መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየሴቶች በተለያዩ በሽታዎች የመጠቃት ምጣኔ ከወንዶች 50 በመቶ የላቀ ነው

የሴቶች በተለያዩ በሽታዎች የመጠቃት ምጣኔ ከወንዶች 50 በመቶ የላቀ ነው

የሴቶች በተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች የመጠቃት ምጣኔ ከወንዶች 50 በመቶ የላቀ መሆኑን “ዮንሴ ግሎባል የጤና ማዕከል” በጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ።
ይህም በተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች የመጠቃት ምጣኔ በሴቶች ላይ 75 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን፣ በወንዶች ላይ ግን 25 ነጥብ 5 በመቶ ነው ሲል ማዕከሉ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ከ100 ሺሕ ወሊድ ውስጥ 412 የእናቶች ሞት ይከሰታል ነው ያለው።

ኤች አይቪ ኤድስ በሴቶች ላይ የመከሰት ምጣኔው 1 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ በወንዶች ላይ ግን አንድ በመቶ መሆኑ የሴቶችን በጤና እና በሕይወት የመኖር ሁኔታን የቀነሰ እንዲሆን አድርጎታል ነው የተባለው።
ማዕከሉ ጥናቶችን መሰረት አድርጎ እንደገለጸው፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለግርዛት፣ ለጠለፋና ለኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት እና ሌሎች ችግሮች የተጋለጡ ናቸው ብሏል።

በአፍሪካ ንዑስ ሳህራ (Sub-Saharan Africa) ከሚገኙ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሆነ የጾታ እኩልነት የሚታይባት አገር መሆኗን ጠቅሶ፣ ሴቶች ከወንዶች አንጻር ሲታዩ በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ያነሰ ተጠቃሚዎች ስለመሆናቸው አመላክቷል።
ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 የሚሆኑ 14 ነጥብ 1 በመቶ ሴቶችም ያገቡት በ15 ዓመታቸው ሲሆን፣ 40 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በ18 ዓመታቸው ያገቡ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ይህ ጉዳይ በክልሎች መካከል የተለያየ ቢሆንም በአማራ ክልል የጎላ ነው ተብሏል። ያለዕድሜ ጋብቻና እርግዝና ሴቶች በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስገድዳቸው ስለመሆኑና በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሚሆኑ 13 በመቶ ሴቶች ያለዕድሜያቸው እንደወለዱም ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ዮንሴ ዓለም ዐቀፍ የጤና ማዕከል በኢትዮጵያ ከ22 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት አካል የሆነ ብሔራዊ የፕሮጀክት ትግበራ አካላት አውደ ጥናት ባካሄደበት ወቅት እንደገለጸው፣ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ 14 ሺሕ 452 ቤተሰቦች ላይ በተካሄደ ጥናት 54 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑት የቤተሰብ እቅድ አጠቃቀም ላይ ያላቸው አመለካከት መጥፎ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያለው።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች በኩልም 95 በመቶ የሚሆኑት የወሊድ መከላከያ ከየት ማግኘት እንደሚችሉ የማያውቁ አልያም ስለዘመናዊ የወሊድ መከላከያ ያላቸው እውቀት አናሳ ነው ተብሏል።
ለአብነትም በሶማሌ ክልል ያለው የወሊድ መከላከያ ምጣኔ ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑ ተመላክቷል።

የሴቶች ጤና በድህነት፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የጤና አገልግሎት እንደልብ አለማግኘት የተነሳ በአሉታዊ መንገድ የተቃኘ መሆኑን ማዕከሉ ጠቁሟል።
ዓለም ዐቀፍ በተሠራ ጥናትም በዚህ ወረርሽኝ ወቅት በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሚከናወን የማዋለድ ተግባር በ27 በመቶ ዝቅ ብሏል። የቤተሰብ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ቁጥርም በ27 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የማስወረድ አገልግሎት በ16 በመቶ ዝቅ ስለማለቱ አመላክቷል።

ማዕከሉ አደረግኩት ያለው ጥናት አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልልን ያካተተ ነው ተብሏል። በጥናቱ 48 ወረዳዎች፣ 918 ቀበሌዎችና 14 ሺሕ 452 ቤተሰብ የተካተቱበት መሆኑም ተጠቅሷል።
ዮንሴ ዓለም ዐቀፍ የጤና ማዕከል ተቀማጭነቱን ደቡብ ኮሪያ ባደረገው ዮንሴ ዩንቨርሲቲ የተመሠረተና በዓለም ዐቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራ ተቋም ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች