‹‹ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሐሳብ የምኞት ዝርዝር ነው›› ኢትዮጵያ

0
430

ባሳለፍነው ሳምንት በግብጽ ካይሮ ከአንድ ዓመት በኋላ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ላይ በተደረገው ድርድር ላይ ግብጽ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ያመጣቸው አዳዲስ ጥያቄዎች የምኞት ዝርዝር እንጂ ሒደቱን የጠበቀ መደራደሪያ እንዳልሆነ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ፣ በግድቡ ላይ ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች በባለሞያ በመደገፍ እና ሦስቱንም አገራት በማሳተፍ ሲደረጉ መቆታቸውን አስታውሰው፣ ከዚህ አካሔድ በወጣ መልኩ ግብጽ ለብቻዋ በመነጠል ያቀረበቸው ጥያቄ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው እና አግባብነት የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ድርድሩን የፖለቲካ መልክ ማስያዝ የሚፈልጉ አካላት ቢኖሩም ኢትዮጵያ ግን ይህ የቴክኒክ ጉዳይ ነው ብላ እንደምታምን እና ቀጣይ ውይይቶችንም በዚሁ መልክ እንደምትመለከት ተናግረዋል። በግድቡ ላይም እስከዛሬ በተደረጉ ውይይቶች ምንም ዓይነት ውጤት እንዳልተገኘ ማስመሰሉ መልካም አይደለም ያሉት ስለሺ፣ ከዚህ በኋላም አላስፈላጊ ግጭቶችን በመቀነስ የታችኛው ተፋሰስ አካላትን በማይጎዳ መልኩ ግድቡ በታሰበለት ወቅት ወደ ሥራ ይገባል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ግድቡ ከሚኖረው 16 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች አምስቱ የውሃ ሙሌቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ይገጠማሉ ሲሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ መጥቀሳቸውን በማውሳት ከአዲስ ማለዳ ላቀረበችላቸው ጥያቄም በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳልተላለፈ ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ በምንም ዓይነት ከ15.8 ጊጋ ዋት በታች የሆነ ኃይል እንደማያመነጭ እና ተርባይኖች ላይም ቅልጥፍናቸውን በተመለከተ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ተናገረዋል። እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ቦርድ እና በሚመለከታቸው ባለሞያዎች ተጠንቶ የሚወሰን እንደሆነም ጠቅሰዋል።

እንደ ስለሺ ገለፀም፣ ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ የነበረውን በግድቡ ላይ የሚደረገውን ውይይት ለመቀጠል በካይሮ በነበረው ስብሰባ ላይ መወሰኑን እና ግብጽ ይዛ በመጣቸው አዲስ ሐሳብ ምላሽ የሚሆን ምክረ ሐሳብ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ባለሞያዎች ተዘጋጅቶ በሱዳን በሚካሄደው ቀጣይ ውይይት ላይ እንደሚቀርብም ተናግረዋል።

ግብጽ በካይሮው ጉባኤ ላይ አዲሱን ሐሳቧን አጀንዳ አድርጋ ለማቅረብ ሞክራለች ያሉት ሚኒስትሩ፣ በኹለቱ ሃገራት ተቃውሞ ግን አጀንዳው ውድቅ እንደተደረገ ተናግረዋል።

ግብጽ የሕዳሴው ግድብ የሚሞላበት ዓመት ከፍ እንዲል፣ የአስዋን ግድብ በመጠን እንዳይጎድል እና በየዓመቱ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው የውሃ መጠንም ከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እንዳይቀንስ የሚል ሐሳቧን በውሃ እና መስኖ ሚኒስትሯ መሐመድ አብደላቲ አማካኝነት በነሐሴ ወር ወደ አዲስ አበባ መላኳ ይታወሳል።

ይህ ኢትዮጵያን ከ 86 በመቶ በላይ ውሃ እና ለም አፈሯን የምታዋጣበት ወንዝ ላይ እንዳታለማ የሚያደርግ ጥያቄ ነው ያሉት ኢንጂነር ሰለሺ፣ ግድቡ ወደ ሥራ ሲገባ ግብጽ ግድቡ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ያቀረበቸው ሐሳብ አግባብ አይደለም ብለዋል። የግብጽ ሐሳብ የሱዳንን የውሃ ድርሻ የሚጎዳ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በመስከረም 13 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሱዳን የሚካሔደው ቀጣይ ስብሰባም የተፈጠሩት ችግሮች ይፈቱበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ሦስቱ ሃገራት በሚያቀርቡት አዲስ ሐሳብ ላይ ተመስረቶ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል ሲሉ ስለሺ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግድቡን ኃይል ለመቀነስ በግብጽ ተስማምተው መጥተዋል በሚል ለተናሳለቸው ጥያቄም ‹‹እንኳን የሃገር መሪ ማንም ኢትዮጵያዊ እንዲህ አያደርግም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች እና በእለት ተእለት ሥራ ላይ ጣልቃ አይገቡም›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here