ያስመዘገቡት መታወቂያ ሕገወጥ ሲሆን ይህንን ተጠቅመው መሣሪያዎቹን ማውጣት መቻላቸውን ፖሊስ አረጋግጫለሁ ሲል በምርመራ መዝገቡ አስፍሯል።

ደረሰኞቹን ሲያዘጋጅ ነበር የተባለው እና ስምንት ሰዎች በተካተቱበት መዝገብም አንደኛ ተከሳሽ የሆነው አልአዛር ገዛኸኝ ከነ መሣሪያዎቹ እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሲሆን፣ መሣሪያዎቹን በሽያጭ እንዳገኛቸው ለፖሊስ መናገሩንም አምደ ሚካኤል ተናግረዋል።

ፖሊስ ወደ አልአዛር እስከሚደርስም ሕገወጥ ደረሰኙን ተጠቅሞ ተመላሽ የጠየቁትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን እሳቸውም ከየት እንዳገኙት መርተው አሳይተዋል ተብሏል። ደረሰኙን ባቀረቡት ግለሰብ እና በአልአዛር መካከልም ሰባት የሚሆኑ ግለሰቦችን በያዘ ሰንሰለት ፖሊስ ምርመራ አካሒዶ ሁሉም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከገቢዎች ሚኒስቴር ፈቃድ ወጥቶባቸው የተወሰዱ ከ 400 በላይ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ያሉበት እንደማይታወቅ እና በየዓመቱም ግብይታቸውን እንደማያሳውቁ የገቢዎች ሚኒስቴር በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወቃል። ድርጅቶቹም ወጪአቸውን በማሳበጥ ግብር ለመሰወር እንዲሁም ባልከፈሉት ግብር ተመላሽ ለማግኘት እነዚህን ሀሰተኛ ደረሰኞች ይጠቀማሉ በማለት ሲገልፅ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመትም የገቢዎች ሚኒስቴር ካሉት ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መካከል ከ703 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ከ 1580 በላይ ሀሰተኛ ደረሰኞች የተገኙ ሲሆን በ 50 ከፍተኛ ግብር ከፋይ ድርጅቶች ላይ በተደረገ ምርመራ 22ቱ የ 8.5 ቢሊዮን ብር ኦዲት ክፍተት ተገኝቶባቸው ነበር። በመሆኑም እነዚህ የጠፉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች እነዚህን ሀሰተኛ ደረሰኞች ለማተም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይገመታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here