ፍርድ ቤቱ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ ላይ እገዳ አስተላለፈ

0
948

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የኤ.ቢ.ኤች ሰርቪስን ስም የሚያጠፉ እና ማህበሩን ኪሳራ ላይ የሚጥሉ ሀሳቦችን እንዳያስተላልፍ የእገዳ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ኤ.ቢ.ኤች ነሐሴ 23/2011 በመሠረተው ክስ ኤጀንሲው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን በማሰራጨት የድርጅቱን መልካም ስም እና ዝና የማጥፋት ተግባር እየፈፀመብኝ ነው በማለት የኤጀንሲው የሥራ ኃለፊዎች 174 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ በማድረሳቸው ካሳ እንዲከፈለውም ድርጅቱ ጠይቋል።

ኤጀንሲው ባቀረበው መልስ፣ ከሳሽ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሠራ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑን ገልጾ የትምህርት ጥራት መለኪያዎቹ ተገምግመው የማያውቁ በመሆናቸውም የተባለውን መግለጫ ለመስጠት ምክንያት እንደሆነ ተከራክሯል።

በተያዘው የትምህርት ዓመትም የትብብር ትምህርት እንዳይሰጥ በአዋጅ ተከልክሎ ሳለ ኤ.ቢ.ኤች ግን ተማሪዎችን ለመቀበል በመገናኛ ብዙኀን ማስታወቂያ ማስነገሩን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ኤጀንሲው፣ ከሳሽ ፈቃድ ያለው መስሎት ህብረተሰቡ እንዳይታለል በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱንም ኤጀንሲው በእግዱ ላይ ያቀረበው መልስ ያስረዳል።

ከኤጀንሲው ባሻገርም ክስ የተመሰረተባቸው አምስት የሥራ ኀላፊዎች በበኩላቸው፣ በኤጀንሲው ባላቸው የተለያየ የሥራ ግዴታቸውን መወጣታቸው ሊያስከስሳቸው እንደማይገባ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ተከራክረዋል። በመግለጫው ያስተላለፍነው መልዕክትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተባለውን ሁከት የማይፈጥር እና እውነቱን ብቻ የሚገልፅ በመሆኑ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ኤጀንሲው የትምህርት ጥራትን በተመለከተ የመከታተል፤ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን ያለው መንግሥታዊ ተቋም ከመሆኑ አንፃር በ2012 በትብብር የሚሰጥ መረሃ ግብር አለመኖሩን እና ተማሪዎች እንዳይመዘገቡ መናገሩ አግባብነት ያለው ተግባር በመሆኑ ክሱ ተቀባይነት የለውም በሏል።

ኤ.ቢ ኤች ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተገባው ውል ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ለሚሰጠው ትምህርት የመማሪያ ክፍሎችን፣ ቢሮዎችን፣ የቤተ መጽሐፍት፣ የኮምፕዩተር ላቦራቶሪ፣ ፋይናንስ አስተዳደር እና መሰል ተያያዥ ድጋፎችን በማቅረብ እንደሆነ ጠቅሶ ተከራክሯል። ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የመመልመል፣ አስተማሪ ማቅረብ እና የትምህርት ጥራትን የመከታተል ሥራን ሲሠራ እንደነበር ተገልጿል።

ፍርድ ቤቱም ኤጀንሲው ኤ.ቢ ኤችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ውል ወይም የአስተዳደር ትስስር ባለመኖሩ ተከሳሾች ከሳሽን የሚቆጣጠሩበት የሕግ አግባብ የለም ሲል ጭብጡን ይመረምራል። የከሳሽ የንግድ ፈቃድም ከኤጀንሲው ያልተገኘ እንደሆነ የሚያትተው ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው አገልግሎትም የማስተማር ሳይሆን ሌሎች አገልግሎቶች በመሆኑ ቀጥታና ግንኙነት በሌለበት የከሳሽን ስምና ዝና መንካት አይችሉም ሲል ችሎቱ በይኗል።

‹‹እንደዚህ ዓይነት ሐሳቦችና ንግግሮች የከሳሽን መልካም ስም እና ወደፊት ሊሠሩ ለሚችሉት ሥራም ጉዳት በሚያደርስ እና ጥርጣሬ በሚፈጥር መልኩ መገለፁ ከሳሽ በፍርድ ቤት ተከሶ ጥፋተኝነቱ ባልተገለፀበት ወይም በቂ ጥናት ባልተደረገበት ሁኔታ መሆኑ አግባብነት የለውም›› ሲል ብይኑ ያስረዳል።

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘም ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲን መጠየቅ ነበረበት ያለው ችሎቱ፣ ተከሳሾች የከሳሸን ስም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በማያያዝ በሚዲያዎች ማንሳቱ የከሳሽን ሥራ የሚጎዳ በመሆኑ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ከመስከረም 2 ጀምሮ ታግዶ እንዲቆይ በዳኛ አብዲሳ ዳሹራ የተመራው ችሎት በይኗል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here