የአፍሪካ ቀንድ ቅርምት እና ኢትዮጵያ

0
1265

መረጋጋት የተሳነው የአፍሪካ ቀንድ ከምዕራባውያን አገራት፣ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ እና የሩቅ ምሥራቅ አገራት ለጦር ቀጠናነት እየተሻሙበት ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ ሁሉ መነሻ እና መድረሻ ምንድን ነው?በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች የእህት መጽሔታችን ‹ኢትዮጰያን ቢዝነስ ሪቪው› ዋና አዘጋጅ ሳምሶን ብርሃኔ ያጠናቀረውን ጽሑፍ ለአዲስ ማለዳ አንባቢያን ታምራት አስታጥቄ ተርጉሞታል።

በታሪክ ተመዝግቦ እንደምናገኘው የአፍሪካ ቀንድ ከቀደመው ኦቶማን ቱርክ እስከ ሶቪየት ኅብረትና ምዕራባውያን ፍጥጫ ብሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የባሕረ ሠላጤው አገሮች እና እስያዊቷ ቻይን ጨምሮ ሌሎችም ተፅዕኗቸው እየበረታ መጥቷል። ይህ የሆነበት ዐቢይ ምክንያት ወሳኝ የዓለም ዐቀፍ ንግድ መሥመር መሆኑ ነው። በአንድ በኩል ሕንድ፣ ቻይናና ጃፓን የወጪ ንግዳቸውን በባብኤል መንደብ በኩል ወደ አውሮፓ ለማስገባት ሲጠቀሙበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የባሕረ ሠላጤው አገራት ማለትም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳኡዲ አረቢያ የኤደንን ባሕረ ሠላጤ፣ የባብኤል መንደብንና የቀይ ባሕር መሥመሮችን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ያጓጉዙበታል።
ሌላው የአፍሪካ ቀንድ ዋና የአፍሪካ ገበያ መግቢያ በር በመሆን በማገልገሉ የዓለም ኃያላንን ለመማረክ ችሏል። በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አገራትም ባለወደብ ከሆኑት ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ጋር የኢኮኖሚና ፖለቲካ ትስስር እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።
የአፍሪካ ቀንድ መልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ ፋይዳ የዓለም ኃያላን አገራት እሽቅድምድም የፍልሚያ አውድማ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ከመካከለኛው ምሥራቅ በመቀጠል ትልቁ የኃያላን መተጋተጊያ ሜዳ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ ተንታኙ ሰለሞን መብሬ (ዶ/ር) “የከባቢው ታሪክ በውጪ ኃይሎች ተፅዕኖ ቅርፅ እንዲይዝ ተደርጓል” ይላሉ። በሌላ በኩል በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው ኬሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና የአፍሪካ ቀንድ መልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ ተንታኙ አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) እንደሚሉት ብዙዎቹ ኃያላን አገሮች የአፍሪካ ቀንድን የስዊዝ ካናል (ማስተላለፊያ) ቅጥያና ከ1967ቱ የእስራኤል-አረቦች ደም አፋሳሽ የስድስት ቀናቱ ጦርነት ጋር ብቻ በማያያዝ ይመለከቱታል።
በአጠቃላይ ቀጠናው ለፖለቲካ እና ደኅንነት ጉዳይ ባለው ፋይዳ ላይ ባተኮረ ሁኔታ ቢታይም በባብኤል መንደብ ሰርጥ በኩል የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ በኃያላኑ የዘወትር ጥበቃ ውስጥ ነው። ይሁንና በ1970ዎቹ የእስራኤል አጋር የነበሩት ምዕራባውያን በአረብ አገራት የቅጣት በትራቸውን በማንሳት የነዳጅ ምርታቸው እንዲቀንስ አድርገዋል። በዚህ የነዳጅ እጥረት ምክንያት ሱዳን፣ ሶማሊያና ጅቡቲ የኑሮ ዋጋ ማሻቀብ ስላጋጠማቸው የባሕረ ሠላጤውን አገራት ዕርዳታ ለመጠየቅ ተገደዋል፤ በምትኩም የፖለቲካ ታማኝነት ለማሳየት ተስማምተዋል።
ሱዳን እስላማዊ ሪፐብሊክ በመሆኗ፣ ኤርትራ ነጻነቷን በመቀዳጀቷና ሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመዘፈቋ ምክንያት የተፈጠረው ግንኙነት አጭር ለሚባል ጊዜ ብቻ እንዲቆይ ማድረጉን አወል ይናገራሉ። እንደ አወል ገለጻ የባሕረ ሠላጤው አገራት ለቀጣዩ 20 ዓመታት የቀይ ባሕር ቀጠናን ጠቃሚ ሆኖ አላገኙትም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባካሔደችው ጦርነት ምክንያት የወጪና ገቢ ንግዷን ሙሉ በሙሉ ወደ ጅቡቲ ወደብ በማዘዋወሯ የጅቡቲ ወደብ እንዲለማ ዕድል ፈጥሯል። በሌላ በኩል ግን ኤርትራ ያሏት አሰብና ምፅዋ ወደቦች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፤ ሶማሊያም በቀይ ባሕር ላይ እያደገ በመጣው የባሕር ላይ ዘረፋና በውስጣዊ ሠላም እጦት ምክንያት ወደቦቿን ልታለማ አልቻለችም።
የባሕር ላይ ውንብድናዎችና የየመን የእርስ በርስ ጦርነት የቀጠናውንና የዓለም ኃያላንን ትኩረት በመሳቡ ወታደራዊ ሰፈሮችን የመገንባት እሽቅድምድም እንዲኖር አድርጓል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በከፊል የራሳቸውን አስተዳደር በመሠረቱት በሶማሊላንድና በፑንትላንድ ወታደራዊ ሰፈር ከመገንቧቷ ባሻገር በኤርትራ አሰብ ወደብ ላይም ከሳኡዲ አረቢያ ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ወታደራዊ ሰፈር ገንብታለች። ይህንኑ ፈለግ በመከተል ሳኡዲ አረቢያም በጅቡቲ የራሷን የጦር ሰፈር ገንብታለች።
ኃያላኑ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ጀርመን እና ስፔን በተመሳሳይ በቀጣናው የጦር ሰፈር የገነቡ ሲሆን የሁሉም ምርጫ ጅቡቲ ሆናለች። ሩሲያ ቀጠናውን የተቀላቀለች አዲሲቷ ኃያል አገር ስትሆን በምፅዋ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመገንባት በቅርቡ ከኤርትራ ጋር ውል አስራለች፤ በሶማሊላንድ ደግሞ ወታደራዊ ሠፈር ለማቋቋም ፍላጎቷን ገልጻለች።
የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ተቀናቃኟ ግብጽም በቀድሞ መሪዋ ሆስኒ ሙባረክ ላይ በአዲስ አበባ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር የነበራትን ግንኙነትና የአፍሪካ ኅብረት አባልነቷን አቋርጣ ከርማለች። ሆኖም የ2003ቱን የፀደይ አብዮት ተከትሎ ግብጽ በብጥብጥ ስትናጥ ኢትዮጵያ ደግሞ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ መገንባት መጀመሯን ተከትሎ ግብጽ ብዙም ሳትቆይ በ2006 ወደ አፍሪካ ኅብረት አባልነቷ ተመልሳለች፤ ከኤርትራም ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ስትመሠርት በብጥብጥ የሚታመሰውን የደቡብ ሱዳን መንግሥትም በገንዘብ በመደገፍ በቀጠናው ያላትን ተፅዕኖ ጨምራለች።
በሌላ በኩል ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ከጎረቤቶቿ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያልነበራት ኤርትራ በቀጠናው ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመጨመር ግንኙነት ከመሠረተችባቸው አገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋርጣ ከኳታር ጋር አዲስ ወዳጅነት መሥርታለች። ይህም በኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ አስችሏታል። ሆኖም ኳታር ኢትዮጵያንና ኤርትራን ለማስማማት ባደረገችው ሙከራ ግንኙነታቸው ሊቀዛቀዝ ችሏል።
በ2008 ኤርትራ ከሳኡዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የቀረበላትን የአብረን እንሥራ ጥሪ ተከትሎ የፀጥታ ጉዳዮች ትብብር ስምምነትን ከአረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈራረመች ሲሆን ስምምነቱን ተከትሎ የገንዘብ ድጋፍ፣ የመሠረተ ልማት ማስፋፋትና የነዳጅ አቅርቦት ሲያደረግላት፣ ኤርትራ በምትኩ አሰብ ላይ ወታደራዊ ሸፈር እንዲያቋቁሙ፣ የአየር ግዛቷን በመፍቀድ እና 400 ወታደሮችን ወደ የመን በመላክ አጋርነቷን አስመስክራለች።
በቀጣናው ተለዋዋጭነት ምክንያት አገራት ያላቸውን ስልታዊ ግንኙነት እንደገና እንዲመረምሩ አስገድዷል። እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ኦዎል አስተያየት ከሆነ ይህንንም ተከተሎ ሦስት ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። እነሱም በሳኡዲ አረቢያ የሚመራው እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን፣ ግብጽን፣ ባሕሬንን የሚያካትተው ቡድን በጅቡቲ ወታደራዊ ሰፈር ገንብቷል፤ ሁለተኛው የኢራኑ ቡድን ሲሆን፣ ሦስተኛው ኳታርንና ቱርክን ያካተተው ቡድን ነው።
ይሁንና ኢትዮጵያ ከውጪ ፖሊሲዋ በሚመነጨው፣ ጣልቃ ገብነትን በማይፈቅደው እና የአገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ ከአገራት ጋር በምታደርገው መስተጋብር ገለልተኝነቷን አስጠብቃለች። ለዚህ እንደማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው ኢትዮጵያ የኳታርን መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን የሳበችውን ያክል ቱርክ በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ ካፈሰሰችው ስድስት ቢሊየን ዶላር ግማሹን ኢትዮጵያ ላይ ፈሰስ እንድታደርግ ማድረጓ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ከቀጣናው አዳዲሶቹ ተፅዕኖ ፈጠሪ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ይጠቀሳል።
የሳኡዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሼክ ሙሐመድ ቢን ዛይድ ያለፈው ሐምሌ የኢትዮጵያ ጉብኝትን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሦስት ቢሊየን ዶላር ድጋፍና የመዋዕለ ነዋይ ፈሰስ አድርገዋል። ከሳኡዲው ልዑል የኢትዮጵያ ጉብኝት አንድ ወር በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አዴል ቢን ሞሐመድ አል ጁቤር አዲስ አባበ የመጡ ሲሆን የአገራቸውን ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አግባብተዋል። ይህ የሚያሳየውም “ኢትዮጵያ ከባሕረ ሠላጤው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሚዛኑን የጠበቀ” መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ከወር በፊት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይሁንና አንዳንዶች ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት ትርክት በጥርጣሬ ይመለከቱታል። ከእነዚህም መካከል የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር መኮንን ፍሰሐ “የኢትዮጵያ መንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ ግልጽነት ይጎድለዋል” ይላሉ። አክለውም “በመካሔድ ላይ ያለው ኅብረት ሥር ነቀል የውጪ ግንኙነት ለውጥ መኖሩን አመላካች ነው” ይላሉ። “ከባሕረ ሠላጤው አገራት ጋር መወገኗ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል መደበኛ ግንኙነት እንዲፈጠር የተጫወተውን ሚና ማየቱ ብቻ በቂ ነው” የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ።
አወልም በበኩላቸው “ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ገለልተኛ መሆኗ በአፍሪካ ቀንድ ላይ እየታዩ ባሉ ፍላጎቶች መጨመር ተጠቃሚ ብትሆንም አደገኛ ጨዋታ ውስጥ የገባች ይመስለኛል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ “የባሕረ ሠላጤውን አገራት የግብይት ፖለቲካና የአፍሪካውያኑ ሥልጣንን ተገን አድርጎ የተፈጥሮ ሀብትን መመዝበርና በስርቆት መጠመድ ለቀጠናው አለመረጋጋት፣ ለታሪካዊ ተቀናቃኞች አዲስ አሰላለፍ እንዲኖራቸው በማድረጉ ሁኔታው ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ቁጥጥር ውጪ እንዲሆን አድርጎታል” ይላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ የፖሊሲ አቅጣጫ በአስደናቂ ፍጥነት ተለውጧል፤ የኅብረቶቹም መስተጋብሮች ተለዋዋጭ ናቸው፤ ይሁንና እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ተቋማት የአባል አገራቱን ፖሊሲ አቅጣጫ ከማሲያዝና የመንግሥታቸውን ባሕርይ ለማረቅ የሚያደርገው አስተዋጽዖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሰሎሞን ናቸው።
በቀጠናው የባሕረ ሠላጤው አገራት ተሳትፎ መሻሻልና ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ሥምምነት ላይ ቢደረስም እና ኢትዮጵያ እስካሁን የገለልተኝነት አቋሟን ጠብቃ ለመቀጠል የቻለች ቢሆንም ሳኡዲ አረቢያ ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ጋር በቅርቡ ከካናዳ ጋር በገባችበት አተካራ በአስመራና ሞቃዲሾ በፈጠረችው ተፅዕኖ አገራቱ ካናዳን ከማውገዝ አልተቆጠቡም።
የአፍሪካን ቀንድ በቅርበት የሚከታተሉትና ያጠኑት የአሜሪካ መንግሥት አማካሪ ማርቲን ፕላውት የአፍሪካ ቀንድ ደካማነትን ከገንዘብ እጥረት ጋር ያያይዙታል። “ምንም እንኳን የአፍሪካ ቀንድ አገራት የፖለቲካ አቋማቸውን ካላቸው ፍላጎትና በየጊዜው ከሚለዋወጡ ሁኔታዎች ጋር አብሮ ለማስኬድ ቢሞክሩም፣ በግልጽም ሆነ በስውር በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ ተፅዕኖ ሥር ይወድቃሉ” ይላሉ።
