በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭት በ15 ሺሕ ጨመረ

0
936

በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭት ከፍተኛ እድገት በማሳየት በአራት ቀናት ውስጥ የአምስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከባለፈው 2010 ዓመት ጋር ሲነጻጸር በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር በ15 ሺ ጭማሪ ማሳየቱን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ባለፈው አንድ ዓመትም ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ለመያዛቸው እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው በሽታውን ለመከላከል የሚረጭ ኬሚካል እጥረት እና ህብረተሰቡም ወባ እንደጠፋ በማሰብ መደበኛ ጥንቃቄዎችን ያለማድረጉ እንደሆነ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

‹‹ባለው ጥቂት ኬሚካልም በከፍተኛ ደረጃ ችግሩ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ርጭት እያደረግን ነው›› ያሉት የኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታ መርሀ ግብር አማካሪ ፀሐይ ተዋበ፣ እንደ ቋራና ጠገዴ ያሉ ቆላማ ስፍራዎች በርካታ ሰዎች በበሽታው የተያዙባቸው ናቸው ሲሉም አክለዋል። በምሥራቅ አማራ፣ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደርም የበሽታው ስርጭት ጎልቶ መታየቱን አመልክተዋል። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ15 ሺሕ ጭማሪ አሳይቷል። ስርጭቱ በ7 ነጥብ 7 ከመቶ ጨምሯል። በ2010 በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 285 ሺሕ መድረሱን የገለጹት ፀሐይ፣ በ2011 ወደ 3 መቶ ሺሕ ከፍ ማለቱን አስታውቀዋል።

‹‹በባለሙያዎችና በጤና አጠባበቅ ትግበራው ላይ መዘናጋት በመፈጠሩ የግብዓት መቆራረጥ ተከስቷል›› እንደ ፀሐይ ገለፃ ‹‹በየሦስት ዓመቱ አጎበር የሚቀየር ቢሆንም ያልተቀየረላቸው አካባቢዎች መገኘታቸው አሁን ለጨመረው የወባ በሽታ ምክንያት ሆኗል።››

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭት ጎልቶ ከሚታይባቸው ሁለት ወቅቶች መካከል ዋናው የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከመስከረም እስከ ኅዳር መገባደጃ ያለው ሲሆን፣ የበልግ ዝናብን ተከትሎ አነስተኛ የወባ ስርጭት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ አጋማሽ ባሉት ወራት ውስጥ ይከሰታል።

ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች የተካሔደው የኬሚካል ርጭት 40 ከመቶ ብቻ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል በሽታው በሚበዛባቸው ዘጠኝ ቆላማ ወረዳዎች ላይ 110 ባለሙያዎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል። በተለይ የቀን ሠራተኞች በቆላማ የልማት ቦታዎች በሚጓዙበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክር እንደሚሰጥም ነው የገለጹት።

የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በመላው አገሪቱ በዓመት አንድ ጊዜ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ይካሄዳል። ከሰኔ – ነሐሴ ባሉት ጊዜያት የሚካሔደው ርጭትም ከመስከረም – ታኅሳስ ያለውን ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚታይበት ጊዜን ለማለፍ ይረዳል። ነገር ግን ኬሚካሉን በማምረት አቅም ውስንነት ምክንያት በበቂ መጠን ሊሰራጭ አለመቻሉን የገለፀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ይህንን ችግር ለመፍታት እየሠራሁ ነው ብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here