የሻምቡ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

0
1003

አርብ ግንቦት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሻምቡ ከተማ የተገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አሸናፊ ሙሉብርሃን እንዳስታወቁት፤ ማከፋፈያ ጣቢያው ለሻምቡ ከተማ እና ለአሊቦ ቀበሌ በአማካኝ ኹለት ሜጋ ዋት ኃይል እየሰጠ ይገኛል፡፡

ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመር እና ስድስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉት ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

ከወጪ መስመሮቹ ኹለቱ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ አራቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን በመጠባበቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ኹለት ትራንስፈርመሮች፣ አንድ የኃይል መቆጣጠሪያ ክፍል እና የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ሥርዓት አሉት፡፡

ፕሮጀክቱን ለመገንባት አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡

የቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ በዋና ተቋራጭነት፤ አገር በቀሉ መላ ኢንጂነሪንግ የሲቪል ሥራውን በንዑስ ተቋራጭነት ሲያከናውኑት የጣሊያኑ ኢ.ኤል.ሲ ኤሌክትሮ ኮንሰልት ደግሞ የማማከር ሥራውን አከናውኗል፡፡

ከአዲስ አበባ በ335 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፤ በሻንቡ ከተማ የተገነባው የማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢው ማህበረሠብ እና የማምረቻ ፋብሪካዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here