መነሻ ገጽዜናትንታኔበሥነልቦና የደቀቁ ተስፈኞች

በሥነልቦና የደቀቁ ተስፈኞች

የሕወሓት ታጣቂዎች በሰሜን ዕዝ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት በነበረው “የሰላም ማስከበር ዘመቻ” እንዲሁም ተቋጨ ከተባለ በኋላ ደግሞ “የሰላም ማስከበር ዘመቻው” ወደ ጦርነት ተቀይሮ ለወራት ያህል በተካሄደውና እስከ አሁንም ድረስ ባልተቋጨው ጦርነት፤ በአማራ እና በአፋር ክልል ንፁሓን ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከስተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ሆነ ተብለው የተፈፀሙ ግድያዎችን ሳይጨምር በጦርነቱ ሳቢያ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ንፁሀን ሰዎች ለቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት መዳረጋቸውን በምርመራ ማረጋገጡን መጋቢት 2/2014 ባወጣው የዳሰሳ ጥናት ማወቅ ተችሏል።

ጥናቱም “በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተገድለዋል። በሕገ ወጥ መንገድ ከተገደሉት በተጨማሪ 309 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል” የሚል ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል አደረግኩት ባለው “የሰላም ማስከበር ዘመቻ” በርካታ የትግራይ ንፁሓን ዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደደረሰባቸው ሲነገር መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ካሳለፍነው የየካቲት መገባደጃ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቆቦ ከተማ ተፈናቅለው ነበር። አሁን ላይም ከነበሩበት መጠለያ ጭፍራ ወደተባለ ቦታም ተዛውረዋል።

የቀድሞ የቆቦ ከተማ ከንቲባ አዲሱ ወዳጆ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በየቀኑ ሦስትና አራት መኪና የትግራይ ተወላጅ ወደ ከተማው እየመጣ ሲሆን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻም 35 ሺሕ ሰዎች እየገቡ ነበር።

ጉዳቱ የደረሰባቸው ሰዎች ቤተሰቦች ለበቀል እየተነሳሱ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል የተባለ ሲሆን፣ ለአብነትም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ ስር በምትገኘው ገደባ ተብላ በምትጠራው አካባቢ አንድ ልጁ በሕወሓት ታጣቂዎች የተገደለበት አባት ለበቀል በመነሳሳት አራት ከትግራይ የመጡ የሕወሓት አባላትን እንደገደለ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

አንገት ያቀረቀሩ ወላጆች
ዕድሜ ለቴክኖሎጂ፣ ዓለምን በአንድ መንደር ጨምቆ እያንዳንዷን ክስተት ለማወቅ ቅርብ የሆነበት ዘመን ላይ መድረሳችን አይካድም። ይሁንና ጎልተው እንዳይወጡ አፈሙዙ የጀቦናቸው የልብ ቁስሎች የሚሰሙት ከጦርነት ማግስት ሆኗል። ይህን የዘገዬ እውነት “የጦርነት አስከፊው ገጽታ” ብለዉታል የቀመሱት። ከትግራይ ተፈናቃዮች መካከል አንዲት እናት እንዲህ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። “ጦርነት ሁሌም እርጉዝ ነው። ብዙ ያልተነገሩ ጉዶች አሉት። ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዲሉ ሴራዎቹና ልብ አንፍር ክስተቶቹ የሚታወቁት ከረፈደ ነው” ያሉት አምሰለት ሀጎስ የተባሉት እናት ናቸው።

አምሰለት ኹለት 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆቻቸው ተገደው ለጦርነት ከተሰለፉ በኋላ እንዴት እንደሆኑ ማወቅ አልቻሉም። ጎይቶም ብርሃነ እና ሰመረ ብርሃነ ይባላሉ። ሕወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በነበረው ጦርነት ስልታዊ በሆነ መንገድ ድል ለመቀዳጀት ከፊት ማግዷቸው ከነበሩት ሕጻናት መካከል መሆናቸውን ይገምታሉ።

