መነሻ ገጽዜናወቅታዊድለላና የቤት ኪራይ

ድለላና የቤት ኪራይ

ሰዎች በዚች ዓለም ሲኖሩ፣ የተለያዩ ሕጋዊ ሂደት የሚጠይቁ ድርጊቶችን ያከናውናሉ። ለምሳሌ ያህል ጥቂቱን ብንጠቅስ፤ ቤት ይከራያሉ፣ ያከራያሉ፣ ጋብቻ ይፈፅማሉ፣ ንብረት ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ እንዲሁም የሠራተኛ ቅጥርን የመሳሰሉ ተግባራትንና ሌሎችንም ያከናውናሉ።

ለዚህም በእለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የተለያዩ ውሎችን እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ። ብዙ ጊዜም ንብረት ሲገዙ እና ለንግድም ሆነ ለመኖሪያ ቤትን ሲከራዩ፣ የጽሑፍ ውሎችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል። በአንጻሩ ምንም ዓይነት ውል ሳይጠቀሙ ጉዳያቸውን የሚፈጽሙ አካላት እንዳሉም የማይካድ ሀቅ ነው።

ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከሚያካሂዷቸው ተግባራት መካከል ለመኖሪያ ፍለጋ የሚያደርጉት ውጣ ውረድ በተለይ አሁን ኑሮ በተወደደበት ወቅት በስፋት የሚታይ ነው። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ አንድም ጦስ የሆነው መኖሪያ ቤትን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ላይ ነው።

በተለይም ኀብረተሰቡ በየእለቱ የሚጠቀምባቸው መሠረታዊ ፍጆታዎች፣ የግንባታ እቃዎችና በሌሎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየተፈታተነ ይገኛል።

መንግሥት በበኩሉ ለዋጋ ግሽበቱና ላስከተለው የኑሮ ውድነት እንደምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው አገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳዮችን ነው። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የጥሬ ግብዓት ውድነት፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያለው የፀጥታ አለመረጋጋቶች እንዲሁም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ለዋጋ ግሽበቱ እና ለኑሮ ውድነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው።

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሕይወት ከተፈታተነው ከኑሮ ውድነት ጎን ለጎን የቤት ኪራይ ጉዳይ ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ አይካድም።

የኑሮ ውድነቱን ተገን በማድረግ ሳቢያ በየወቅቱ የቤት አከራዮች በቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ ባለፈ ከተከራዩ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁሉ እንዲለቁ የሚያደርጉ እንዳሉም ሲያነሱ ይደመጣል። ቤት ማስለቀቅና ዋጋ መጨመር በወቅታዊ ሁኔታው ሳቢያ በመንግሥት ቢከለከልም፣ ያን ያህል ውጤታማ መመሪያ አለመሆኑን የሚናገሩ አሉ።

አበበች ዓለሙ የመኖሪያ ቤት አከራይ መሆኗን ትናገራለች። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ አበበች እንደምታስረዳው፣ ያላትን አንድ ክፍል የሚከራይ ቤት ከስድስት ወር በፊት እስከ 2500 ብር እንዲያከራይላት ለደላላ መንገሯን ታወሳለች።

ነገር ግን በደላላው በኩል ቤቷን 3 ሺሕ ብር እንደሚያከራይላት እና ለኮሚሽን ከምትከፍለው ከ250 ብር በተጨማሪ ተጨማሪውን 500 ብር እንዲከፈለው የጠየቀበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቁማለች። አበበች ከደላላ በቀረበላት ሐሳብ ተስማምታ እና የተጠየቀችውን ክፍያ ፈፅማ ቤቷም እንደተከራየላት አልሸሸገችም።

ይህ ዓይነቱ አሰራር እና ግንኙነት አሁን ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ደላሎች ለአከራዮች በሚያቀርቡት ጥያቄ በስፋት እየተተገበረ ያለ ልምድ ነው ባይ ናት።

