ከ 300 በላይ ድርጅቶች ከዲያሰፖራ ትረስት ፈንድ ጋር ለመስራት ጥያቄ አቀረቡ

0
708

የኢትዮጵያ ዲያሰፖራ ትረስት ፈንድ በውጪ ሃገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቀን አንድ ዶላር በሚል መነሻ የሚያሰባስበውን እርዳታ ለመተግበር ባቀረበው ጥሪ መሰረት ከ300 በላይ ድርጅቶች የሥራ ሃሳባቸውን አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን በቀን አንድ ዶላር ለሃገራቸው እንዲያወጡ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ትረስት ፈንዱ ማስተወቁ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ገንዘቡን በተግባር ላይ ለማዋል የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች እንዲቀርቡ በጠየቀው መሰረት ነው ሃሳቦቹ የቀረቡት።

ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ሀገር በቀል የልማት ድርጅቶች፤ የሕዝብ እና የሙያ ማህበራት፤ የክልል እና ኣካባቢያዊ የመንግሥት ተቋማት ምክረ ሃሳባቸውን ካቀረቡት ድርጅቶች ውስጥ ይገኙበታል።

ለትረስት ፈንዱ የገቡት ምክረ ሃሳቦች ብዛት ሊጨምር እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አንገብጋቢ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ በሃገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው ሲል የትረስት ፈንዱ መግለጫ ያትታል።

የምክረ ሃሳብ ምዘና እና የመረጣ ሥራውን ፍትሐዊ እና ግልፅነት የተሞላው ለማድረግ በሚዲያዎች በተደረገ ጥሪ በርካታ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው 30 ባለሙያዎች ተመርጠዋል። ይህም ቡድን ከትረስት ፈንዱ አመራሮች ጋር ተወያይቶ በቀጣይ ኹለት ወራት ድርጅቶችን ለዳይሬክተሮች ቦርድ በማቅረብ ይሁንታ ያገኙትን ምክረ ሃሳቦች በኅዳር ወር 2012 ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here