ሀገር ፍቅር ቴአትር

0
1525

በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ቴአትር ቤቶች መካከል የመጀመርያ የሆነው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመጀመሪያ በ1927 የተቋቋመ ሲሆን በጣልያን ወረራ እና ጦርነት ወቅት የሀገር ፍቅርንና አንድነትን በማቀንቀንና የአርበኝነት ስሜትን በማነሳሳት አገልግሏል። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ድጋሜ የተመሰረተው ማኅበሩ እጅግ በርካታ የጥበብ ሰዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ጸሐፊ ተውኔት እንዲሁም የተለያዩ ተዋንያን አፍርቷል።

ሀገር ፍቅር እንደሥሙ የአገር አንድነት ላይ አተኩሮ የተለያዩ ጥበባዊ ክዋኔዎችን የማቅረብ ዓላማ ነበረው። በተለይም ከጣልያን ወረራ ጋር ተያይዞ ያለው ሲታይ ከጦርቱም ቀደም ብሎ አርበኝነትን በማበረታታትና በማጽናት በኩል የጥበብን ፋይዳ በተግባር ለማሳየት ሀገር ፍቅር ቴአትር ብዙ የሠራ እንደሆነ ይነገርለታል። በወቅቱ ይቀርቡ የነበሩ ጥበባዊ ክዋኔዎች በሽለላና ፉከራ የታጀቡ ናቸው። ግጥሞች፣ ሙዚቃዎች፣ ዝማሬዎችና ትወናዎችም ይህንኑ የሚደግፉ ነበሩ።

ሆኖም ግን በታሰበው ልክ የተሳካለት አልነበረም። ኢትዮጵያ በጣልያን ክንድ ሥር በተያዘችበትና በእንቢ ባይነት አርበኝነት በቀጠለበት ጊዜ፤ ሀገር ፍቅር እንደአጀማመሩ ባይሆንም አገልግሎቱ አልተቋረጠም። በተለይም ጣልያን ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለመግዛት በአንድ በኩል ብሔርን በሌላ በኩል በሃይማኖት ለመበታንና ለማለያየት የሚያደርገውን ጥረት ለመመከትና ማኅበረሰቡ አንድነቱን ጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ በኩል ጥበብን መሣሪያ አድርገው ባለሙያዎቹ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ጣልያን ነገሩን ዘግይቶ የተረዳ ይመስላል። በዚህ ጊዜም የጥበባዊ ክዋኔዎቹን ዋጋ እና እየፈጠሩ ያሉትን ተጽዕኖ በመመልከት የሀገር ፍቅር ማኅበር ባለሙያዎችን ያሳድዳቸው እንዲሁም ያስርና ይገድላቸው ጀመረ። ይህን ፈተና መቋቋም ያልቻለው ሀገር ፍቅር ማኅበር በዚህ ጊዜ ነበር የተበተነው፤ ነገር ግን ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ዳግም ማኅበሩ በእግሩ መቆም ቻለ። በወቅቱም በእግሩ መቆም ብቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅር ማኅበር ስያሜውን ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቀይሮ በደብረ ማርቆስ፣ ከፋ፣ ወላይታ፣ ደሴ እና ባሌ ላይ ቅርንጫፎችን ከፈተ።

በባሕላዊ ሙዚቃ ተወዛዋዥና ገና በወጣትነት ሀገር ፍቅርን የተቀላቀለ ባለሙያ የሆነው ታደለ አያሌው በመጀመሪያ ሲቀጠርም በወር 127 ብር ደመወዝ ይከፈለው ነበር። በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚሠሩ ከሆነ አበል እስከ 13 ብር ይገኛል ይላል። በጊዜው ገንዘብ ከነበረው ዋጋ አንጻር የታደለ ገቢ ትንሽ የሚባል አልነበረም።

አሁን ስልሳዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ታደለ ግን መለስ ብሎ ሲያስታውስ፤ ከችሎታው አንጻር ክፍያው የሚመዛዘን አልነበረም ይላል። “ያኔ ስንሠራ ዓላማችን ብር ሳይሆን አንድነት እና የአገር ፍቅርን በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎች ማስተጋባት ነበር” ብሏል። በእርግጥም ሀገር ፍቅር ቴአትር የተመሠረተበት ዓላማም ይኸው ነበርና።