ሕወሓት ልጆቻቸውን ለጦርነት እንዲያሰልፉ በተደጋጋሚ መልዕክት ሲያስተላልፍ ከእሳቱ ለማዳን ወደ ገጠር ሊያሸሹ ሲሉ አስገድደው እንዳሰለፏቸው አምሰለት እንባ ያቀረረ ዐይናቸውን አቦዝዘው፤ ሳግ በሚተናነቀው ድምፃቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“ኹለት አንበሶች ሲፋለሙ ምስኪኑ ሳር ይጎዳል” እንዲሉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት የሚያደርጉት ፍልሚያ የሕዝብን ነጻነት ማወጅ የሚመስል የሕዝብን የመኖር መብት መመንተፍ መሆኑ እኔ እንደገባኝ ሌሎቹም እንዲገለጽላቸው አብዝቼ ተመኘሁ ብለዋል፤ አምሰለት በቆዘመ ሁነት።

ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው በኢትዮጵያና በሕወሓት መካከል ባለው ጦርነት፤ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የጠራው የሕወሓት ቡድን ሕጻናትን ለጦርነት አሰልፎ እንደነበር ይታወሳል።

ከመቀሌው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ 16 ወራት ውስጥ 139 ሕፃናት በቀጥታ በጦር መሣርያ በደረሰባቸው ጉዳት ወደ ሆስፒታሉ የተወሰዱ ሲሆን፤ 11 ሕፃናት ሞተዋል። በሌላ በኩል ሌሎች 39 ሕፃናት ደግሞ ለዘላቂ የአካል ጉዳት መዳረጋቸው እየተገለጸ መቆየቱን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።

የሕወሓት ቡድን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ሕጻናትን የሚጨፈጭፍ በማለት “ፋሽስት” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ታዲያ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ያለው የጥፋተኝነት ሥም ተሸላልሞ መነቋቆር፣ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተሰጠ “የወዳጅ ስሙ አመዳም ነው” ዓይነት ነገር መሆኑ ገብቶናል ይላሉ አንዳንዶቹ ደግሞ።

አዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው። ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው፣ “ሴራው ሕዝብን አዳክሞ መሬት የመሸንሸን ጉዳይ ነው። በዐይነ ቁራኝነት መተያየቱም ፌክ ነው” ብለዋል።
አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ ሲያስቆጥር እስከ አሁን ምንም መፍትሄ ባልተሰጠው ጦርነት ሳቢያ 8 ሺሕ 419 ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው መጠፋፋታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሪፖርት ጠቁሟል።

መንግሥት የሰላም ማስከበር ዘመቻ ብሎ በጠራውና በትግራይ ክልል ስምንት ወራትን በወሰደው ጦርነት፣ ሰባት ሺሕ 165 ሕጻናት ከወላጆቻቸው ተጠፋፍተዋል ነው የተባለው። ቀሪዎቹ ደግሞ የሰላም ማስከበር ዘመቻው በይፋ ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ ሲፋፋም አፋር ክልል 39፤ በአማራ ክልል 1ሺሕ 215 የሚሆኑት ሕፃናት ከወላጆቻቸው እንደተጠፋፉ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉትና በቆቦ ከተማ ከዘመድ ቤት ተጠግተው ያሉ ሕይወት ክብሮም የተባሉ እናት፣ “አራት ልጆቼ የት እንዳሉ አላውቅም” ብለዋል። ሕይወት ልጆቻቸው ጋር ለመለያየት የተዳረጉት፣ ሕወሓት በጦር ግንባር የሚሰለፍ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ልጅ አዋጡ ሲል መሆኑን አንስተዋል።

ከመፈናቀሉና ከርሃቡ ይልቅ ጭንቅላቴን ወጥሮ ሰላም የነሳኝ ልጆቼ ያሉበትን ሁኔታ አለማወቄ ነው ያሉት ሕይወት፤ እስከ አሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ) ልጆቻቸውን እንዳላገኙና የሚተኙት እንቅልፍ ሰላማዊ እንዳልሆነ በማዘን ገልጸዋል።
‹‹የእናት አንጀት ግፉን አይችልም። መልካም መልካሙን ለማሰብ ይሰንፋል።›› ያሉት ተፈናቃይዋ፣ ምንም የማያውቁትን ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ማለያየት ብቻ መጥፎ ታሪክ ነውና አይደገም ሲሉ አውግዘዋል።

- ይከተሉን -Social Media

እንዲህ ባለ ወቅት፤ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ይታመናል። ዋነኛ ምክንያቱም ሴቶች ብዙ ጊዜ ተገዶ የመደፈር ዕጣ ፈንታ ስለሚገጥማቸው ነው። ምንም እንኳ አሁን አሁን ሴት ልጅ የእኩልነት መብቷ ሊከበርላት ይገባል የሚለው መርህ እየጎላ ቢመጣም፣ ችግሩ ግን እስከ አሁን የተተወ አይመስልም። በተለይም በጦርነት ወቅት ሲብስበት ተስተውሏል።

