ንግድ ባንክ የሠራተኞቹን ደምወዝ በእጥፍ አሳደገ

0
629

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሐምሌ 2011 ባካሔደው ስብሰባ የባንኩ ሠራተኞች ለኹለት ዓመት ሲያቀርቡ የነበረውን የደምወዝ ጥያቄ በማጽደቅ ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ የሚታሰብ እስከመቶ በመቶ የደምወዝ ጭማሪ እንዲፈጸም ወሰነ።

በቦርዱ ውሳኔ መሠረትም የባንኩ የሰው ኃይል ክፍል ለሠራተኞቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ የደምወዝ ጭማሪውን ማፅደቁን የገለፀ ሲሆን፣ የጭማሪውን መጠንም በያዝነው ሳምንት በሚተላለፍ የውስጥ ማስታወሻ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ባንኩ ከ37 ሺሕ በላይ ከሚሆኑ ሠራተኞቹ ሲቀርብበት የነበረውን ይህንን የደምወዝ ጥያቄ ለመፍታት ባለፈው ዓመት የተለያዩ የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ የባንኩ ሠራተኞች ካለው የሥራ ጫና እና ከባንኩ አቅም ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንደሆነ ሲያማርሩ ቆይተዋል። ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ላይ በከተማ ለሚገኙ ሠራተኞቹ 15 በመቶ የኑሮ ውድነት ጭማሪ ያደረገ ሲሆን ከከተማ ውጪ ለሚገኙት ደግሞ የበረሃ አበል ላይ ተመሳሳይ ጭማሪ ማድረጉ ይታወሳል።

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎችም ወደ ሌሎች ባንኮች የተሻለ ክፍያ ፍለጋ በመፍለሳቸው ይህ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳስፈለገ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የንግድ ባንክ ደሞዝ ጭማሪ አዳዲስ ለሚመጡት ባንኮች ፈተና እንደሚሆን የሚናገሩት የባንክ እና ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዱልመናን ሞሐመድ፣ የደሞዝ እርከን መጨመሩ ወጪአቸውን ከፍ በማድረግ ጫና መፍጠሩ ስለማይቀር ቶሎ አትራፊ እንዳይሆኑ ሊያደርግ እንደሚችል ይናገራሉ። ጭማሪው የባንኩ ዓመታዊ ትርፍ አንድ ሦስተኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የባንኩን ወጪ በማናር የትርፍ መጠኑ ላይ የራሱ ጫና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

እንደ አብዱልመናን ገለጻ፣ ይህ ጭማሪ በግል ባንኮች ተመሳሳይ ጭማሬ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው። ይህ ደግሞ በባንኮቹ ትርፍ ላይ የሚያሳድረው ጫና ይኖራል። በአጭር ጊዜ ትርፋማ በመሆን የሚታወቁት የግል ባንኮች ከንግድ ባንክ ተፎካካሪ የሆነ ጭማሪ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ።

በተገባደደው የበጀት ዓመት 17.9 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያተረፈው ባንኩ ከአንድ ሺሕ 4 መቶ በላይ ቅርንጫፎች የከፈተ ሲሆን ከ37 ሺሕ በላይ ሠራተኞችም አሉት።

በበጀት ዓመቱ 89.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ገቢ ማድረጉን፣ የባንኩ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ከሆነው የግሉ ዘርፍ 67.9 ቢሊዮን ብር እንዳሰባሰበ ባንኩ አስታውቋል። የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችትም ወደ 541.2 ቢሊዮን ብር መሻገሩን እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድ ከወጪ ንግድ 268.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ሐዋላ 3.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ከብሔራዊ ባንክ የተላለፈ 2.1 ቢሊዮን ዶላር፣ በአጠቃላይ 6.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳስገባ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here