ሰሞኑን ከሙስና እና ከሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል ከ60 በላይ ሰዎችን በሕግ ጥላ ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ይሁንና ከተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እየተሰራጩ ያሉ ዘገባዎች ከወዲሁ አነጋጋሪ ሆነዋል።
በተለይም በማን እንደተሠራ መረጃ ያልተገለጸበት “ምናባዊው” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም በቴሌቪዥን ጣቢዎች መታየቱ የሕግ ባለሙያዎችንና የጋዜጠኝነት መምህሮች መከራከሪያ ነጥብ ሆኗል።“ካንሰርን በጋራ እንከላከል” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ኅዳር 6/2011 የተሰጠው መግለጫም ሌላው የፍርድ ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድር ይሆናል በሚል ውዝግብ አስነስቷል።
ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ የሕግ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደ አኬልዳማና አዲስ አበባን እንደባግዳድ ያሉ ዘጋቢ ፊልሞች (ዶክመንታሪዎች) መሠራታቸውን የሚስታውሱት የሕግ ባለሙያው አበበ አሳመረ እንዲህ ዓይነቶቹ ዘገባዎች “በፍትሕ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል” ይላሉ። የመንግሥት መግለጫም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ዘገባዎች ከፍረጃ ወይም ውሳኔ ሰጭነት መቆጠብ እንዳለባቸው የሚመክሩት የሕግ ባለሙያው፤ ዳኛውም በመንግሥት እና የመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መረጃዎችን ስለሚመለከት የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ አመልክተዋል።
እንደ አበበ ገለጻ ዘገባዎቹ ቀድመው ተጠርጣሪን ወንጀለኛ የሚሉ ከሆነ ዳኛው ተጠርጣሪውን ነጻ እንኳን ሆኖ ቢያገኘው ነጻ ነህ ለማለት ይፈራል፤ ቀድሞ በመንግሥትና በሕዝቡ ውሳኔ ላይ ከተደረሰ ዳኛውም ከዚህ ጫና ውስጥ ለመውጣት ይቸገራል። ነጻ ነህ ቢለው እንኳን “ዳኛውን ሙስና በልቶ ነው” የሚል ፍረጃ ውስጥ እንደሚያስገባም ያክላሉ። ዳኛው ሕዝቡንና መንግሥትን በመፍራትም እንዲህ ዓይነት መዝገቦችን ላለማየት ቀጠሮ ወደመግፋት አላስፈላጊ ሒደት ውስጥ እንደሚገባም ያነሳሉ።
የሕግ ባለሙያው የዳኛ ውሳኔ እስካልተላለፈ ድረስ የተጠርጣሪዎችን ነጻ ሆኖ የመገመት መብት የሚጋፋ አካሔድ እየተስተዋለ ስለመሆኑም ያነሳሉ። ለዚህም የሚያነሱት የመገናኛ ብዙኃን የቃላት አጠቃቀምና የዐቃቤ ሕግን መግለጫ አተረጓጎም ነው። ዐቃቤ ሕግ “ጠርጥሬ ይዣቸዋለሁ” እያለ መገናኛ ብዙኃኑ ግን ወንጀለኞች፣ ጥፋተኞችና ዘራፊዎች የሚል ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ ይመክራሉ።
በርግጥ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 451 (1) የፍርድ ሒደትን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የተከለከለን ዘገባ ስለመግለጽ “ማንም ሰው በቀጠሮ ወይም በመሰማት ላይ ስላሉ ወይም ውሳኔ ስላላገኙ የዳኝነት ጉዳዮች ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃን፣ ማስታወሻን ፍሬ አሳብን ወይም ዘገባን የገለጸ እንደሆነ፣ እንዲሁም አንቀጽ 457 የፍትሕ ሒደትን ለማዛባት በተንኮል ስለሚገለጽ ወሬ በሚመለከት “… የተሳሰተ ስሜትን በማሳደር በተሳሳተ መንገድ ውሳኔ እንዲሰጥ በማሰብ፣ ተፅዕኖ ለማድረግ በማሰብ ትክክለኛ ያልሆነ ወይም የሚያሳስት ወይም ፍሬ ነገሩን የሚያዛባ ወሬ፣ ማስታወሻ፣ ፍሬ አሳብ፣ ትችት፣ ዘገባ ወይም በራሪ ጽሑፍ በማንኛውም መንገድ የገለጸ ወይም ያሰራጨ እንደሆነ” በሕግ እንደሚጠየቅ ይደነግጋል።
በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብኣዊ መብት ማዕከል የሕግ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂው ሔኖክ አሻግሬ በበኩላቸው ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓትን ተከትሎ የተሰጠ ፍርድ አለ የሚባለው አንድም ፍርድ ቤቶች ከምንም ተፅዕኖ በፀዳ መልኩ በሕግ ብቻ ተመሥርተው አድሎ በሌለበት ሁኔታ ውሳኔ ሲሳልፉ፤ ሁለትም ምልዓተ ሕዝቡ ውሳኔው የተሰጠው ከተፅዕኖ በፀዳና በሕግ ብቻ ነው ብሎ አምኖ ሲቀበለው እንደሆነ ያስረዳሉ።
ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 19ን ጨምሮ ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው የሰብኣዊ መብት ሰነዶች ጥበቃ የሚደረግለት መብት መሆኑን የሚያነሱት ሔኖክ በእነዚህ ውስጥም ሰዎች በፍርድ ሒደት ላይ እስካሉ ድረስ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ ፍርድ ቤት ራስን የመከላከል መብቶች እንዳሉ ያነሳሉ።
ይህ መብት ካልተከበረ የእኩልነት፣የክብርና የመልካም ሥም፣ እንዲሁም የነጻነት መብት ያሉ ሌሎች መብቶችን ለመጣስ በር እንደሚከፍት ያስገነዝባሉ። ሲያልፍም የፍርድ ሒደትን በማስተጓጎል የሰውን በሕይወት የመኖር መብት (አንቀጽ 15) እስከማሳጣትም እንደሚደርስ ያክላሉ። ስለሆነም ማንኛውም አካል ይህን መብት ማቀጨጭ እንደማይችል በመግለጽ የሚዲያ ተቋማት ሐሳብን የመግለጽ መብታቸውን በምንም አግባብ ፍትሐዊ ዳኘነት የማግኘት መብትን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ መፈፀም እንደሌለባቸው ያስረዳሉ።
ሐሳብን የመግለጽ መብት ፍፁማዊ ጥበቃ ያለው መብት ሳይሆን በሕገመንግሥቱና አገሪቱ በተቀበለቻቻው ሥምምነቶች ሊገደብ እንደሚችል የሚጠቅሱት ሔኖክ፤ ሕገ መንግሥቱ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ፍትሐዊ ዳኝነት ከማግኘት መብት ጋር ስለሚኖራቸው ተግባቦትና አፈፀፀም ግልጽ ነገር አለማስቀመጡን ያነሳሉ።
ይሁንና ዓለም ዐቀፍ መርሖዎች መረጃን መሰብሰብና ማሰራጨት ከፍርድ በፊት፣ በፍርድ ሒደትና ከፍርድ በኋላ መከወን እንደሚቻል ሲያስቀምጡ፤ መብቱ ግን ገደብ እንዳለው በግልጽ ማስቀመጣቸውንም ይገልጻሉ። ሔኖክ በዋናነትም ገደቦቹ ሚዲያዎች የተከሳሽን እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን በመጣስና በተከሳሽ ላይ ተፅዕኖ በሚያመጣ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደማይችሉ የሚያሳስቡ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ።
ዐቃቤ ሕግን ጨምሮ ማንኛውም የመንግሥት አካል የተከሳሾችን እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን ማክበርና መግለጫቸውም የፍርድ ሒደቱ በማጣራት ላይ የሚገኝ መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈ ተከሳሾችን እንደጥፋተኛ ከማስቆጠር መቆጠብ እንዳለበትም ያክላሉ። እንደሔኖክ አረዳደድ አሁን ላይ ሕዝቡ ተጠርጣሪዎች እንዲቀጡ መፈለጉን ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይም መረዳት ይቻላል።“በዚህም ዳኞችም እንደሕዝብ አባልነታቸው ተፅዕኖ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።በዚህ መሠረት ዳኞች በመግለጫና ዶክመንታሪዎች ጫና ውስጥ ከወደቁ ውሳኔያቸው እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን ዘንግቶ ሊነሳ ይችላል። በዚህም ያለቅቡልና አሳማኝ ማስረጃ ተከሳሾች ጥፋተኛ ሊባሉ ይችለሉ።” ይህ ከሆነ ደግሞ ነጻና ገለልተኛ ዳኝነት እንደሚጥስ ሔኖክ ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ዳኞች በመግለጫና ዶክመንታሪዎቹ ተፅዕኖ ሥር ሳይወድቁ ተከሳሾች ላይ ጥፋት ባለማግኘታቸው ነጻ ናችሁ ቢሉ ሕዝቡ ቀድሞ ጥፋተኛ ስላላቸው፣ ምልዓተ ሕዝቡ ውሳኔው የተሰጠው ከተፅዕኖ በፀዳና በሕግ ብቻ ነው ብሎ አምኖ ስለማይቀበለው ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ነው ከማለት ይልቅ ፍርድ ቤቱ በጉቦ ሠርቷል ወደሚል ድምዳሜ እንደሚሔድም ያነሳሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ አሰማኸኝ አስረስ በበኩላቸው የዶክመንታሪውን ዓላማ የሚያውቀው የሠራው አካል ቢሆንም፣ ይህ አሠራር ዓለም ዐቀፋዊ እነደሆነ ይገልጻሉ። ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር አንፃር ስህተት ነው፣ ወይም ትክክል ነው ወደሚል መከራከሪያ መግባት እንደማይፈልጉ በመጥቀስ ዶክመንታሪው ተፅዕኖ አሳደረም አላሳደረም የእውነት መረጃን እስከያዘ ድረስ ችግር እንደማይኖረው ያምናሉ። ነገር ግን ዶክመንታሪው “እከሌ ወንጀለኛ ነው” ይበል ማለት እንዳልሆነ በማንሳትም “መረጃን እስከያዘ ድረስ ለማስተላለፍ የፍርድ ውሳኔውን መጠበቅ አይገደድምም” ይላሉ።
ያሉ መረጃዎችን ለሕዝብ ማድረስ እንደሚቻል የሚጠቅሱት አሰማኸኝ ዶክመንታሪው እንዴት ተሠራ የሚለው ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም ከሕዝብ የማወቅ መብት አንፃር መተላለፉ ስህተት እንዳልሆነ ያምናሉ።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮመዩኒኬሽን መምህሩ አፈወርቅ ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው የሕዝብ የማወቅ መብት ገደብ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ዶክመንተሪው በጋዜጠኝነት መርሕ ከታየ ስህተት ነው የሚል አቋም አላቸው። ከመጀመሪያው ዘጋቢ ፊልሙ በሚዲያዎች አለመሠራቱን በመጥቀስ ያዘጋጀው መንግሥት እንደሆነም ነው የሚያምኑት። ዘጋቢ ፊልሙን ሚዲያዎች በምርመራ ሥራ ያላገኙት መሆኑም በራሱ የመረጃ ሚዛናዊነት ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ይገልጻሉ። አፈወርቅ አክለውም ቃለ መጠይቅ የሰጡ ሰዎች ከመረጣው ጀምሮ ያለው የሚዘናዊነት ጥያቄ እንደተጠበቀ፣ ከሳሽ ተከሳሽን ያላካተተ ዘገባ “ሁሉም ሰው እኩል ነው” ከሚለው የሕግ ማዕቀፍ እንደሚወጣም ያነሳሉ።
አፈወርቅ የሰሞኑ ዘጋቢ ፊልምና የሚዲያዎች አቀራረብ የፍርድ ሒደቱን ይጋፋል፣ እውነተኝነቱን ማረጋገጡ የፍርድ ቤት ሥራ ነው፣ ዳኞችንም ጫና ውስጥ ያስገባል ይላሉ። አሰማኸኝ ግን በዚህ አይስማሙም፤ ዳኞች በዶክመንተሪው ተፅዕኖ ሥር ሊገቡ አይችሉም፤ የፍርድ ሒደቱ በማስረጃ እና ክርክር የሚያልቅ በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹን ነጻ ቢሏቸው ዶክመንተሪው ስህተት ነው ማለት አይደልም ሲሉም ይሞግታሉ።
ታዲያ በዚህ ሒደት የመገኛኛ ብዙኃን ሚናና አዘጋገብ ምን መሆን አለበት ለሚለው ጥያቄ የሕግ ባለሙያው አበበ እውነትን መዘገብ እንጂ ከእውነት ያለፈ ነገርን ማንሳት እንደሌለባቸውና መረጃዎችን መተርጎም ተገቢ እንዳልሆነ ይመክራሉ። ስለዚህ ሲያስረዱም ሜቴክ ያለ ጨረታ ከውጭ የ37 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈፀሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢገልጽም ሚዲያዎችና ሕዝቡ ጋር ያለው አረዳድ 37 ቢሊዮን ብር ተዘርፏል የሚል መሆኑን ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል 37 ቢሊዮን ብር ምን ምን ይሠራ ነበር ወደሚል ትንተናም የተሻገሩ ዘገባዎች ማስተዋላቸውን በመጥቀስ ተገቢ አይደለም ይላሉ።
በመንግሥት በኩል ሙስናን እና ሌባን አንድ ዓይነት አድርጎ የመሳል ነገር ስለመኖሩ በመጥቀስም “ሌብነት” እና “ሙስና” በኢትጵያ ሕግ የተለያዩ ናቸው ይላሉ። ‹ሌባን ሌባ ብሎ መጥራት እንጂ ማሽሞንሞን የለብንም› የሚለው የጠቅላይ ሚንስትሩ አነጋገር በመሠረቱ የሕግ ስህተት ያለው በመሆኑ እንደማይቀበሉት የገለጹት አበበ የፖለቲካ ፍርድ ወደ መስጠት ውስጥ መገባት እንደሌለበት፣ ይልቁንም የዳኝት ሒደቱ በነጻነትና ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ የተላቀቀ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።