ጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ አንበሴ የወጣቱን የፍራንኮ-ርዋንዳዊውን የጋይል ፋይ ግለ ታሪክ [Autobiography] መጽሐፍ ‹Petit Pays›ን የፈረንሳይ ቋንቋ እውቀቷን በመጠቀም ‹ትንሿ ሀገር› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉማ ለአንባብያን ካደረሰች ከራረመች። መጽሐፉ በሩዋንዳ የነበረውን አሰቃቂ የእርስ በእርስ መጠፋፋት ያወሳል። ‹‹ሀገር ብታንስም ይሄን መከራ መቀበል የለባትም። የእኛ ትልቅ ሀገር ነውና ትልቅ ጠላት ገጥሞታል።›› ሲሉ በድሉ አበበ ይህን መጽሐፍ የቃኙበት ኹለተኛ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።
በሩዋንዳ የዘር እልቂት ጉዳይ ከግል እስከ ‹ደቦ› አንብበናል። ብዙ ባለሙያዎች ከተራ የሩዋንዳ ጎብኚ ኢትዮጵያውያን እሰከ ጉምቱ ፕሮፌሰሮች አሁን በእኛ ሀገር እየሆነ ያለው እንዳይሆን ብዙ ወትውተዋል፤ ጽፈዋል፤ እኛም አንብበናል። ወሳኙ አልሰማም አለ እንጂ።
ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስከ ኦክስፎርድና ሀርቫርድ ድረስ ኢትዮጵያውያን እንኳ ጽፈናል፤ መርምረናል፤ ተመራምረናል። አጥንተን አስጠንተናል። ሀገር ውስጥ አንዴት እንደወደቅን እኔም አላውቅም እንጂ። መርማሪ ተመርማሪ ሲሆን ተፈጥሮም መልስ ታጣለች፤ እጅን በአፍ ላይ ከማስጫን በቀር። ከዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እስከ መለስ ቲዮሪ ነበረን፤ ተግባራዊ አልሆን አለን እንጂ።
ወደ ጉዳዬ ልመለስ። ወደ አማርኛ ከተተረጎሙት የሩዋንዳ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች ውስጥ እያለቀስንና ሰው መሆናችንን እስክንጠላ ድረስ ልብ ከሰበሩን መጻሕፍት ውስጥ የደብረ ብርሃኑ መዘምር ግርማ ወደ አማርኛ የተረጎመላት ኢማኪዩሊ አሊባጊዛ “Left to Tell” ‹ሁቱ ቱትሲ›ና ይሄ አሁን የምንዳስሰውና በታላቅ እህታችን ገነት አየለ አንበሴ የተተረጎመው “Petit Pays” ወይም ትንሿ ሀገር አንዱ ነው።
ይህ ጉዳይ ዳግም እንዳይከሰት ፋውንዴሽን አቋቁማ ትታገላለች፤ ከሀገረ አሜሪካ። መዘምርን እናመሰግናለን። አንቺንም እንዲሁ። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ባንጨምር ደግሞ ብዙ እንጎድላለን። እባክዎ የመጻሕፍት ቤታቸን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ያሳተመውን፤ የእርሳቸውን SOCIETY STATE and HSITORYን ከገጽ 407-427 ይጋበዙ። አረንጓዴው መጽሐፍ የ‹ደም እንባ›ን ያስታውሳል። በነገራችን ላይ የሩዋንዳን ዘር ዕልቂት ከመረመሩ የዓለም የተከበሩ ኤሊቶች አንዱ ናቸው፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ።
ይህቺ የ‹ትንሽ ሀገር› መጽሐፍ ዳሰሳ ለእነሱም፤ ብዙ የግድያ ዕቅዶችን ላከሸፉም፤ ሲከሰት ላስጠለሉ፤ ለተከላከሉ፤ ለመከለልና ለመሻር ለተሰዉ፤ አካለ ጎዶሎ ለሆኑ፤ ዛሬም ሌሊትና ቀን ለሚተጉ፤ በግልም እንደ መንግሥትም ለሚጠብቁን ተሻጋሪና አሻጋሪ ኢትዮጵያውያን ሸዋረገዶች ማስታወሻ ትሁንልኝ።
በነገራችን ላይ Petit ማለት በላቲን ትንሽ ማለት ሲሆን grand ማለት ደግሞ የትልቅ ትልቅ ማለት ነው። Grand ERD እንደ ማለት። ከትልቅ ትንሽ እንዲሰውረን እየተማጸንን፣ “Petit Pays” ወይም ትንሿ ሀገር ዳሰሳችንን እንቀጥላለን። መታወቅ ያለብት ብዙ ልዩነቶች እንዳሉንና ሁኔታዎችም የሚለያዩበት መንገድ መኖራቸውን ነው፤ በእኛና በሩዋንዳው ዕልቂት ጉዳይ።
ለምሳሌ ሩዋንዳ የሦስት ብሔሮች ሀገር ብቻ ናት። ሁቱ፣ ቱትሲና ትዋ ይባላሉ። ሦስተኞቹ በቁጥር ጥቂት ናቸው። ለዛ ነው አየሩን ያልሞሉት። የሩዋንዳ ዕልቂት ከቤልጅየም የዘር ካርድ መታወቂያ ከሶሾሎጂ እሰከ ሥልጣን ሽሚያ ይሰፋል። ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው። እኛም ጋር ይህ ሀቅ ይሠራል።
“እኔ የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም!”