በሀገር ፍቅር ማኅርና በቴአትር ቤቱ ዛሬ ላይ ሥማቸው አንጋፋ ሆኖ የሚጠራው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ጨምሮ የበርካቶች ሥም በዋናነት ይጠቀሳሉ። ንጋቷ ከልካይ ደግሞ የመጀመሪያ ሴት ተዋናይት በመሆን ወንዶች የሴት ገጸ ባሕሪን ወክለው የሚሠሩበትን ጊዜ ፍጻሜ ያደረገች ተዋናይት ሆና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ታሪክ ተመዝግባለች። ከዛም ባሻገር በሙዚቃው አይጠገቤ የሆኑት ጥላሁን ገሠሠ እና አስቴር አወቀ ሥራቸውን በሀገር ፍቅር ቴአትር መድረክ ጀምረዋል።

አሰለፈች አሽኔ ሀገር ፍቅርን በለጋ ዕድሜዋ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተቀላቀለች ሲሆን ሁለገብ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነች ማለት ይቻላል፤ የባሕላዊ ሙዚቃ ተወዛዋዥ፣ ሙዚቀኛ እና ተዋናይት ናት። ገና በ12 ዓመቷ የተቀላቀለችውን ቤት ለሰላሳ ዓመታት አገልግላለች። በተቀጠረችበት ወቅት መነሻ ደሞዟ 50 ብር የነበረ ሲሆን ይኸውም በወቅቱ ኹለተኛው ትልቁ ደሞዝ ነበር።

የመጀመሪያ የተውኔት ሥራዋ የነበረው “ቆራጥ” የተሰኘ ቴአትር ሲሆን ይህም በአርበኞች ሕይወት ላይ የሚያጠነጥን ታሪክ ነበረው። “በእኔ ጊዜ የምንሠራቸው ቴአትሮች የአገር አንድነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። እኛም እርስ በርስ በመከፋፈል ሳይሆን አንድ ሆነን ነበር ሥራዎቹን የምንሠራው” ያለችው አሰለፈች በድምሩ ከሰማንያ በላይ ቴአትሮች ላይ በትወና ተሳትፋለች።

በደርግ ዘመነ መንግሥት ሀገር ፍቅር ቴአትር ሥራውን የቀጠለ ቢሆንም የጥበባዊ ሥራዎቹ ቃና ሶሻሊስት በሆነ ርዕዮተ ዓለም ተይዞ ነበር። ይህም የሆነው በመንግሥት በኩል ሳንሱር በመኖሩ ምክንያት ነው። በጊዜው እንደማሳያ ይጠቀስ ቢባል የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ተስፋዬ ገሠሠ፤ “እቃው” በተሰኘና በደርግ ፀረ ደርግ ነው ተብሎ በተገመገመው ቴአትሩ ምክንያት ለእስር ተዳርጓል።

ከዚህ ባሻገር ግን የዊልያም ሼክስፒር፣ የሞልቬርና የፍሬድሪክ ሺለር ተውኔቶች በውርስ ትርጉም ተዘጋጀተው ለእይታ ቀርበዋል። ከእነዚህ ቴአትሮች ውጪ ቀጥታ የሬድዮ ስርጭትም ያዘጋጁ ነበር። በኋላ ግን በደርግ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ አካባቢ ቴአትሮች ንግድ ተኮር እየሆኑና የፍቅርና አሳዛኝ ዘውግ ያላቸው ቴአትሮች ለተመልካች ይቀርቡ ነበር።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ እስከ 1992 ድረስ በቴአትር ቤቱ 360 ቴአትሮች ለእይታ ቀርበዋል። መምህር ጫሞ እንደሚናገሩት ከሆነ ደግሞ፤ ከ1992 ጀምሮ በአመራር ድክመት የተነሳ ለእይታ የቀረቡ ቴአትሮችና ጥበባዊ ሥራዎች በአግባቡ ሳይመዘገቡ ቀርተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት 141 ሰዎች ተቀጥረው ይሠራሉ። ከሰኞ ውጪ ባሉት ቀናት ሁሉ ቴአትሮች ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን በየበዓላቱ ደግሞ ሙዚቃዊ ትዕይንቶች ይቀርባሉ። ቴአትር ቤቱ 6 ሺሕ 856 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ላይ ኹለት የቴአትር አዳራሾችን ይዟል። ትንሹ 400 ሰው የሚይዘውና ለሥልጠና እና የተለያዩ ክዋኔዎች የሚከናወንበት ሲሆን ኹለተኛው 800 ሰዎችን መያዝ የሚችለው አዳራሽ ነው።

