ምርጫ ቦርድ መስከረም 23 በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ዙሪያ ስብሰባ ጠራ

0
685

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ አካላት ጋር ለመምከር መስከረም 23/2012 ቀጠሮ መያዙን አስታወቀ።

በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔው ዝግጅት፣ ድምፅ አሰጣጥ እና ድኅረ ሕዝበ ውሳኔው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን፣ መወሰድ ያለባቸውን የመፍትሔ ተግባራት እና ኃላፊነቱን የሚወስደውን አካል የሚያሳይ የሕዝበ ውሳኔ ፀጥታ እቅድ ዙሪያ፣ በስብሰባው ተሳታፊ በሆኑት የሕግ አስፈጻሚዎች ተዘጋጅቶ ለመስከረም 23/ 2012 የጋራ ስብሰባ ላይ እንደሚቀርብ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ አስቀድሞ ባወጣው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መርሀ ግብር መሰረት፣ የተለያየ ኀላፊነት ያላቸው የሕግ አስፈጻሚ እና የጸጥታ አካላት እና የቦርዱ የሥራ አመራር አባላት የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም ሰላማዊነት ማረጋገጥ አስመልክቶ መስከረም 07/2012 ውይይት አካሒደዋል።

በውይይቱም የፌደራል ፖሊስ ተወካዮች፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ተወካዮች፣ በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ኀላፊ፣ የሐዋሳ ከተማ ፓሊስ አዛዥ፣ የሲዳማ ዞን ፓሊስ ኀላፊ፣ የክልሉ የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ጽ/ቤት ኀላፊ ተገኝተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ወቅት ቦርዱ ከእለት ተእለት ሰላምና ጸጥታ አጠባበቅ በተለየ የምርጫ ሂደት በራሱ የሚፈልገው የጸጥታ ዝግጅት መኖሩን ገልጾ፣ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ፣ እንዲሁም የድምፅ መስጫ እና የድኅረ ምርጫ ሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ለተሳታፊዎቹ አስገንዝቧል።

ከተለያዩ ቢሮዎች የተወከሉት የጸጥታ አካላትም በነሱ በኩል ያለውን እይታ ያቀረቡ ሲሆን፣ የዞኑ ሰላምና መረጋጋት እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸው፣ በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና በጋራ እና በተናጠል ሊያከናውኗቸው ስለሚገቧቸው ተግባራትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here