በ‹ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን› የታተመው የአሌክስ ደ. ወአል ትንተና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምታካሒዳቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ መስተጋብሮች፣ በገንዘብ ኃይል ሚዛን ላይ መሠረት ያደረጉ ዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ብዙ የምታጣቸው ነገሮች መኖሩን ያስጠነቅቃል። “ፖለቲካዊ መስተጋብሮቹ ከዓለም አቀፍ ገበያውም ሆነ ከደኅንነቱ አንፃር በታላላቆቹ የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያላን፣ በተለይም ከሳኡዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፍላጎት ውጪ አይሆንም” ሲልም ያትታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አውሮፓ ባቀኑበት ወቅት ኢትዮጵያ በምትመሠርታቸው ግንኙነቶች ብሔራዊ ጥቅሟን በምንም መልኩ አሳልፋ እንደማትሰጥ ፍራንክፈርት ላይ መናገራቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በምታካሒደው የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ሁሉንም የወጪና ገቢ ፍሎጎቶቿን ለማርካትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ ባለመወሰን በቅርቡ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶቻና ሶማሊላንድ ጋር በጋራ የወደብ ልማት ትብብር ላይ የ19 በመቶ ድርሻ ስምምነት ተፈራርማለች። ከሱዳንም ጋር እንዲሁ ለተመሳሳይ ዓላማ ውል አስራለች።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት ተጨማሪ ወደቦች ለመጠቀም ያለው ፍላጎት እያደገ የመጣው የአምራች ዘርፉ ፋላጎቶች እንዲሁም የወጪ ንግድ ማደግን ተከትሎ ነው። ስለሆነም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ወደቦችን ዋና አልሚና አስተዳዳሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሆነችበት ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን ማስፋት ካልቻለች በስተቀር ደካማ ተደራዳሪ እንድትሆን ያደርጋታል። በሌላ በኩል ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ኢትዮጵያ ያለባትን ከፍተኛ የውጪ ዕዳ ጫና አፋጣኝ መፍትሔ ካላበጀችለት ውሎ አድሮ የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አጥላው ያሳስባሉ።
በሌላ በኩል ግን የመልከዓ ምድራዊው ፖለቲካ ተንታኙና በአባይ ወንዝ ላይ ጥናት ያካሔዱት አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በዋነኛነት የሚያሳስባቸው እንደወረርሺኝ እየተባዛ በመሔድ ላይ ያለው የአገር ውስጥ ግጭት ጉዳይ ነው። “የኢትዮጵያ መንግሥት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተስፋፉ በሔዱበት ሁኔታ ፍላጎቶቹን ሊያረጋግጥ አይቻለውም” ይላሉ።
የያዕቆብን ስጋት የ‹አሜሪካን ኢንተፕራይዝ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ኤንድ አፍሪካን ሊድ› ለተሰኘ ተቋም ከፍተኛ ተንታኝ ኤምሊ ስቴሌ በሐምሌ 2010 ላይ ባቀረበችው ጽሑፍ ትጋራለች። “የአገር ውስጥና የቀጠናው ግጭቶች ላይ መልክዓ ምድራዊ ውድድር ሲጨመርበት ኢትዮጵያን ወደ አለመረጋጋት ሊወስዳት ይችላል” ነው የምትለው። በተለይ የእጅ አዙር የውጪ ኃይሎች ተሳትፎ መጨመር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በአጠቃላይ ቀጠናው ወደ አለመረጋጋት ሊያመራ ይችላል በማለት የባሕረ ሠላጤው አገሮችና ቱርክ እጃቸውን በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ በማስገባታቸው የደረሰባትን እንደ ምሳሌ በማንሳት ስጋቷን በማስረጃ አስደግፋለች።
በዚህ ሁሉ የማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ያረጀ፣ የተምታታና ግልጽነት የጎደለውን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዋን እያደገ ከመጣው፣ የተለያዩ ኃይሎች በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላቸውን ፍላጎቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ አሰላሳዮችን እና ተመራማሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ተቋማዊ አቅሟን በማሳደግ የውጪ ፖሊሲ መቅረፅ እንዳለባት ምሁራኑ ያሳስባሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here