ቴአትር ቤቱ በተለያየ የመንግሥት ስርዓት የተለያዩ ፈተናዎችን ያለፈ ቢሆንም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የይዞታ ማረጋገጫ አልነበረውም። መምህሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም የነበራቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀገር ፍቅር ከቀደመው መንግሥት ጋር ይሠራ ነበር ብለው ይኮንኑታል። እንደማንኛውም ዓይነት ባለሙያ የኪነ ጥበብ ሰዎችም በየጊዜው ከሚመጣው መንግሥት ጋር በጎውን ይበል እያሉና መጥፎውን እየኮነኑ የመሥራት ኀላፊነት አለባቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቴአትር ቤቱ ይዞታውን ሳያረጋግጥ እንዲቆይ ያደረገው ጉዳዮን ከፍጻሜ ለማድረስ ውስጣዊ ጽናት ማጣት አንዱ ሲሆን ቸልታ ሌላው ችግር ነው” ብለዋል።

መምህሩ ቀጥለው ሲናገሩም ለቴአትር ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ እድሳት የተደረገለት በ2002 ሲሆን፤ ለእድሳት እንዲህ መዘግየቱ ለቴአትር ቤቱና ለታሪካዊ ፋይዳው ጭምር ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የሚባሉ ዘመናዊና ምቹ የሆኑ ቴአትር ቤቶች እየተሠሩ ሲሆን ሀገር ፍቅር በዛ መሰረት እንዲታይ ለማድረግ በአዲስ መልክ ሊታደስ ይገባል ብለዋል።

ይህ ሐሳብ እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም። በቴአትር ቤቱ 84ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አስተዳደር ቴአትር ቤቱ በአዲስ መልክ ለመገንባት እቅድ አቅርበዋል። ይህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀባይነት ማግኘቱና ወጪውም በአስተዳደሩ ይሸፈናል መባሉ መልካም ዜና ሆኗል። ይህ ብቻ አይደለም ሀገር ፍቅር ቴአትር ተጨማሪ የሥራ እቅዶችን ያስገባ ሲሆን በዚህም የቦታ ማስፋፊያ ተጠይቋል። ይህም ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ቴአትር ቤቱ በድምሩ 19 ሺሕ 800 ካሬ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ይህም ወደ ሥነ ጥበብ ማዕከልነት ያሳድገዋል ተብሏል።

ሀገር ፍቅር ከዚህ ባሻገር ሌላው ፈተናው ለጥበብ ሰዎች የሚደረገው ማበረታቻ ማነስ ነው። በዚህ ቴአትር ቤት በአሁኑ ሰዓት የባሕላዊና ዘመናዊ ተወዛዋዥ እንዲሁም ድምፃዊ ጠቅላላ ደሞዝ 2ሺሕ8 እና 2 ሺሕ 514 ብር ነው። በሌላ በኩል ከፍተኛ የሚባለው የደሞዝ ጣሪያ 6 ሺሕ 700 ብር ነው። በሀገር ፍቅር ለ19 ዓመት ያገለገለው ተዋናይ ዮናስ ጌታቸው በበኩሉ፤ ለጥበብ ባለሙያዎች ማበረታቻ አለመደረጉ በቴአትር ቤቶቹ ይዘጋጁ የነበሩ ቴአትሮች ለመቀነሳቸው ምክንያት ነው ይላል።

የሀገር ፍቅር ሰዎች የሚጠብቁት የነበረው መልካም ቀን እየቀረበ ይመስላል። ለ2012 በጀት ዓመት ለቴአትር ቤቱ የተመደበው በጀት ለዚህ አንዱ አመላካች ሊሆንም ይችላል። የከተማ አስተዳደሩ በዚህኛው በጀት ዓመት 13 ሚሊዮን ብር በጀት ለቴአትር ቤቱ የመደበ ሲሆን፤ ይህም በቴአትር ቤቱ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለው እንደሆነ መምህሩ ይናገራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here