በትግራይ ክልል አምስት የክልሉ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ከብልጽግና ጋር አብራችኋል በሚል መታሰራቸው ተገለጸ

0
1257

ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ አምስት የክልሉ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ከብልጽግና ጋር አብራችኋል በሚል ለሳምንታት በእስር ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለፁት ጋዜጠኞች ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን፤ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ከባልደረቦቻቸው ሰመምቻለሁ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

ከታሰሩት ጋዜጠኞች አራቱ በእስር ላይ ለኹለት ሳምንታት ያህል ቢቆዩም እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣ አንደኛው ጋዜጠኛ ደግሞ ለ6ኛ ቀን በእስር ላይ ይገኛል።

ቢቢሲ በዘገባው ምንጮቹ አንድ የሂሳብ ባለሙያ እና አምስት የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን እንዳረጋገጡለት ገልጿል።

የታሰሩት ጋዜጠኞች ምስግና ሥዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ኃይለ ሚካኤል ገሠሠ፣ ተሾመ ጠማለው እና ዳዊት መኮንን መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው አረጋግጠዋል።

ሌላው በቁጥጥር ሥር የዋለው የፋይናንስ ባለሙያ ክፍሎም አፅብሃ እንደሚባልም ገልጸዋል።

የመቀለ ከተማ ዐቃቢ ሕግ አዲስ ገብረ ሥላሴ እንደተናገሩት፤ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው ሲሆን ጉዳያቸው በምርመራ ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጦር ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ተባብራችኋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባልደረቦቻቸው ገልጸዋል።

ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ምስገና ሥዩም እና ተሾመ ጠማለው ከቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆኑ፣ ሀበን ሀለፎም፣ ኃይለሚካኤል ገሠሠ እና ዳዊት መኮንን ቀደም ሲል ‘በግምገማ’ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር።

ከታሰሩትጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ሀበን ሀለፎ በትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር ሲቋቋም ከአንድ ሳምንት በላይ ታስሯል።

ከኅዳር 2013 መጨረሻ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የቴሌቭዥን ጣቢያው ዳግም ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲገኙ ጥሪ አቅርቦ ሥራውን ቀጥሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here