ዳሰሳ ዘ ማለዳ ማክሰኞ መስከረም 6/2012

0
889

1-በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋን አጠናክሮ ለማስቀጠል ፣ በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደምርት ለመግባት የሚያስችል የነዳጅ ሥራዎች ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ። ረቂቁ በነዳጅ ማውጣት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ በክልሎችና በፌደራል መንግስት ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታውቋል። (አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………

2-በሐምሌ ወር 2011 ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ40 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።  252 ነጥብ 19 የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዶ የተገኘው ገቢ 252 ነጥብ 23 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል፡፡(አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………

3- ከብራዚል ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪ የነበሩ ኹለት ናይጀሪያውያን አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች በሆዳቸው ይዘውት የነበረው ዕፅ በመፈንዳቱ ለህልፈት ተዳርገዋል። (አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………

4የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሠረተ ልማቱንና አገልግሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሚያስችል የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላንኒግ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ በማደረግ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ። ደንበኞች የፍጆታ ክፍያቸውን በባንክ ወይም በየትኛውም የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎች መክፈል እንደሚያስችል የታወቀ ሲሆን ይህም ተቋሙን ከማዘምን ባለፈ ተጠቃሚውን ለመድረስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሆነም ገልጿል። (አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………

5-በአዲስ አበባ ከተማ  11 ባለኮከብ ሆቴሎች ግንባታ ወደ ትግበራ እንዲገባ የከተማዋ ካቢኔ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።ሆቴሎቹን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚገነቧቸው እንደሆነም  ተገልጿል።(ዋልታ)

……………………………………………………

6- -በአዲስ አበባ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከ22 ሺህ በጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው ደም ሆስፒታሎች የደም ዕጥረት እንዳያጋጥማቸው ማድረጉን የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።ባለፈው ሐምሌ 1/2011 በተጀመረው የበጎ ፈቃድ የደም መስጠት መርሃ ግብር 14 ሺሕ ከረጢት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ 22 ሺሕ ከረጢት ደም ማግኘት መቻሉን ተነግሯል።(ኤዜአ)

……………………………………………………

7 በአዲስ አበባ የተበላሹ መንገዶች ከመጪው ጥቅምት 1/2012 ጀምሮ ጥገና እንደሚደረግላቸዉ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታዉቋል።ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ይሸፍናል ተብሎ የሚጠበቀዉ ይህ የጥገና ስራ ባለፉት ሐምሌ እና ነሐሴ 2011 በጊዜያዊነት በሲሚንቶ የተጠገኑትንም አፍርሶ እንደ አዲስ መገንባትንም እንደሚጨምር ተገልጿአል። (ሸገር)

 

……………………………………………………

8- -ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት አብራሪ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ቀጠናዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል።ስብሰባውን የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ሲከፍቱ እንደተናገሩት በአቪየሽን ዘርፍ የደኅንነት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል።ስብሰባው ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ አብራሪዎች ማኅበርን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የአብራሪዎች ማኅበራትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here