በአክሱም የሚገኘው የሃ ሆቴል በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ሊያካሒድ ነው

0
253

በቱሪስት መዳረሻ አክሱም ከተማ ከተገነባ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሃ ሆቴል የማስፋፋፊያ ግንባታ ለማካሔድ ሲባል ለቀጣይ 18 ወራት ሆቴሉ አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታወቀ።

የዛሬ 11 ዓመታት በፊት ወደ ግል ይዞታ በ20 ሚሊየን ብር የተዘዋወረው ሆቴሉ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ግንባታ ለማካሔድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጿል።

ግንባታው በኹለት ዙር የሚካሔድ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር በቀጣይ ወር ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ስምንት ወራት የሚወስድ ሲሆን ኹለተኛውም ዙር በተመሳሳይ ወቅት እንደሚጠናቀቅ የሆቴሉ አስተዳደር አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው ለማካሔድ ጨረታ ለማውጣት እና ኮንትራክተር ለመምረጥ ዝግጅት መሆኑንም አስተዳደሩ ይፋ አድርጓል።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው ሆቴሉ በአሁኑ ወቅት 60 መኝታ ቤቶች ያሉት ሲሆን ማስፋፊያው ቁጥሩን በ254 ቁጥሩን ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በጎንደር ከተማ ከሚገኘው ጎሃ ሆቴል እና በላሊበላ ከሚገኘው ሮሃ ሆቴል ጋር በተመሳሳይ ወቅት የተገነባው ከፍተኛ የገቢ መቀነስ እና የደንበኞች ቁጥር መቀነስ ገጥሞት የነበረ ሲሆን ለዚህም ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ደካማ እና ዘመናዊ አለመሆኑ ነበር።

የየሃ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አምዶም ተክሌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ድርጅቱ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው አክሱም ከተመሰረተ ከ50 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም የሚያገኘው ገቢም ሆነ የሚሰጠው አገልግሎት እምብዛም ነው።

“በተለይም ማስፋፊያው ይህንን በመቅረፍ ትልቅ ሚና ይኖረዋል” ያሉት አምዶም “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለአገሪቷ እንደሚያስገኝም” ገልፀዋል።

በተሠራው ዲዛይን መሰረት ሆቴሉ ከዘመናዊ ክፍሎች ባሻገር መሰብሰቢያ አዳራሾች እና የሔሊኮፕተር ማረፊያ የሚኖረው ሲሆን የቱሪስት ቆይታ ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ማስፋፊያውን ለማካሔድ የሥነ ምኅዳር እና ከርሰ ምድር ጥናት ተደርጎ የተጠናቀቀ ሲሆን የሆቴሉ አስተዳደር ከኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ይሁንታ አግኝቷል።

የባለሥልጣኑ የአክሱም ቅርሶች አካባቢ ዋና ኀላፊ ሚካኤል ተስፋይ ለድርጀቱ የግንባታ ፈቃድ መሰጠቱን ያረጋገጡ ሲሆን ዲዛይኑ ከአክሱም ቅርሶች ጋር ያለው ዓውድ የተጣመረ እንዲሆን በባለሙያዎች ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።

ፀጋዬ ዓለማየሁ የተባሉ ባለሀብት ንብረት የሆነው ሆቴሉ ከአክሱም ሃውልት 200 ሜትር ርቀት የሚገኝ ሲሆን ተራራ ላይ በመቀመጡ ቱሪስቶች የአክሱም ቅርሶችንና ከተማውን ሙሉ ለሙሉ ማየት ያስችላል።

ከየሃ በተጨማሪ በአክሱም ከተማ ከ90 በላይ ሆቴሎች የሚገኙ ሲሆን ያፈሰሱት አጠቃላይ መዋዕለ ንዋይ ወደ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ይደርሳል።
በባለፈው በጀት ዓመት ወደ 18 ሺሕ የሚጠጉ የውጭ ዜጎች የአክሱም ከተማን የጎበኙ ሲሆን ወደ 41 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ከተማዋን ጎብኝተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here