የከተማዋ ታክሲዎች ነገር እንዴት ሰነበተ?

0
699

ባሳለፍነው ሳምንት በማኅበራዊ ሚዲያዎች የመነጋገሪያ እንዲያውም ላቅ ብሎም በርካታ እንቅስቃሴዎች እና የድጋፍ ድምጾችም በዋናነት በትዊተር ሲደመጡ ነበር። ጉዳዩ ደግሞ ማክሰኞ፣ መስከረም 6/2012 አዲስ አበባ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ አገልግሎትን በተመለከተ አዲስ መመሪያ ይዞ ብቅ ማለቱ ነበር።

ቢሮ ኀላፊው ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) በመግለጫቸው በኮድ ሦስት የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ቀለማቸውን ሰማያዊ በነጭ በመቀየር ሰሌዳቸውን ወደ ኮድ 1 በማድረግ አገልግሎታቸውን መቀጠል ይችላሉ ካሉ በኋላ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት በተለምዶ ላዳ የሚባሉት ታክሲዎች ደግሞ መደራጀታቸው ግድ እንደሆነ አብስረዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሚታወቀው የ“ራይድ” ባለቤት ሳምራዊት ፍቅሩ በትዊተር ገፃቸው ችግሮች እየተጋረጡባቸው እንደሆነና ለመታገልም ቆርጠው መነሳታቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ “አይ ስታንድ ዊዝ ራይድ” የሚል የድጋፍ እንቅስቃሴ ተከታታይ ቀናትን በትዊተር የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ሲደመጥ ውሏል። በተቃራኒው ደግሞ የላዳ ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ውሳኔው ኹሉንም እኩል የሚያደርግና ውድድሩን በእኩል ሜዳ ላይ የሚያደርግ ነው ሲሉ የከተማዋን ትራንስፖርት ቢሮ ውሳኔ በሙሉ ልብ ድጋፍ አስምተዋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ዝምታን መርጠው አልተቀመጡም ። በትዊተር ገፃቸው ማንም የፈጠራን ሥራ እና የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ አገልግሎትን የማስቆም ፍላጎት እንደሌለው ገልፀው ነገር ግን ኹሉም ነገር ፍትሐዊ እንዲሆንና ነጭ በሰማያዊ ቀብተው ሰሌዳቸው ኮድ 1 የሆኑ የታክሲ ባለቤቶችንም ማካተት መንግሥት ድርሻ መሆኑን ተናግረው ኹሉም ነገር ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ቀደመውን አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ተናግረዋል። ከውዝግቡ በኋላም ሳምራዊት ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ እንደሚቀጥልና አብረዋቸው ለነበሩት የማኅበራዊ ትስስር ደጋፊዎች ምሥጋናን አቅርበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here