ቃየን አቤልን በድንጋይ ሲገድለው ማንም አላየውም ነበር። በምድር ላይ በሕይወት የነበሩትም የቅርብ ቤተሰቦቹ ብቻ ነበሩ። ባዮሎጂካል ወይም ኑኪላር ፋሚሊ ብቻ እንብለው። ከግድያው መልስ አባቱ አዳም ‹ወንድምህ አቤል ወዴት አለ› አለው። ሥራውን የሚያውቀው ቃየን መለሰ፤ ‹እኔ የወንድሜ ጠባቂ አይደለሁም!› አለ። ያልተጠየቀውን ነው የመለሰው። ገዳይ አያርፍምም አያፍርምም፤ ደም በእጁ አለና። የሰው ደም ደግሞ ጩኸቱ አያስተኛም። ቃየል ቀጠለ ‹የሚያየኝ ሰው ሁሉ ይገድለኛል›› ይላል።
ትንሿ ሀገር የተሰኘው መጽሐፍ ባዮግራፊ ነው። ግለ ታሪኩ የተጻፈለት ሰው ታሪኩ እንዲህ ነው። እርሱ ባለታሪኩ ጋብርኤል እና እህቱ ኣና ከፈረንሳዊ አባታቸውና ከቱትሲ ሩዋንዳዊት እናታቸው ይወለዳሉ። ሲቃ ከመከሰቱ በፊት የተደላደለና የሚያስቀና ኑሮ ይኖራሉ። ፈረንሳዊ አባታቸው አፍሪካዊ ሠራተኛውን ‹ዝንጀሮ› ከማለት አያትና ልጅ እስከመናቅ ለጥጦ ጥላቻውን ይገልጻል፣ በመጽሐፉ።
አፍሪካዊት አያቱ ፎክሎር፤ ታሪክና ባህል ሲያስተምሩ እንታዘባለን። ፈረንሳዊው አባት ተልዕኮ ያለውና ሁሉንም ማለትም እየሆነ ያለውን ጨምሮ ወደፊትም ሩዋንዳ ውስጥ የሚሆነውን የሚያውቅ ይመስላል፤ በእኔ የግል ዕይታ። ለልጆቹ ፍቅር አለው። በውበት ተማርኮ በፍቅር የተንበረከከላትን አፍሪካዊት ውብ፤ የኹለት ልጆቹን እናት፤ ያልተገባ የሚያሳፍርና ፍቅርና ቤተሰብን የሚገድል፤ ከሰውነት ደረጃ በታች በሆነ ዘረኝነት ቤት ውስጥ እሳት ይለኩሳል።
ታላቁ መጽሐፍ ‹አንደበት እሳት ነው› ይላል። ልዩነት ቤት ውስጥ ሲጀምር መሸሻ ይርቀናል። የት እንጠለላለን? አእምሮ ጠንስሶ፣ ስሜት ሁሉን በልጦ ምላስ ተናገረ። የተናገረበት ቦታና የተናገራቸው ሰዎች ‹ታርጌት ኦድየንሱ› አልነበሩም። ‹በሀልዮ፣ በነቢብ፣ በገቢር› የተደረገውን ይቅር በል ነው የሚል፤ መጽሐፍ። የታሰበ ነገር ሁሉ ባይነገር የት በደረስን ነበር። ለታሰበ ክፋት ብንጸጸት ደግሞ ዓለም እጅግ ባልመረረችብን።
በመጽሐፉ ውስጥ ልጅነትና እውቀት በአጭር ይቀጫሉ። እህትነትና ወንድምነት ይጋጫል። ጓደኝነት እንደ ጽጌረዳ አብቦ በክፉ ጎርፍ በጊዜ ይጠረጋል። ልጅ ያለዕድሜው ያረጃል። እናት ማህጸኗን ትጠራጠራለች። አባትነት ከዘር ልጓም በላይ ይሳባል። አፍሪካዊ የጠዋት ፍካት ደመና ይሰውረዋል። ከውቂያኖስ ርቀት በላይ የዘር አክራሪነት አንድ አፍሪካዊ ጎጆ ያፈርሳል። ሩዋንዳዊቷ የጠዋት ጀምበር እኩለ ቀን አትዘልም። ጽናት፤ ማን አለብኝነት፤ አርበኝነት፤ ሀገራዊነት አገርን ከጥቃት ለመከላከል ክንፍ አውጥተው ሰማየ ሰማያት ይበራሉ። ከሀገር ወጥተው ሀገር ይቤዣሉ። የቤት ሠራተኛ ከቤት ውስጥ ሳይናገር ሲጠፋ ትህትና ቦታዋን ታጣለች። ጎበዝ ወንድ የቤት ሠራተኛ የለንም አይደል! ይሄ ብቻውን ሌላ ጉዳይ አይደለም? ኅብረት አንድነትና ውሳኔ ይጎድላሉ፤ መከራም ባይቀርም ቅሉ። ሩዋንዳ በቅርቡ የእልቂቱን 25ኛ ዓመት “ኑ ከእኔ ተማሩ” ብላ ዓለምን ጋብዛ አስከፊውን የክቡሩን የሰውን ልጅ እልቂት ባጭሩ ለመግለጽ አስጎብኝታለች።
ከወቅታዊነት፤ ከቀድሞ የሷ/የገነት አየለ የጽሑፍ ልምድም፤ መጽሐፉ ካለው ሀገራዊ አስተዋጽኦ፤ በይዘትም በቋንቋ ቁጥብነት/ልልነት አንጻር፤ ሀገራችን ካለችበት ሁኔታና በመጽሐፉ አስተማሪነት ምክንያት እነሆ ይሄን መጽሐፍ በወፍ በረር እንድንዳስሰው መርጠናል። የትርጉም ሥራ ክፍተቶች እንዳሉ ሆነው ማለቴ ነው። ለምሳሌ ምን ዓይነት የትርጉም ስልት እንደተከተለች አላብራራችልንምና።
በብሔር ጡዘት ትግል፤ ግድያና ዕልቂት ወጣት ተስፋው ይሞታል። ሀገር ታስጠላዋለች። ይሰደዳል። “ቅናትና ምቀኝነት ከኃጢአት ሁሉ የከፋ ነው“ (ገጽ 108) እያለ “ተስፋችንን ገደሉት“ እያለ በወጣትነት ሳይኖር ያረጃል። የማንነት መዛነፍ ይገጥመዋል። አፍሪካዊ ነኝ፤ ፈረንሳዊ ነኝ፤ ነጭ ነኝ ጥቁር ወይስ የቀይ ዳማ ነኝ በሚል ግራ መጋባት ውስጥ ይወድቃል።
እናት ከብሔር ተኮር የባሏ፤ የልጆቿ አባት ስድብ በኋላ ትወስናለች። ጓደኝነት፤ አብሮ አደግነት፤ ብሔር፤ ሚዲያ፤ ሴራ ይጎላሉ። የመናቅና የመገፋት ጥቃት ትሁቱን ሰው ‹አክራሪ› ሲያደርግ ሀገራችን ውል ትልብናለች። እሱ/እሷ ናት አይደለችም? ብለን የተከራከርንባቸው/የተከራከርንላቸው ሰዎቸ በዐይናችን ይደቀናሉ። የቀድሞ ባህሪዋ አልነበረም። ያለሞያችን ለጥል ከተሰለፍን ባለሞያዎቹ ይዘርሩናል። በነገራችን ልምድ የማይጠይቅ ሞያ አለ እንዳትሉኝ ብቻ። ይሄ መሆኑ እጅግ ነፍስን ያውካል።
መጽሐፉ በየምዕራፉ ያሳርፈናል። ቦታ አለው። ትንፋሽ እንወስዳለን። ማሰላሰያ ጊዜም ይሰጠናል። ቃላት ይሾራሉ። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ፓን አፍሪካዊ ምልክት ሲውለበለብ በቡሩንዲና በሩዋንዳ እናነባለን። በየመሃሉ ልብን የሚሰረስሩ ገለጻዎች ይገጥሙናል። ሁሉም የጥላቻ መነሻ ብሔር ብቻ አይደለም፤ አይሆንምም። ‹የሚሆነው ሁሉ የሆነው አንድም ሁለትም ሦስትም… ለብዙ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል› እንዲል ሊቁ። ቅናትና ምቀኝነት እጅ አውጥተው ይቧጭሩናል። ከአባ ጨጓሬ በላይ ቀፋፊ ዳሳሽ ማንነቶች ይኮሰኩሱናል፤ ከግል ወዳጅ እስከ ፖለቲከኛ። በ ‹ቦህ ላይ ቆረቆር› ሆኖብን ነው እንጂ።
ወጣትና እናት በዘር ልዩነት የቤት ውስጥ ችግር ተስፋ ይቆርጣሉ።“ክፉ ውሻ“ ገ.32 የሚል አጥር በር ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ስናነብ እኛም አብረን እንታመማለን። የበራችን መቃን እንቅፋታችን ይሆናል። “ቅናትና ምቀኝነት ከኃጢአት ሁሉ የከፋ ነው“ ገ.108 ሲል የዛሬ ሚናችንን መለየት አለመቻላችን ውል ይልብናል። “ለቤት እንስሶቻቸው እንደሚጨነቁ ለሰው ልጅ ቢጨነቁ ጥሩ ነው/ነበር“ ገ.116 እያልን ፈጣሪ ልብ እንዲያራራ እንማፀናለን። ወጣቱ “ተስፋችንን ገደሉት“ ገ.119 “ስቃይ ፍትህ አልባ ናት፤ ስብራት ፍርደ ገምድል ናት” ሲል ልባችን በውጋት ይቃትታል።
“ቆሻሻ ሁቱ ቆሻሻ ቱትሲ ቆሻሻ ሁቱ“ ገ.129 ሲባል ኢትዮጵያውያን ሀገራችን ውስጥ በሚሆነው ነገር ውስጥ የለንበትም ወይ ስንል በሐሳብ ፈረስ ወደ ኋላ እንገሰግሳለን። “ማንኛውም የሰው ዘር የተባለ ሁሉ ሊፈረጅ የሚችልበትን መስፈርት በጠቅላላ የሚያሟሉ ክፉዎች ከደጎች፤ እርኩሶች ከግፉዓን ጋር ይርመሰመሱልሃል።“ ገ.171 በሚል አንቀፅ ስር ፍረጃንና ፍረጃችንን በክፉ እንጠላለን። እናት በምትሳሳላቸው ልጆቿ ላይ ጭምር ትጨክናለች። አባት በንቀት ጥሉን ከለኮሰ በኋላ ይፀፀታል። ይማጸናል። ‹ሞኝ ካመረረ ፍየል ከበረረ› ነውና፣ ትሁቷ እናት አትሰማም። ሁሉም እንዳልነበረ ይሆናል።
ወጣት “ይቺ አገር የምትገድል ወጥመድ ሁናለች።“ ገ.197 ሲል ይቆዝማል። አክስት የእህቷን ልጆች የከረመ አስከሬን ለመቅብር ስታነሳ ይፈረካከሱባታል። ግማቱ ይጠነባታል። በሳሙና ደግማ ደጋግማ ወለሉን ታጥበዋለች። በቃ ከዛ ጊዜ ጀምሮ በዚያ ትዝታ ሰቆቃና ተስፋ እዚያው ቆማ ትቀራለች። መርሳት ያቅታታል። ሁሉም ነገር በቀቢጸ ተሰፋ ይተካል። በሽተኛ ትሆናለች። ሀገር እንዴት የምትገድል ወጥመድ ትሆናለች፤ ሀገር ዘውድና ክብር መሆኗ ቢቀር እንዴት የምትገድል ወጥመድ ትሆናለች? ይሄ በጣም ያማል!
