“ማን የፍቅር ጥያቄ ያቅርብ?” – የወደደ

0
954

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ወንድ ልጅ ለወደዳት የፍቅር ጥያቄ እንዲያቀርብ፤ ሽማግሌ ወደ ሴት ቤት እንዲላክ፣ የጋብቻ ጥያቄንም ወንድ ልጅ ለሴት እንዲያቀርብ ይጠበቃል። ይህ ለዓመታት የተኖረበት ባሕል ነው። ዓለም ከአሁን ይልቅ ቀድሞ የአንድ መንደር ያህል የጠበበችና አንድ የሆነች እንደነበር ማሳያ የሚሆን ይመስል፤ ይህ ስርዓት በዓለም ዐቀፍ ደረጃም የተለመደ ነው። ወንድ ልጅ ነው የወደዳትን ለጓደኝነት መጠየቁ።

ሁሉን ነገር የውድድር ሚዛን ላይ በማስቀመጥ መንፈስ ሳይሆን እንዲሁ ስታስቡት የወደደ ይጠይቅ እንጂ ሴት ትሁን ወንድ ምን ችግር አለው? ብዙ ጊዜ ከሚሰሙ አባባሎች አንዱ ሴት ልጅ ወደ ፍቅር ግንኙነት እንዲሁም ጋብቻ ስትገባ ከምትወደው በላይ የሚወዳትን ማግባት አለባት የሚለው ነው። በእውነቱ ከሆነ በሁለቱም ወገን መዋደድ አስፈላጊ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ነገር ግን ከምትወደው ወንድ ይልቅ የሚወዳት ወንድ የሚመረጥላት እርሷ ተገዢ ሆና ትኖራለች የሚል እሳቤም ስላለ ይመስለኛል።

እንዴት ቢባል፤ ወንድ ልጅ ከምንም ሊገደብ የማይችል ተደርጎ መቆጠሩ እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ይህም የቤቱ የገቢ ምንጭና ገንዘብ አምጪ መሆኑ፣ ቤተሰቡን እንዲመራ መጠበቁ እና ውጪ ስለሚውል ብዙ ያያል፣ ብዙ ይሰማል ተብሎ ስለሚታመን ነው። በአንጻሩ ሴት ልጅ ትዳሯን አክባሪ እንድትሆን ይጠበቅባታል። እናም ምቾት ብታጣ እንኳን አፍጥጦ የሚያያት ማኅበረሰብና ጉዳይ ብዙ በመሆኑ በመጀመሪያ “ይለወጣል” በኋላ ደግሞ “ለልጆቼ ስል!” እያለች ተኮራምታ መኖር እንደማይከብዳት ሁሉም ይስማማል።

ይህ የእኔ እይታ ሆኖ ሁላችን ግን ሳንነጋገር የተግባባንበት ጉዳይ ይመስለኛል። በእርግጥ ይህ በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይ ጫና በመሆኑ አነሳን እንጂ ወንዶችም ጋር ተመሳሳይ ጉዳይ ሊነሳ ይችላል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ከከተማነት ባልደረሱ አካባቢዎች ኹለት ሰዎች ሳይተዋወቁ የሚዳሩበት ጊዜም አለ። ይህም ማኅበረሰቡ ለትዳር ከሚሰጠው ትርጉምና ቤተሰብ ለልጆቹ ኀላፊነት ይሰማኛል ብሎ ከማመን የመነጨ ነው።

አሁን ከተሜነትና የዘመናዊነት እሳቤ በተወሰነ ደረጃ የተስፋፋበት ጊዜ ላይ ነን። ታድያ በዚህ ጊዜ የወደደ የፍቅርም ሆነ የጋብቻ ጥያቄ ቢጠይቅ ምን ችግር አለ ነው ጥያቄው። በእርግጥም የተለመደውም ባሕል የሴትን ክብር የሚነካ አይደለም፤ እንደውም ክብር የሚሰጥ ነው። የፍቅር ጥያቄ የሚቀርብላት እንጂ የማታቀርብ መሆኑን ከንቀት የሚመለከቱ ካሉ ነው ችግሩ።

ነገር ግን ሴት ልጅም ጥያቄ ብታቀርብ ተዓምር የተከሰተ ያህል አዲስ ነገር የተፈጠረ የሚመስለው ብዙ ነው። ለምን? ከማኅበራዊ አኗኗር ሕግ የተጻፈ ልምድ ስላለ፤ ግን ደግሞ መዋደድ ከሕግ በላይ ነው። እናማ! የወደደ ይጠይቃ!
ሊድያ ተስፋዬ
mekdichu1@gmail.com

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here