ሰመጉ በመንግስት የታገደበት ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ እንዲለቀቅ ጠየቀ

0
534

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) እንዳስታወቀው ከዘጠኝ አመት በፊት በኢፌድሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በሕገ ወጥ መንገድ ታግዶብኛል ያለውን 8.7 ሚሊዮን ብር እንዲለቀቅለት ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት ደብዳቤ አስገብቷል፡፡
ሰመጉ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ በፍርድ ቤት በኩል ያደረገው ሙከራም በዳኝነት አካሉ ነጻነት እጦት ምክንያት አለመሳካቱን ገልፆ ገንዘቡ በመታገዱ ከነበሩት 13 ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ዐሥሩን መዝጋቱን እና ሰማንያ በመቶ የሚሆኑ ሰራተኛቹን ለመቀነስ መገደዱን በደብዳቤው አስታውቋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሰመጉ ህልውና ስጋት ውስጥ መግባቱን ጠቅሶ የታገደው ገንዘብ እንዲለቀቅለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው በደብዳቤው ላይ አመላክቷል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ታደሰ ጉዳዩ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡
በሥራ ላይ ባለው የበጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ መሰረት ‹‹የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት›› ከዐሥር በመቶ በላይ የሚሆነውን ገቢያቸውን ከውጪ አገር ምንጮች ማግኘት እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ ሕጉ በቅርቡ በተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካጋሪ ጉባኤ በመሻሻል ላይ የሚገኝ ሲሆን ይሻሻላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ በገቢ ምንጭ እና መጠንን ላይ ያለው ክልከላ ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉም በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወቃል፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሰመጉ ተጠባባቂ ዳሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ አዋጁ እንደሚሻሻል ቢታወቅም ገንዘቡ የታገደው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣልቃ ገብነት መጠየቅ እንዳስፈለጋቸው አስረድተዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here