በተጨማሪም ደላሎች ተጨማሪ ጥቅም ወይም የኮሚሽን ክፍያ ለማግኘት ሲሉ፣ ‹‹ቤትሽን በተሻለ ብር እናከራይልሻለን። ያከራየሻቸውን ሰዎች ተጨማሪ የቤት ኪራይ ጨምሩ በያቸው። የሚስማሙ ካልሆነ አስወጪ።›› የተባለችበት ጊዜ መኖሩን ታስታውሳለች። በወቅቱ በቀረበው ጥያቄ ባትስማማም በሐሳቡ የሚስማሙና ተከራዮችን የሚያንገላቱና የሚያሳቅቁ አከራዮች መኖራቸው ሊታወቅ ይገባል ትላለች።

አበበች የቤት ሠራተኛም በደላላ በኩል ቀጥራ እንደነበርም ጠቅሳለች። በየወሩ 2 ሺሕ ብር ለመክፈል በደላሎቹ አማካኝነት ተስማምታ፤ የራሷን ድርሻ 2 መቶ ብር እንዲሁም የቤት ሠራተኛዋም ከመጀመሪያ የወር ደመወዟ ላይ የሚቆረጥ ተጨማሪ 2 መቶ ብር ክፍያ በድምሩ 4 መቶ ብር ለደላላው የኮሚሽን ክፍያም ፈጽማለች።

የቤት ሠራተኛዋ ቅጥር አልቆ በሥራ ላይ በቆየችባቸው አራት ቀናት የሚጠበቅባትን የቤት ሥራ ማለትም ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብ እና ሌሎችን ሳታስተጓጉል ማከናወን መቻሏን እና ኃላፊነቷን መወጣቷንም አበበች ተናግራለች።
ከአራቱ ቀናት በኋላ ግን የቆየችበትን ቀናት የደመወዝ መጠን እንደማትፈልግ ካስረዳች በኋላ፣ በአምስተኛው ቀን እህቷ የጤና ሕመም እንዳጋጠማትና ቤተሰቦቿ ስልክ ደውለው እንደነገሯት በማስረዳት ተሰናብታ መውጣቷን ገልፃለች።
የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ኹለት ጊዜ እንዳጋጠማት ያነሳችው አበበች፣ እነዚህ አጋጣሚዎች በሌሎች ሠራተኞችም በኩል ጎረቤተቿና ወዳጆቿ ላይ በተደጋጋሚ አጋጥሞ መታዘቧን ጠቅሳለች።

ለዚህ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማለት ባይቻልም፣ አንዳንድ የቤት ሠራተኞች ከደላሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠንከር እና በመመሳጠር እንዲሁም የኮሚሽን ክፍያን በጋራ ተጠቃሚ በመሆን ከአንድ ቀጣሪ ቤት በመውጣት በሌላ ቤት የሚቀጠሩበትን ሰንሰለት ለመፍጠር ነው ብላለች።

ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እና የቤት አከራይ መሆኑን የሚናገረው ክፍሌ ሞላ ነው። ክፍሌ እንደሚያስረዳው ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ በደላላ በኩል ቤቱን እንዳከራየ እና ለደላላው መደበኛ የኮሚሽን ክፍያ በኹለቱም በኩል 20 በመቶ ሲያስገኛቸው እንደነበረ ይናገራል።

በደላላው በኩል ምንም ዓይነት ጥያቄ ባይመጣም፣ በተከራዩ በኩል ግን የማይዘነጋ አጋጣሚ አጋጥሞኛል ያለው ክፍሌ፣ ከኹለት ዓመት የኪራይ ቆይታ በኋላ ያከራየው ግለሰብ ቤቱ የራሱ መሆኑን እና መክሰስ እንደሚችል አስታውቆ ኪራዩን እንዳቋረጠበት ተናግሯል። ምንም እንኳን ያከራየው ቤት ራሱን የቻለ ግቢ ቢሆንም፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ለኹለት ጊዜ የቤት ኪራይ ጭማሬ ማድረጉን ጠቁሟል።