“ለይልኝ”
በብሔር ጉዳይ ሴት አትጎዳ፤ በእውነት። እናት አትጎዳ። እናት አትበድ። እህት ትህትና አትጣ። ሴት ቤት ውስጥ ከታመመች የማይታመም የሰው ዘር የለምና። ቤት ሀገርና ዓለም በአንድ ላይ አናታችን ላይ ይደፋሉ። እናት ተገፍታ ስትወስን መልስም መልስ ያጣል… ከኔ ይበልጥ መታዘብ ከፈለጉ ደግሞ መጽሐፉን ገዝተው ያንብቡት። “ስቃይ ፍትህ አልባ ናት። የልብ ስብራት ፍርደ ገምድል ናት። “ ገ.163
የባለታሪኩ ጋብርኤል ጓደኛ አርማን ከጓደኛው ጋራ ይነጋገራል፡-
“ባያንሙላንጌ (የጥላቻ ሥም መሆኑ ነው) ብለው ነው የሚጠሩን እዛ”
“ይሄንን ያለዛሬ ሰምቼ አላውቅም”
“እሺ የማንንም ቡድን መደገፍ የማይፈልግስ? መብቱ አይደለም?” ብዬ ጠየቅሁ
“አማራጭ የለንማ። ሁላችንም የየራሳችን ካምፕ አለን።” አለ ጁጁኖ ፈገግታው የነገር መሆኑ እያስታወቀበት ገ.164
“እያነቡ እስክስታ”
መጽሐፉ እጅግ የሚያስደምሙና የሚያስቁ ገጠመኞቸ አሉት። ለምሳሌ የተራኪው ጓደኛ ግርዛትና ታሪኩን እኔ አልፌበታለሁ። ብዙ ኢትዮጵውያንም እንዲሁ። እባክዎ ግርዛት ከኤች አይ ቪ ስለሚከላከል ወንዶች ሆይ ተገረዙ። ስንቀጥል በግራዬ በኩል ታክሲ ውሰጥ አንዲት ወጣት አጠገቤ ተቀምጣ ስለ ግርዛታቸውና ሁኔታው እያነበብኩ ሳቄን መቆጣጠር ስላልቻልኩ፤ እያፈርኩም ቢሆን ጉዳዩን አውርቻታለሁ። ‹አየሽ! አፍሪካውያንኳ አብረን አድገናልኮ› ብዬ።
አፍሪካውያን በእውነትም አብረን አድገናል። ብዙ ነገሮቻችን አንድ ናቸው። ከድህነት፤ ከሳይክል ስርቆት፤ ከተረባችን፤ በንግግራቸን፤ አካባቢያችን ዋናና ሴቶ፤ በውሃ መበላት፤ ደኖች ውስጥ መዝናናት…ወዘተ። የትምህርት ቤት ትዝታና አብረን ማደጋችንን እየታዘብን ከልብ እንስቃለን።
ሩዋንዳ በቡሩንዲ፤ በፈረንሳይ፤ በሚዲያ ፋክተሮችና በብሐየር ልዩነት ጡዘት፤ በፖለቲካ ልምምድ እጥረት፤ በስደትና ተያያዥ ምክንያቶች፤ በዴሞክራሲ መቀጨጭና ተቋማት ግንባታ ዝግመት ምክንያት እልቂት እንደገጠማት ዓለም ተስማምቷል። ለማንኛውም ይሄ ዳሰሳችን የይዘት ብቻ ዳሰሳ እንደሆነ ይያዝልኝ፤ ያላለቀ Content analysis እንደ ማለት። መጽሐፉን እንዲያነቡትና ለሀገርዎም የልዩነት ምክንያት እንዳይሆኑ እየጋበዝኩ፣ እርስዎ ደግሞ አንብበው ያልጨረስኩትን ይሂዱበት።
እናትን ጭፈራ ቤት ሥር የማያኖር ሀገር ይስጠን !
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014



