የባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተባለ

0
883
  • አዳዲስ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችም መጥፋታቸው ተነግሯል

የባህርዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ታካሚዎች ለተጨማሪ ወጪ እንዲዳረጉ በማድረግና በቂ የመድኀኒት አቅርቦት ባለማቅረብ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም የሚል አቤቱታ ከሠራተኞቹ ቀረበበት።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሆስፒታሉ ያሉ ላቦራቶሪዎች ግማሾቹ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፣ ግማሾቹ ደግሞ የት እንደገቡ እንደማይታወቅና ታካሚዎች በዚህ ሳቢያ ለምርመራ ወደ ግል ህክምና ተቋማት እየተላኩ ለለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን አስታውቀዋል።

‹‹ሆስፒታሉ ኦዲት ተደርጎ አያውቅም›› የሚሉት ሠራተኞቹ፣ በርካታ አዳዲስ የህክምና መሣሪያዎች ተገዝተው አገልግሎት ሳይሰጡ ከሆስፒታሉ መሰወራቸውን ተናግረዋል። ታካሚዎች በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው ለተቋሙ ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡም ይስተካከላል ከሚል ባለፈ ለውጥ መምጣት አለመቻሉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር የሰውበላይ ምናለ፣ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው አንዳንድ መሣሪያዎች ለብልሽት በመዳረጋቸው አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውንና አንዳንድ ማሽኖችም አዲስ በመሆናቸው በአስራ አምስት ቀን አንዴ ባለሙያዎችን ከአዲስ አበባ እያስመጡ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ማሽኖች ከሆስፒታሉ መጥፋታቸውን አስመልክቶ ያቀረቡት አቤቱታ ስህተት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር የሰውበላይ፣ ማሽኖቹ ለብልሽት በመዳረጋቸው በተለይ ለእንቅርት መመርመሪያ የሚውለው ማሽን በመበላሸቱ በርካታ ታካሚዎች ሌላ ቦታ ተመርምረው እንዲመጡ በመደረጉ መጉላላታቸውን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት አለበት ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ የመድኀኒት መግዣ እንኳን እየጠፋ ታካሚዎች የግል መድኀኒት ቤት እንዲገዙ ይደረጋል ይላሉ። በርካታ መሟላት ያለባቸው የሆስፒታሉ የላቦራቶሪና ሌሎች መገልገያ መሣሪያዎች መገዛት ባለመቻላቸው ተገልጋዩም ሆነ አገልጋዩ ለችግር ተዳርገዋል። ተቋሙ ኦዲት አይደረግም የሚለው ስህተት መሆኑን ገልጸው፣ በውስጥ ኦዲተሮች በየወሩ ኦዲት እንደሚደርግ አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች ግን የዳይሬክተሩን ሃሳብ በመቃረን ‹‹በቅርብ ጊዜ የተገዙ የላቦራቶሪ እቃዎች እንኳን በአግባቡ እየተጠቀምንባቸው አይደለም›› ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ። የሆስፒታሉ አንዳንድ ኀላፊዎች ከግል ክሊኒኮች ጋር በመመሳጠር ታካሚው ውጪ ተመርምሮ እንዲመጣ እንደሚያደርጉ ያወሳሉ። ይህንን አቤቱታ የሚቃወሙት ዳይሬክተሩ የተቋሙን ስም ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሠራተኞች የሚያቀርቡት ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የክልሉ ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉጌታ ይትባረክ፣ በሆስፒታሉ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች መኖራቸውን ተናግረው፣ ጤና ቢሮው ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ዝርዝር ጉዳዮችን በቦታው ተገኝተን እውነታውን ካረጋገጥን በኋላ የምናሳውቅ ይሆናል ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here