- ይከተሉን -Social Media

ከዚህ ባለፈ ግን በደላላ ተመርኩዞ አከራይ ላይ ተጨማሪ የቤት ኪራይ መጨመርም ሆነ እንዲወጡ ጥያቄ አቅርቦ እንደማያውቅ ይናገራል። አክሎም፣ ተከራዩ ላይ ክስ ጀምሮ ጉዳያቸው በሕግ ክትትል ስር በነበረበት ወቅት፣ በወረዳው በኩል ያለው የቤት ካርታ መረጃ በተከራዩ በኩል መሆኑን የሚያስረዳ ነበር።

ነገር ግን፣ ቤቱ የራሱ መሆኑን የሚገልፅ እና የአከራይ እና ተከራይ ውል የፈፀመበት እንዲሁም ተጨማሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የአከራይ እና ተከራይ የቤት ግብር የከፈለበትን ማስረጃ ማቅረብ በመቻሉ አከራይቶት የነበረው ቤት ሊመለስለት እንደቻለ አስረድቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አከራይና ተከራይን በማገናኘት ሕይወቱን እንደሚያስተዳድር የሚናገረው ሀብታሙ አበራ ነው።

ሀብታሙ እንደሚለው ትላልቅ ቤቶችን አከራይና ተከራይን በምናገናኝበት ወቅት ተከራዩ ግለሰብ የሦስት ወር የቤት ኪራይ ቀድሞ የሚከፍል ከሆነ፣ እስከ ቀጣዩ ስድስት ወራት ምንም ዓይነት የቤት ክፍያ እንደማይጨምር እና በራሱ ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር ለመልቀቅ እንደማይገደድ ይናገራል።

ለዚህ ደግሞ አከራዩና ተከራዩ በሚገናኙበት ወቅት ከፈረሰ በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ ውል እንደሚፈራረሙ እና ግልባጩን ለቀበሌ ከማስገባት ባለፈ በወረዳ በኩል ራሱን የቻለ የአከራይና ተከራይ ግብር እንደሚከፈል ያስረዳል።
ሀብታሙ አክሎም፣ አከራይና ተከራይ ውሉን ከተፈራረሙ በኋላ ከኹለቱም አካላት የኮሚሽን ክፍያ 20 በመቶ ከመቀበል ባለፈ ምንም ዓይነት አሻጥር የለም ባይ ነው።

የአከራዩ እና ተከራዩ ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ግን በአከራዩ በኩል ተጨማሪ የቤት ኪራይ የሚጨምርበት ሂደት እንደሚኖር እና ለመልቀቅም የሚገደድበት ሁኔታ መኖሩን ያነሳው ሀብታሙ፣ በዚያ ወቅት ግን በአዲስ መልክ ቤቱን ለማከራየት ሥራ የሚጀምሩበት ወቅት መሆኑን አልሸሸገም።

በተጨማሪ ትናንሽ ቤቶችን ለማከራየት አከራይ እና ተከራይ በሚያገናኙበት ወቅት ጥቂት የሚባሉ ካልሆኑ በስተቀር ውል እንዳልተለመደ አስረድቷል።
በዚህ ጊዜ አከራይ እና ተከራይን አገናኝተው፤ ከሁለቱም በኩል የኮሚሽን ክፍያ ከመቀበል ባለፈ ምንም ዓይነት ውል እንዲፈራረሙም ሆነ ጣልቃ እንደማይገቡም ተናግሯል።

ምናልባት ይላል ሀብታሙ፤ ተከራዩ ተከራይቶ የመጀመሪያ ወር የቤት ኪራይ ከከፈለ በኋላ ብዙ እንግዶች በየወቅቱ የሚያቀኑ ከሆነ በአከራዮች በኩል ተጨማሪ የቤት ኪራይ እንዲከፍል ከመገደድ ባሻገር የፀጥታ ችግሮችን በተከራየበት ወቅት የሚፈጥር ከሆነ የተዋዋሉት ውል ከሌለ እንዲለቅ ይገደዳል።