በጦርነት ወቅት ልጃገረዶች ብቻ ሳይሆኑ ባለትዳሮችን ጨምሮ መነኮሳትም ተደፍረዋል። በመደፈራቸው የሥነ ልቦና ጫናውን መሸከም አቀበት የሆነባቸው ነገን ቀጥ ብሎ ባለመየት እንደዋዛ ራሳቸውን ለማጥፋትም ደርሰዋል። በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በነበረችው ወልድያ ከተማ ወጣ ብለው ይኖሩ ከነበሩ ባለትዳሮች መካከል፣ ባለቤቷን አስረው ከፊቱ የደፈሯት ሴት ራሷን ማጥፋቷን ቤተሰቦቿ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ታዲያ በጦርነቱ ጦስ ልጆቻቸው የጠፉባቸው ወላጆች በሕሊናቸው “ልጆቼ ተደፍረው ይሆናል” የሚል ሥነ ልቦናን የሚያውክ መጥፎ ስሜት ፈጥሮባቸው ይገኛል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከተጠፋፉት 8 ሺሕ 419 ሕፃናት መካከል 4 ሺሕ 311 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፤ 387 ጠፊዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቢገናኙም 2 ሺሕ 580 የሚሆኑት ደግሞ በመጠለያ ውስጥ ሆነው ቤተሰብ ለመገናኘት የሚጠባበቁ ናቸው። በመሆኑም፣ በትግራይ ክልል 331፤ በአማራ 397 ያህሉ ሕፃናት በቀይ መስቀልና በሌሎች ተቋማት ትብብር ከቤተሰቦቻቸው የተገናኙ ሲሆን፣ የአፋር ሕፃናት እስካሁን ቤተሰባቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ቅጥ ያጣው ሕግ
የዓለም አገራት በርካታ የረቀቁ ሕጎች እንዳሏቸው ሁሉ ኢትዮጵያም የረቀቁ ሕግና ደንቦች አሏት። ተፈጻሚነታቸው ግን አይስተዋልም። ዜጎች በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል የሚሉት የሕግ ባለሙያው አንዱዓለም እያሴ፣ ተፈጻሚነቱ ግን ተግባር ላይ እየዋለ አይታይም ብለዋል።

በርካታ ንጹሓን ዜጎች ሕይወታቸው በጦርነት የተቀጠፈው፤ በርካቶች የተፈናቀሉት፤ ሕፃናት ለጦርነት የተሰለፉት፤ ቤት ንብረት የወደመው ሕግ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ተፈጻሚነት ጎድሎት ነው ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
በመሆኑም፣ ሕግ ከመጻፍ በዘለለ ተግባር ላይ ማዋሉ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የሰላም መደፍረስ ሊያላቅቃት የሚችለው ብቸኛውና አስፈላጊው መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

ከሥነልቦና ጉዳት መላቀቅ እንዴት?
በርካቶች በሥነ ልቦና ጉዳት እየተብሰለሰሉ አንገታቸውን እንዲደፉ መንስኤ ከሚሆኑ ክስተቶች መካከል በጦርነት ወቅት የሚደርሰው ጉዳት ተጠቃሽ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያወሳሉ።
በጦርነት ወቅት ብዙዎች ላይ የሥነልቦና ጉዳት ይደርሳል የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ቴዎድሮስ ጌታቸው ናቸው። በሥነ ልቦና መጎዳት የሚመጣው የሚፈልጉትን ነገር በማጣት፤ አሰቃቂ አደጋዎችን በማየት እና በመሰል ክስተቶች መሆኑን ያነሱት ቴዎድሮስ፤ ሰዎች ሲገዳደሉ ያዩ በተለይም የሚወዱት ሰው ሲገደል ያዩ ሰዎች ሥነ ልቦናቸው ይጎዳል ባይ ናቸው።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ ከሆነ፤ እንኳን የሰው ሕይወት እያለፈና በጦርነት ወቅት የሚሰማው የተኩስ ልውውጥ ብቻ ለፍርሃት፤ ፍርሃቱ ለጭንቀት፤ ጭንቀቱ ደግሞ ለሥነ ልቦና ጉዳት ይዳርጋል ይላሉ።
በሥነ ልቦና ጉዳት ምርኮ ሳይታሰብበበት ቀስ በቀስ በጭንቀት አማካኝነት ተላምዶ ከሰዎች ጋር ስለሚዋሃድ ልምድን ማስወገድ ዋጋ ሊያስከፍል ቢችልም፤ የሚከተሉትን መስፈርቶች በመከተል ግን ከጉዳቱ መላቀቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ከሥነ ልቦና ጉዳት ለመላቀቅ በመጀመሪያ ደረጃ ጸሎት በማድረግ ወደ ፈጣሪው መጣበቅ፤ ሆድ የመባስና የመረበሽ ስሜት ሲሰማ “ብቸኛ ነኝ” ብሎ ከመቆዘም ይልቅ ፈጣሪ እንዳለው ማሰብ። ከዚህም በዘለለ ሌሎች በርካታ ወዳጆችን ማፍራት እንደሚቻል ማሰብና ያሰቡትን ማድርግ ችግሩን ለማቃለል ይረዳል። የሚረብሽ ስሜት የአእምሮን በር ሲያንኳኳ መልካም መልካም ነገሮችን በማስታወስ ለመጥፎው ክስተት ቦታ መንፈግ ኹለተኛውና ተመራጩ መፍትሄ ነው ተብሏል።

በሦስተኛ ደረጃ ለምሳሌ የመደፈር፤ የወዳጅ በጦርነት መሞት፤ ልጅ መጥፋት ክስተት በልቦና እየተመላለሰ የሚረብሽ ከሆነ፤ በዳዩ አካል ካሳ እንዲክስ፤ በሕግ እንዲጠየቅ ማድረግ፤ የልጅ መጥፋት ከሆነ የሚቻለውን ያክል ማፈላለግና እንደሚገኝ ተስፋ ማድረግ፤ ካልተገኘም ጉዳዩን ለሚያምኑበት ፈጣሪ መስጠት በሐሳብ ከመብከንከኑ ለመዳን ይረዳል።

ከዚህ በዘለለ ብሔራዊ ምክክር በማድረግ ጎጂና ተጎጂን በሰከነ መንፍስ እንዲወያዩ ማድረግ ሌላኛው ችግሩን ሊያቀል የሚችል መንገድ መሆኑን የሥነ ልቦና ባለሙያው አንስተዋል።

የአገር ሽማግሌዎች ሚና
በድንበር ክለላ፤ በሀብት ክፍፍል፤ በግጦሽ መሬት እንዲሁም በሌሎች መሰል ክስተቶች አለመግባባቶች ጎልምሰው ወደለየለት ጥላቻና መገዳደል ሲያመሩ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በየአካባቢው ያሉ የዕድሜ ባለጸጋዎች ምክር በመለገስ ትኩሳት የሚሰማቸውን አቀዝቅዘው የተበደሉትን ካሳ እንዲሰጣቸው ወስነው ነገሩን ከጡዘት ሲመልሱ ይስተዋላሉ።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሥማቸው በላይ የተባሉ የዕድሜ ባለጸጋ አባት፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር እንድትላቀቅ በየአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ሕዝቡ ከሕዝቡ ጋር ያለው አመለካከትና ቀረቤታ መልካም ነው፣ ችግሩ ባለሥልጣናቱ ናቸው ያሉት የዕድሜ ባለጸጋው የተራራቁት ብሔሮች በሽማግሌዎች ቢገሰጹ መፍትሄ አይጠፋም ባይ ናቸው።

ትላንት መስዋዕት ተከፍሎባት የተረከብናትን አገር ለነገዎቹ ለማስረከብ እንኳን ከተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ከአርሶ አደሩም አልታየም ያሉት ሥማቸው፤ ትውልዱ ይህን ሊያስተውል፤ ባለሥልጣኑ ኃላፊነቱን በመወጣት ከጸጸት ዕዳ መዳን የአዕምሮ ሰላም እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

ትላንት የነበረውን አስታውሰን ዛሬ ኢትዮጵያን እዚህ ደረጃ ካደረስናት፤ የዛሬውን ሰፊ ክስተት ብቻ አንጠልጥለው የሚጓዙ የነገ አገር ተረካቢዎች ምን ደረጃ ይደርሱ ይሆን? የጥያቄውን መልስ ለሁሉም የቤት ሥራ ሰጥቻለሁ ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች