በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም በኃይል ዘርፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የቻይናው ኩባንያ ስቴት ግሪድ ኮርፖሬሽን በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተገለፀ። ኩባንያው ከገራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በቴክኖሎጂ እንዲሁም በዕውቀት ሽግግር ዘርፍ አብሮ ለመስራትም መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መለሰ ይመር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በመግባቢያ ሰነዱም ላይ ቻይናዊያን አስተማሪዎች ወደ ኮሌጁ በመምጣት ያካበቱትን ዕውቀት ለተማዎች በማካፈል ጠቃሚ ልምዶችን እንደሚያጋሩም ተጠቁሟል። መለሰ በዚህ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የሚደረገው ድጋፍ ቻይናዊያን አስተማሪዎችን ከማስመጣት ባሻገር ተማሪዎች እዛው ቻይና አገር ድረስ በመሔድ የሚሰለጥኑበትንም መንገድ እንደሚመቻች ጠቁመዋል። አያይዘውም ድጋፉ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ዕድል ለሚሰጣቸው ከሌሎች አፍሪካ አገራት ለተወጣጡ ተማሪዎችም ጭምር እንደሆነ ተገልጿል።
ስቴት ግሪድ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከኃይል ጋር በተያያዘ ግንባታዎችን እያካሔደ እና ግንብቶም ያስረከበ ኩባንያ ሲሆን ከዚህም መካከል በሆለታ የሚገኘው እና በትልቅነቱ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነውን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ (ሰብ ስቴሽን) መገንባቱን ለማወቅ ተችሏል። በቻይናው ስቴት ግሪድ ኩባንያ የተገነባው እና በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልቅነቱ እና በቴክኖሎጂ ስብጥሩ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የሆለታ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያ (ሰብ ስቴሽን) በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ስልጠና ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነም መለሰ ተናግረዋል። በሰብ ስቴሽኑም በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ሄደው የሚጎበኙበት ዕድልም እንደተመቻቸ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።