ከዚህ ውጭ ግን ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከተከራዩችም ሆነ ከአከራዩች ጋር በመመሳጠር የጥቅም ግንኙነት ለማግኘት ምንም ዓይነት ርቀት እንጓዝም ባይ ነው።
ሌላው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ እና በድለላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚኖር ያስረዳን ግለሰብ፤ ሀብታሙ ባነሳው ጉዳይ ይስማማል። በትላልቅ ቤቶች ላይ ራሱን የቻለ ውል እንዳለ ጠቅሶ፤ አከራዩ እና ተከራዩ ከተዋዋሉት ያፈነገጠ ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ

- ይከተሉን -Social Media

አግባብነት የሌለው ጥያቄ ነው የተነሳው ብሎ የሚያምነው ግለሰብ ወደ ሕግ ማቅናት እንደሚችል እና በውላቸው መሠረት ተከራክሮ በሕግ አሸናፊ መሆን እንደሚቻልም ይገልፃል።
በተጨማሪ በትናንሽ ቤቶች ላይ በየወቅቱ አከራይ እና ተከራይን አገናኝተው የኮሚሽን ክፍያ ከመቀበል ባለፈ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማይኖራቸው ያስረዳል።

አከራዩ እና ተከራዩ መደበኛ ውል ከሌላቸው ተነጋግረው ሐሳባቸውን በመነጋገር መፍታት የሚችሉበት ሂደት ከሌለ እና ከአከራዮች በኩል ቤቱ እንዲከራይላቸው የሚመራ ጥያቄ ከመጣ ግን፣ ተከራይን ከማገናኘት ወደ ኋላ አንልም ብሏል።
ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ፣ በኮሚሽን ኤጀንትነት የመሬትና ንብረት ሻጭና ገዥን በማገናኘት በኩል ሕጋዊ ወይም ፍቃድ ያላቸው ደላሎች እንዳሉ ሁሉ፤ ንብረት እናሻሽጣለን፣ የቤት ሠራተኛና ቀጣሪ እናገናኛለን እንዲሁም የቤት ተከራይ እና አከራይ እናገናኛለን በማለት ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው የሚሠሩ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ በደላሎች በኩል ቤት ተከራይ እናገናኛለን በሚል የሚሠራው የድለላ ሥራ አሁን ላይ በመዲናዋ ለቤት መወደድም ሆነ ለኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ጫና አስከትሏል ብለዋል።
አንዳንድ ደላሎች ከቤት አከራዮች ጋር በሚፈጥሩት የጥቅም ግንኙነት ሳቢያ ሕግን መሰረት ባላደረገ መልኩ አንድ ተከራይ ቤት ከተከራየ በኋላ የቤት ኪራይ ጭማሬ እንደሚደረግበት ከመነገር ባለፈ ከፀጥታ ችግር ጋር በማያያዝ እና ምክንያት በማድረግ ተከራዮች እንዲለቁ የሚደረግበት ሂደት መኖሩንም ተናግረዋል።

አንዳንድ ደላሎችና የቤት አከራዮች በሚፈጥሩት ግንኙነት አከራዮች ላይ ከሚያሳድረው ተፅእኖ ጎን ለጎን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ስለሚፈጥር የኑሮ ውድነቱን እንደሚያንርም ባለሙያው ይገልፃሉ።
እንደዚህ ዓይነት ሕጉን የሚጥሱ ተግባራት ላይ መንግሥት በትኩረት መሥራት እንዳለበት እና ሕግ የሚጥሱ ደላሎች ላይ ተከታትሎ እና ከኅብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ ተንተርሶ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
ባለሙያው አክለውም፣ የአከራይ እና ተከራይ ግንኙነት በሕግ የተደገፈ፣ ጠንካራ የውል ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት በወረዳ እና በቀበሌ በኩል እንዲሠራ ማድረግ አለበት ባይ ናቸው።

በተጨማሪም፣ በየአካባቢው መንግሥት ባደራጀው በቀጠና ኮሚቴ በኩል አንድ አከራይ ቤቱን በሚያከራይበት ወቅት የውል ማስረጃውን ለቀበሌ እንዲያስገባ ከመቆጣጠር ባሻገር ያልተገባ፣ ጥቅም ለመሰብሰብ እና ኢኮኖሚው ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ደላሎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2001 መደበኛ ወይም ተቀጣሪ ሠራተኞች በግል የኢኮኖሚው ዘርፍ ውስጥ ሆነው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የሚተዳደሩበት ሲሆን፣ በመደበኛና በጊዜያዊነት ቅጥር ተብሎ በኹለት እንደሚከፈል ተናግረዋል።
ይህ ሕግ፣ ሕጉን የጠበቀ ውል ላላቸው የሚያገለግል ሲሆን፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን በተመለከተ ግን ራሱን የቻለ ሕግ አልወጣለትም ብለዋል።

የቤት ሠራተኞች በደላላ በኩል በአንድ ግለሰብ ቤት የሚቀጠሩበት እድል እንዳለ እና ሠራተኞች ከቀጣሪ ባለቤቶች ጋር ባለመስማማትም ሆነ በራሳቸው ፍላጎት አንድ ሳምንት እንዲሁም ከዚያ ባነሱ ቀናት ለቀው የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ ታዝቤአለሁ ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

የቤት ሠራተኞች በሚቀጥሯቸው ሰዎች የሥራ ጫና እና ጭቆና ስለሚፈጠርባቸው ለመልቀቅ እንደተገደዱ በምክንያትነት የሚያነሱ ሲሆን፣ በቀጣሪ አካላት በኩል እንዲሁ ያለምክንያት ሠራተኞቻቸው እንደሚለቁ እና በተደጋጋሚ አዲስ የቤት ሠራተኛ ለመቅጠር ደላሎች ጋር ለማምራት እንደተገደዱ ሲያነሱ እንደሚሰሙ ባለሙያው አውስተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በቀጣሪ አካላት በቤት ሠራተኞችም ሆነ በደላሎች በኩል ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ለሚታዩ ክፍተቶች ዋናው ችግር ራሱን የቻለ ሕግ አለመኖሩ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል። በተጨማሪ ደላሎች የሚፈጥሩት ሕግን የጣሰ አሠራር ለችግሩ መነሻ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ደላሎች አንድን የቤት ሠራተኛ በአንድ ግለሰብ ቤት እንድትቀጠር ካደረጉ እና ኮሚሽን ከተቀበሉ በኋላ ሠራተኛዋ ጋር በመነጋገር አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ከገባችበት ቤት በማስወጣት ከ50 እስከ 100 ብር አስጨምረው ሌሎች ሰዎች ዘንድ የሚያስቀጥሩበት ሁኔታ እንዳለ የሕግ ባለሙያው ገልፀዋል።

ከዚህ ባሻገር በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 አንቀፅ 55 ላይ በማንኛውም ተቋም በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት ተቀጥሮ ስለሚሠራ ሠራተኛ አነስተኛ የደመወዝ ክፍያ መጠን የሚያነሳ ሲሆን፣ ሠራተኞች የጉልበት ብዝበዛ ጋር በተያያዘ ጥያቄ መነሳቱን ተከትሎ የደመወዝ መጠን ይኑረው ተብሎ በሕግ ተደንግጎ እየተሠራ ነው።

በቤት ሠራተኛነት የሚቀጠሩ ሠራተኞች ራሱን የቻለ የደመወዝ መጠን አለመኖሩ ተጨማሪ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተጠቃሽ እንደሚሆን እና ጤናማ የሆነ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲሁም ጤናማ የሆነ የሥራ ግንኙነትን እያሻከረ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።
የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ ራሱን የቻለ የሕግ ሽፋን ባይኖር እንኳን በቀበሌ እና በወረዳ በኩል በቀጣሪዎችና በተቀጣሪ የቤት ሠራተኞች በኩል መደበኛ የሆነ ውል የሚፈራረሙበት ሂደት ቢኖር ችግሩን ለመቀነስ ያስችላል ባይ ናቸው።
አያይዘውም ራሱን የቻለ የደመወዝ መጠን በቀበሌ እና በወረዳ በሚገኙ የመንግሥት አካላት በኩል ቢወጣ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች