መነሻ ገጽዜናትንታኔኢትዮጵያ እና ሱዳን ከየት ወዴት?

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከየት ወዴት?

በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ሱዳን አያሌ ዘመናትን ያስቆጠረ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

ሰፊ ድንበር የሚጋሩት ኹለቱ አገራት፣ በቋንቋ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ ልውውጥ፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በኪነጥበብ ሥራዎች ከፍ ያለ መስተጋብር እንዳላቸው ነው የሚወሳው። ኢትዮጵያና ሱዳን በዚህ መልኩ ብሔራዊ ጥቅማቸውን አስጠብቀው በትብብር ይዝለቁ እንጂ፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተካረረ የመጣ ልዩነትም አላቸው። ከዚህ ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠር የድንበር ውዝግብ ዋነኛ ችግር ሆኖ ይታያል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ደቻሳ አበበ (ተባባሪ ፕ/ር)፣ የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት በታሪክ ሲታወስ ከቅኝ ግዛት በፊት ያለው ከእንግሊዝና አልፎ አልፎ ከግብፅ ጋር ነው የሚሆነው ይላሉ። በተረፈ ሱዳን ሉዓላዊ የራሷ መንግሥት ኖሯት ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ግንኙነት የለም ነው የሚሉት።

ከቅኝ ግዛት ከወጣችና የራሷን ሥርዓተ መንግሥት መሥርታ መኖር ከጀመረች ወዲህ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግኙነት በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን አንዱ የአንዱን ችግር በመለጠጥና አንዱ የሌላኛውን ተቃዋሚ በመደገፍ የቆዬ ነው ብለዋል።
ኹለቱ አገራት ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ የቤት ሥራ ሲሰጣጡ ነው የኖሩት የሚሉት መምህሩ፣ ለዲፕሎማሲ ሲባል አይነገርም እንጂ ግንኙነታቸው ውስጥ ብዙ የሻከሩ ጉዳዮች ነበሩ ባይ ናቸው።

በተለይ ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያለው ድንበር የማካለል ሂደቱ በብዙ የአፍሪካ አገራት ችግር አለበት። የቅኝ ግዛት ውርስም ስለሆነ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከልም ይህ ችግር ያለ ነው። በዚህም ለዲፕሎማሲ ላይ ላዩን ወንድማማቾች ይባባሉ እንጂ ውስጥ ውስጡን ግን ብዙ ችግሮች አሉ ነው ያሉት።

በርካታ የአፍሪካ ድንበሮች አንድ ዓይነት ሕዝብን ለኹለት የከፈሉ ስለሆነ፣ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ለማድረግ ሲያስቸግር ይስተዋላል ካሉ በኋላ፣ በዚህም ምክንያት በመንግሥት ደረጃ ባይሆንም ቡድኖች በጥቅምና በሌሎች ምክንያቶች ይጋጫሉ ሲሉ ተደምጠዋል።
ታሪክ እንደሚያስረዳ፣ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት (እኤአ 1902) ሱዳንን በቅኝ ግዛት ከምታስተዳድረው እንግሊዝ ጋር ኢትዮጵያ አንድ ስምምነት ተፈራርማለች።

በስምምነቱ አንቀፅ ኹለት ላይ ‹‹ኹለቱ አገራት ድንበር ሲካለሉ ወኪሎቻቸው ሊገኙ ይገባል›› የሚል ቢሆንም፣ ነገር ግን ሱዳን ያለኢትዮጵያ እውቅና ስምምነቱ ከተደረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ በጎንደር አካባቢ የሚገኘውን ድንበር እና እ.ኤ.አ. በ1909 ደግሞ በጋምቤላ በኩል ያለው ድንበር በእንግሊዝ ብቻ እንዲካለል ተደርጓል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ውዝግቦች እየተበራከቱ መቀጠላቸው ይነሳል።

በኢትዮጵያ ገበሬዎች ሲታረስ የኖረው አል-ፋሽጋ ግዛት
ሱዳን ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ወረራ ማድረጓ ይገለጻል።

ቆየት ብሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ ‹‹ትኩረታችንን ወደ ሰሜኑ ጦርነት ስናደርግ ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጠው ድረስ የምናከብረውን ስምምነት በመጣስ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ አድርጋለች›› ሲሉ ተናግረው ነበር።

አክለውም፣ ሱዳን በወረራ በያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች የሕዝብ ስብጥርን ለመቀየር እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፣ ሆኖም ግን የተወሰደው የኢትዮጵያ ግዛት ‹‹በየትኛውም መመዘኛ›› ይመለሳል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሱዳን በበኩሏ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ጠንከር ባለ መግለጫ አጣጥላዋለች። ይህም ኢትዮጵያ ከ120 ዓመት በፊት በኹለቱ አገራት መካከል የተደረገውን የድንበር ስምምነት እውቅና የነፈገ ነው ስትል ገልጻለች።

ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር ምላሽ ይሆን ዘንድም፣ ሌትናንት ጄኔራል አብዱል-ፋታህ አል-ቡርኻን በኢትዮጵያ ግዛት ላይ የሰፈረውን የሱዳን ጦር የጎበኙ ሲሆን፣ ሱዳን የፀጥታ ኃይሏን በድንበር አቅራቢያ ማሰማራቷን በግዛቷ ላይ የምታደርገውን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እና ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያለውን ድንበሯን የመቆጣጠር ዋና ዓላማ ነው ስትል እወቁልኝ ብላለች።

በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ወቅት እስከ አሁን ሱዳን ወታደሮቿን በአል-ፋሻጋ የኢትዮጵያ ግዛት አካባቢ አሰማርታ ስለመቆየቷ ይነገራል።
ባለፈው መስከረም ወር ሌተናንት ጄኔራል አብዱል-ፋታህ አል-ቡርኻን ጦራቸው በዚሁ አልፋሻጋ ግዛት አካባቢ በሚገኝ ኦም ባራከት በሚባል ቦታ የኢትዮጵያን ኃይሎች ወረራ መቀልበሱን አስታውቀው ነበር።
በአሁኑ ወቅትም ሱዳን በሰሜን ምዕራብ በኩል አል-ፋሽጋን ጨምሮ 70 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኢትዮጵያን ግዛት በኃይል መያዟን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ታላቁ ህዳሴ ግድብና ሱዳን
ሱደን ኢትዮጵያን የጎሪጥ ማየት የጀመረችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሊገነባ መሆኑን ካወቀች ጀምሮ ነው የሚሉ አሉ።

ሆኖም የግድቡ መጀመሪያ ግንባታ ሰሞን የነበራት አቋም ያን ያህል የተለየ ያልነበረ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን አቋሟን ከመቀያየር ጀምሮ በግድቡ ላይ አሉታዊ ጫና ለመፍጠር በተለይ ደግሞ ከግብፅ የሚሰጣትን የኹለቱን አገራት ግንኙነት የሚያበላሽ የቤት ሥራ ለማስፈጸም ደፋ ቀና እንደምትል ይገለጻል።

በዚህ ወር መጀመሪያም ማሻሻያ የተደረገለት የህዳሴ ግድቡን የሚከታተል ከፍተኛ ኮሚቴ ስብሰባ ማካሄዱን የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል ‹‹ሱና (suna)›› ገልጿል። ይህ ኮሚቴም ተግባሩንና የሥራ ዘዴውን ከገመገመ በኋላ፣ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሱዳንን አቋምና ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅሟን በሚደግፍ መልኩ መከታተል አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጧል ነው የተባለው።

በግብፅ ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው ጋዜጣ (Al-Ahram) ከሰሞኑ ይዞት በወጣው ‹‹ሌላኛው የግድቡ ጉዳት›› በሚል ጽሑፍ እንዲሁ፣ ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ በመጭው ክረምት የምታደርገውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደማይቀበሉት አትቷል።
ለቀጠለው እልህ አስጨራሽ ጉዞ ማሳያ፣ ኢትዮጵያ ከነሐሴ እስከ መስከረም ወር ድረስ ሊካሄድ የታቀደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደማይዘገይ ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች ይላል ጋዜጣው።
ይህ በግብፅም ሆነ በሱዳን የህልውና ስጋት ሆኖ የሚታየው አሳሳቢ ጉዳይ በሚያሳዝን ሁኔታ በኢትዮጵያ ዘንድ የተለመደ ሆኗልም ሲል ይገልጻል።

- ይከተሉን -Social Media

ዘገባው እንደውም የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ለግብፅና ሱዳን ብቻ ሳይሆን በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ሲያደርጉ ለነበሩ ቀጠናዊና ዓለም ዐቀፋዊ አካላት በሙሉ ጥረታቸው ኹሉ ከንቱ እና አላስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል ነው ያለው።
ይህም የሥራ አስኪያጁ አስተያየት ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለመፍታት በዓለም ዐቀፍና በአፍሪካ አሸማጋዮች እየተካሄደ ያለውን ጥረት ለማዳከም ያላትን መጥፎ ዓላማና ጥረት በድጋሜ አጋልጧል። በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ የፍትሃዊ ተባባሪነት የመጫን ፍላጎት እንዳላትም አስመስክሯል። ሆኖም ግብፅ ይህን ኹሉ አካሄድ በቀላሉ አትቀበለውም ሲል ዘገባው አመላክቷል።

ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌቱ እ.ኤ.አ 2015 የተደረሰውን ስምምነት ያላከበረ ከመሆኑም በላይ፣ ሌላ የውሃ አማራጭ የሌላትን ግብጽን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል ገልጾ፣ ሱዳን በበኩሏ ግድቡ አፍንጫዋ ስር የሚገነባ በመሆኑ ግድቡ ላይ በማንኛውም ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል አደጋ ጠራርጎ እንዳይወስዳት ዋስትና ሊሰጣት ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ሰላምን ማስፈን ያቃተው ስለሆነም ግድቡን ለፖለቲካዊ ድጋፍ ማግኛ ይጠቀምበታል ያለው ይህ ጋዜጣ፣ በሩስያና ዩክሬን ያለውን ጦርነት ተንተርሶ ዓለም ዐቀፋዊ ሁኔታውን በማጤንና ወቅቱን እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅማ ኢትዮጵያ ሦስተኛ ዙር ሙሌቱን በተናጠል ለማከናወን አደገኛውን እንቅስቃሴ ጀምራለች ሲል አትቷል።

በተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ድርጊቶችና በዜጎቿ ነውጥ አዘል ሰልፎች የምትታወሰዋ ሱዳን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግብፅ ጋር አዲስ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ አካሄድ እያደረገች ነው ብለው የሚናገሩ አሉ። ይህን ከውሃ ፍላጎቷ ጋር አያይዘው የአባይን ወንዝ እንደምክንያት ያነሱታል።

በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርት ኔቪኔ ሞሳድ (ፕ/ር) በቅርቡ በሱዳን የነበራቸውን የቀናት ቆይታ አስመልክቶ ‹‹ሱዳን ከግብጽ የምትፈልገው ምንድን ነው? ግብፅስ ምን ልታደርግላት ትችላለች?›› የሚል ጹሑፍ አቅርበዋል።
በዚህም ሱዳን የመሠረተ ልማት፣ የዕውቀት እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንደምትሻ ወስደው፣ ግብፅ ለሱዳን የምታቀርበውን የኃይል አቅርቦት ማሳደግ፣ አገራቱን በየብስና ውሃ ትራንስፖርት ማገናኘት፣ በጋራ የግብርና ሥራዎችን ማልማት ወደፊት ልናከናውነው ዕቅድ የያዝንለት ነው ብለዋል።

አሁን ላይ የኹለቱ አገራት ግንኙነት መልካም እንደሆነ አንስተውም ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር ግብፅ ከጎኗ መሆኗን አመላክተዋል። በሚዲያና ፖለቲካ ዘርፍ የሚያስፈልጋትን የሰው ኃይል ተቀብላ ለማሠልጠንም ግብፅ ፈቃደኛ እንደሆነች ነው የገለጹት።
ፕሮፌሰሯ በመጨረሻም፣ ተከታታይ የልብ ለልብ ግንኙነታችን አዲስ አድማስ ከፍቷል፣ መሠረትም ጥሏል። የናይልን የበላይነትም (dominion of the Nile) እንደገና አረጋግጧል ነው ያሉት።

ይህም በዓባይ ወንዝ ከእኔ ሌላ ተጠቃሚ የለም የምትለዋ ግብፅ፣ የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ግንኙነት በጥቁር ቀለም ለመቀባት እና ኢትዮጵያ ላይ ስትፈጽመው ለምትኖረው ሴራ ማሳያ ተድርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ይጠቀሳል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ በየትኛውም ሁኔታ ሊቆም እንደማይችልና የህዳሴ ግድቡ በተለይ ለሱዳን የተለየ ጥቅም አለው ትላለች። ግብፅ እና ሱዳን በርካሽ ዋጋ ኃይል መጠቀም ይችላሉ። የሚያዋጣንም በናይል ወንዝ ላይ አብረን ማደግ ነው። መናቆሩ አይጠቅም፣ በተፋሰሱ በጋራ መጠቀም እንችላለን የሚለው የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።

- ይከተሉን -Social Media

በ2015 በሱዳን መዲና ካርቱም የተደረሰው የሦስትዮሽ ስምምነትም፣ የግድቡ ግንባታ እንዲቆም የተፈረመ አይደለም። ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በመጭው ክረምት ጊዜውን ጠብቆ ይከናወናል ስትል አሳውቃለች።

