ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ዛሬ ማክሰኞ ከማለዳ ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን እና ከፊል የከተማው ክፍል ውስጥ ታጣቂዎች እንደሚታዩ ነዋሪዎች ገለፁ።
በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ ከተማ ውስጥ ታጣቂዎች ዛሬ ሰኔ 07 ቀን 2014 ከንጋት 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ተኩስ መክፈታቸው የተገለፀ ሲሆን፤ እስካሁን ጥቃቱን የሰነዘሩት ታጣቂዎች እነማን መሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።
በዚህም የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ታጣቂዎቹ መቆጣጠራቸውን ብሎም የጥቃቱ ኢላማ የርዕሰ መስተዳደሩን ጽህፈት ቤት ለመቆጣጠር ያለመ ሳይሆን እንደማይቀር የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ኹለት የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በዚሁ ክስተት ሳቢያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሥራዎች ብሎም ሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ ሲሆን ነዋሪዎችም በቤታቸው ዘግተው መቀመጣቸውን ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ አካባቢም ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ላለፉት አራት ሰዓታት እየተሰሙ እንደሚገኙ አንድ በአቅራቢያው ያሉ ነዋሪ አክለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡቦንግ በከተማዋ ስለተከሰተው የተኩስ ልውውጥና አሁን ስላለው ሁኔታ “ምንም የምንሰጠው መረጃ የለም’’ ሲሉ መግለፃቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አንድ የከተማው ነዋሪ ከባሮ ወንዝ ተሻግሮ ያለው የከተማው ክፍል በታጣቂዎች ቁጥጥር ስለሆነ ከባሮ ማዶ ተሻግረው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ከአራት ቀን በፊትም ተመሳሳይ ሙከራ ተደርጎ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ መጠን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ አይተን አናውቅም ነበር’’ ሲሉ ነዋሪው አክለዋል።
የጋምቤላ ክልል በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱባቸዋል ከሚባሉት ከምዕራብ ኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር ይዋሰናል።
በተለያዩ ጊዜያት ከጎረቤት አገር ሱዳን ዘልቀው የሚገቡ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።