ሕወሓትና ሱዳን
ሕዝብ ለሕዝብ ያለው ባህላዊና ማኅበራዊ ትስስር እንዳለ ሆኖ፣ በመንግሥታቱ በኩል ግን ከውጭ ሲታይ የመካካብ ሁኔታ ቢኖረውም እርስ በእርስ በመጠራጠር እንዲሁም፣ አንዱ የሌላውን ተቃዋሚ በማስጠለልና በመደገፍ የተሞላ እንደሆነ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ደቻሳ ጠቁመዋል።

አፄ ኃይለሥላሴም በዘመነ መንግሥታቸው ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሱዳን መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች እንዲፈጠሩ አድርገው ሲደግፉ እንደነበር አንስተው፣ ሱዳንም በበኩሏ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ ላይ ቤንዚን ስትጨምር ነበር ሲሉ ማሳያ ሰጥተዋል። ይህን ዓይነቱ እርስ በእርስ መጠራጠርና የቤት ሥራ እየተሰጣጡ መኖር የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መገለጫ ነው ብለውታል።

የደርግን አገዛዝ በመቃወም የተመሠረተው ሕወሓትም ገና ከምሥረታው ማግስት ጀምሮ ሱዳንን ለወታደራዊ ሥልጠና፣ ለመሸሸጊያ፣ ለወታደራዊና ሰብዓዊ ቁሳቁስ አቅርቦት ሲጠቀምባት መኖሩ ይታወቃል።
በኋላም ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ አስተዳደር እንዲሁ ከሱዳን ጋር መልካም በሚባል ግንኙነት ዘመኑን እንደቋጨ ነው የሚታወቀው።

ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በፈጠረው ልዩነት በተነሳው ጦርነትም በርካታ ታጣቂዎቹ ሱዳን የሚገኙ ሲሆን፣ ሱዳንም ለዚሁ ቡድን ወታደራዊና ሌሎች ድጋፎችን ታደርጋለች በሚል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ክፉኛ ትወቀሳለች።
የሰሜኑ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ሱዳን የፌዴራል መንግሥቱንና ሕወሓትን ላሸማግል ማለቷን ተከትሎ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ሱዳን መንግሥትን እና ሕወሓትን ለማደራደር ተዓማኒነት ይጎድላታል ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው። በዚህም ካርቱም በትግራይ ጉዳይ ለማደራደር ያደረገችው ጥረት በአዲስ አበባ ውድቅ በመደረጉ የኢትዮጵያ አምባሳደሯን ጠርታ ነበር።

አሁንም ድረስ ሽብርተኛ የተባለው የሕወሓት ቡድን ለዳግም ጦርነት ለሚያደርገው ዝግጅት ሱዳን የቡድኑን ተዋጊዎች በማስጠለል እንቅስቃሴውን በመደገፍ ተባባሪው እንደሆነች ይነገራል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁ በቅርብ የፓርላማ ንግግራቸው፣ ሱዳን ለሕወሓት መሠረት መሆኗ ኢትዮጵያን እንደ መውጋት የሚቆጠር ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የተወረረውን መሬት ለማስመለስ መፍትሄው ምንድን ነው?
የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ደቻሳ አበበ፣ በኹለት አገራት መካከል ድንበር ለመካለል ሦስት ደረጃዎች አሉ ይላሉ። የመጀመሪያው ኹለቱም ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መነጋገር ሲሆን፣ ቀጣዩ የተስማሙበትን ካርታ ላይ ማስፈር ነው። የመጨረሻው መሬቱ ላይ በአካል ተገኝቶ ግልፅ ምልክት በማድረግ መካለል ነው በማለት አስረድተዋል። ሆኖም በወቅቱ (እኤአ 1902) አፄ ምኒልክ ከሱዳን ቅኝ ገዥ እንግሊዝ ጋር ድንበር ሲካለሉ ይህን ሂደት በጠበቀ መልኩ ስለመደረጉ እርግጠኛ አይደለሁም ነው ያሉት።

በጣም ብዙ የማይታወቁና የተዘለሉ ጉዳዮች ነበሩ። አፄ ምኒልክ ራሳቸው ብዙ ነገር እንደተሸወዱ ነው የሚታሰበው። በሱዳን በኩል የነበሩት የእንግሊዝ ሰዎች የካርታ ዕውቀት የነበራቸው ባለሙያዎችን ይዘው ነበር ይሠሩ የነበረው። ይህም ወረቀት ላይ ያለውና መሬት ላይ ያለው ነገር ኹሉ በማይመሳሰል ኹኔታ ስምምነቱ እንደተደረገ የሚናገሩ ባለሙያዎችን እሰማለሁ ሲሉ ገልጸዋል። ስለዚህ በካርታ ተካለዋል ተብሎ በታሪክ ተፅፎ እናነባለን እንጂ ሂደቱን የጠበቀ የድንበር መካለል በተግባር ስለመደረጉ አላውቅም ብለዋል።
ሱዳን ወረራዋን በማስፋት ከያዘችው 70 ኪሎሜትር የሚደርስ መሬት ተጨማሪ ለመያዝ ዕቅድ እንዳላት ኹሉ እየተነገረ ይገኛል። በርካታ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችም ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ይሰማል።
ሆኖም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተደጋጋሚ የሚገለጸው ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከድንበር ያለፈ በብዙ የተሳሰሩ እና ችግሮቻቸውን በሰላም የሚፈቱ እንደሆነ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

በሱዳን ድንበር አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ይገኙ የነበረ ሲሆን፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩ አብዛኛዎቹ ወደ መተማ ከተማ እንደገቡ ቀደም ተብሎ ተገልጿል። ሁኔታዎች ምቹ ባለመሆናቸውም ከሱዳን በቀን በአማካይ 1 ሺሕ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን እንደሚመለሱ በዚህ ወር መጀመሪያ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታውቋል።

ሱዳን የኹለቱ አገራት የጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ሥራ በአስቸኳይ እንዲጀምር እና በጉዳዩ ላይ በትኩረት እንዲሠራ ከመጠየቋ በቀር አሁንም በወረራ የያዘችው ግዛት ሕጋዊ ግዛቷ እንደሆነ ትቆጥረዋለች።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በ2013 መጨረሻ ወቅት ሱዳን ከኋላ በስውር የሚገፏትን አጀንዳ ይዛ እንደጋሪ ፈረስ አትምጣ። እናስታርቃለን የሚሉ አገራትም ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት እንድትመልስ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ተናግረው ነበር።
ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ከዚህ ድርጊቷ እንድትታቀብ ብሎም ኹለቱም አገራት ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማሳሰብ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።

ለአብነትም ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን በኹለቱ አገራት መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ትፈታ ዘንድ የአፍሪካ አገራት ሱዳንን በመምከር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
መንግሥት የትኛውም ግጭት የኹለቱን አገራት ደኅንነት የሚጎዳና ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል መሆኑን ሱዳን እንድትገነዘበው ጠይቆም፣ በሱዳን መንግሥት ወታደራዊ ክንፍ እየተበረታታ ያለው ግጭት በሱዳን ሕዝብ ኪሳራ፣ የሦስተኛ ወገንን ፍላጎት የሚያስፈጽም ነው ብሎታል። የኢትዮጵያ መንግሥት አክሎም የድንበር ጥያቄው ሊስተናገድ የሚችልበት በቂ መንገዶች ቢኖሩም፣ የሱዳን ሠራዊት ግን ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል ነበር ያለው።

ሆኖም ሱዳን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ከዓመት በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማፈናቀል የያዘችው ቦታ በብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ እንደተደፈረ ይቆጠራል የሚል አቋም አላቸው።
በድንበር አቅራቢያ ያሉ በርካታ ዜጎች ክፉኛ እንደተጎዱ በመግለጽም፣ መንግሥት ሁሌ ሱዳንን ከማባበል ወጣ ብሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስከብር በርካቶች ያሳስባሉ።

ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበትን የአል-ፋሽጋ አካባቢን የተቆጣጠረችው ጥቅምት 24/2013 በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል መሰማራቱን ተከትሎ ነው።

የመካረሩ ተፅዕኖ
ኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነታቸው እየተካረረ በሄደ ቁጥር ኹለቱንም አገራት የሚጎዳ መዘዝ እንዳለው ይነገራል። በመካከላቸው ያለው የድንበር ውዝግብም በቀላሉ ይፈታል ብሎ ማሰብ ቀላል ባለመሆኑ፣ ረዥም ዘመን ሊቀጥል እንደሚችል ብዙዎች ይገልጻሉ።
መምህርና ተመራማሪ ደቻሳ እንዲሁ፣ በኹለቱ አገራት መካከል ያለው ግጭት እዚያው ድንበር አካባቢ ባለ መቆራቆስና ንብረት ውድመት ብቻ ተወስኖ አይቀርም የሚል እምነት አላቸው። ውስጣቸው ያለውን ቁስል የማስፋት እጀ ረዥም ጉዞ ሊሄዱ ይችላሉ ነው የሚሉት።
በአንጻሩ የአውሮፓ አገራት ድንበራቸውን በጋራ በማልማት ዜጎቻቸውን በኢኮኖሚ እና በባህል በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጎለብቱ ይነገርላቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች