የንፋሱ ፍልሚያ – የኢትዮጵያ ፊልም ከፍታ

0
1001

“በእውነተኛ ክስተት ላይ የተመሠረተ” ብሎ ይጀምራል፤ በአዲስ አበባ ያለውን የጎዳና ሕይወትን አሰቃቂና አሳዛኝ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። እንኳን ከውጪ ያለ በየእለቱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚመላለስ ሰው እንኳ ሊገምተው የማይችለው እውነት በዚህ ፊልም ቀርቧል። እንደዘበት ያለፍናቸው፣ ያላዳመጥናቸው፣ ልናምን የማንወዳቸው መራራ እውነቶች በየጎዳናችን ስለመጻፋቸውም ይህ ፊልም ያረዳናል። እንዲያም ሆኖ በማይታሰብና አስጨናቂ በሆነ ሰዓት ጸንቶ መቆም የቻለ ጓደኝነትና የቱንም የሕይወት መንገድ የሚያሳልፍ ህልም የዚህ ፊልም ክፍል ሆነው ታይተዋል።

በኢንግሊዘኛው Running Against the wind ወይም “የነፋሱ ፍልሚያ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው ይህ ፊልም፤ ኦስካር (አካዳሚ አዋርድ) ሽልማት ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ፤ አገራት አንድ ፊልም ብቻ ለውድድር በሚያቀርቡበት ምርጥ ዓለም ዐቀፍ ፊልም (Best International feature film) በሚለው ዘርፍ ለውድድር ተልኳል። አዲስ ማለዳም ከዚህ ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ጃን ፊሊፕ እንዲሁም ፕሮድዩሰር ከሆነቸው ወጣት ሳምራዊት ሲዒድ ጋር ቆይታ አድርጋ ነበር።
የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ጃን ፊሊፕ ዌይል ይባላል፤ ጀርመናዊ የ32 ዓመት ወጣት ነው። በፊልም ሥራ የቆየ ልምድ ያለው ሲሆን ለኢትዮጵያ ደግሞ ልዩ ፍቅር አለው። ፊልሙን ለመሥራት መነሻ ያደረገው ኹለት የ9 እና 10 ዓመት ልጆችን ሲሆን መኖሪያቸውም ገንዳ አብዲ የምትባል ከሐረር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አካባቢ ነው። ገንዳ አብዲ በሰዎች ለሰዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ትምህርት ቤትና መሠረተ ልማት የተሟላላት፤ በአካባቢው እግር የጣለው ካልሆነ በቀር ብዙ ሰው የማያውቃት ትንሽ መንደር ናት።

ታድያ ፊሊፕ ወደዚህች ከተማ በ2005 በድርጅቱ መሥራች ካርልሀይንስ በም ተጋብዞ ሲሔድ ነው ሕጻናቱን የተዋወቀው። በያዘው ዲጂታል ካሜራም እነዚህን ኹለት ልጆች ፎቶ ያነሳቸዋል። ቀጥሎም እንዲያሳያቸው ሲጠይቁትና ፎቶውን ሲያዩ የተመለከቱት የየራሳቸውን መልክ ሳይሆን አንዳቸው የሌላቸውን ነበር። የእነዚህ ትንንሽ ልጆች ሁናቴን በአእምሮው እያሰላሰለ የቆየው ጃን ፊሊፕ፤ አሁን ከበርካታ ዓመታት በኋላ የፊልሙ መነሻ አድርጓቸዋል። ገንዳ አብዲንም የፊልሙ አንድ መቼት አድርጓል።

ፊልሙ በዚህና መሰል 12 የሚሆኑ እውነተኛ ክስተቶች ላይ መሠረት ሲያደርግ የቀረው ግን የደራሲው የምናብ ፈጠራ የታከለበት መሆኑን ፊሊፕ ይገልጻል። በዚህ ፊልም ላይ ታድያ በርካታ አዳዲስ ተዋንያን ተሳትፈዋል፤ አንጋፋውና ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴም የፊልሙ አንድ አካል ነው። የፊልሙ ማጀቢያ ሙዚቃ (ስኮር) በአዲስ መልክ የተሠራ ሲሆን ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና ኬኒ አለን በዚህ ተሳትፈዋል።

ፊልሙ፤ የሰው ልጅ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢገኝ ህልም ሊኖረው እንደሚገባና ያንን ማሳካት እንዳለበት የሚያሳይ ነው። በዛም ላይ የሕይወትን ህልም የሚሰጠው የኑሮ ሁኔታ አይደለም ይላል፤ ፊልሙ። ለዚህም ጓደኝነት፣ ቃል፣ እምነትና ጽናት የታዩ ናቸው። በዛ መንገድ ያለፉ ሰዎችን አረዓያ አድርጎ መከተልም በፊልሙ የተላለፈ መልዕክት ነው።

የንፋሱ ፍልሚያ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ 65 የፊልም ባለሙያዎች አሻራ አለበት፤ ሁሉም ለኢትዮጵያ መልካም ስሜት ያላቸው መሆናቸውን ፊሊፕ አጠንክሮ ይገልጻል። ከምንም በላይ ደግሞ የተለያየና ቀላል የማይባል ልምድ ያላቸው መሆናቸውም ለፊልሙ ግብዓት መሆኑን ነው ያነሳው።

በፊልም ሥራው ሒደት የተዋናይ መረጣ ዋናውና አንደኛው ክፍል ሲሆን፤ ይህም ከ2014 የጀመረ ነው፤ እንደ ፊሊፕ ገለጻ። መጀመሪያ አራት ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች፤ ጎዳና ላይ ከሚኖሩ ልጆች ጀምሮ አትሌቶችም በተዋናይ መረጣ ላይ አልተዘነጉም። ይህም ቁጥር ወደ 600 ቀጥሎ ወደ 250 ወርዶ በመጨረሻ በዋናነት የሚተውኑ ሦስት ተዋንያን ከዛ ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ፊልሙንም ይህ ጥንቃቄ የተሞላው የተዋናይ መረጣ ለእውነት የቀረበ እንዲሆን አድርጎታል።

ከፊልም ቀረጻ በፊት ለወራት በአምስት ኪሎ አርት ስኩል ጊቢ የተደረገው ልምምድ ጠንካራ እንደነበር ያስታወሰው ፊሊፕ፤ ተዋንያን ‘ኢምፕሮቫይዝ’ እንዳያደርጉና በተጻፈው የፊልም ጽሑፍ መሠረት ብቻ እንዲሔዱ ለማድረግም ልምምድ ሰፊ ጊዜ እንደተሰጠው ነው ያነሳው። በተረፈ ከብዙ ተወዳዳሪዎች መካከል ተለይተው ሊወጡ የቻሉት ተዋንያን ጠንካራ በሆነ ፍላጎትና ተነሳሽነት ይሠሩ ስለነበር የቀረጻው ጊዜም እጅግ መልካም እንደነበር ፊሊፕ መለስ ብሎ ያስታውሳል።

ፊሊፕ ከዚህ የፊልም ፕሮጀክት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ ኹለት ፊልም የሠሩ ያህል ይቆጠራል ሲል ይገልጻል። መጀመሪያ የተዋናይ መረጣውና ልምምድ አልቆ ቀረጻ እስኪጀመር ያለፉት 11 ወራት ናቸው። በኋላም የፊልሙ መቼት ከሆነው መካከል በገንዳ አብዲ በነበረው ቀረጻ እንደተጀመረ የክረምት ወቅት በመግባቱ ቀረጻ ተቋርጧል። ይህም ሲያልፍ ተዋንያን እንደ አዲስ ተጠርተው ዳግም ሥራው ተጀመረ። ይህም ጊዜ የፊልሙን ሥራ ተሳታፊ አባላት ቁጥር እንደጨመረ፤ እርስ በእርስ ግንኙነትና ጓደኝነቱንም እንዳጠናከረ ፊሊፕ ያስታውሳል።

የፊልሙ ፕሮድዩሰር የሆነችው ሳምራዊት ሰዒድ ለፊልም ሥራ እንግዳ አይደለችም። ‘አዱኛ’ በተሰኘው ፊልም የፕሮዳክሽን ማናጀር በመሆን ሠርታለች። በዚህም ፊልም ላይ ሴቶች በብዛት የማይገኙበትን ፕሮድዩሰርነት ያለፍርሀት ተሳትፋበታለች። የንፋሱ ፍልሚያ ቀረጻን በተመለከተ ታድያ ፈታኝ ነገሮች እንደነበሩ ሳታስታውስ አልቀረችም። በተለይም በቀረጻው ወቅት አገሪቱ በኮማንድ ፖስት ስር የነበረች መሆኑ ፈትኖናል ትላለች። ታድያ ይሠሩት የነበረው ፊልም ገና ተመልካች ጋር ሳይደርስ የጽናት ምሳሌና አረዓያ መሆን የጀመረው ለራሳቸው ፊልም ሠሪዎቹ ነበርና ፈተናዎችን ሊጋፈጡ ችለዋል።

ከዛም ባለፈ በገንዳ አብዲ የጎሳ ግጭት የነበረ መሆኑ ከቀረጻ በፊት እሱን ማረጋጋትም በፊልም ሠሪዎቹ የተጣለ ሥራ ሆኖ ነበር። እንዲሁም በአገራችን ፊልሞች እምብዛም ያልተለመዱ ትዕይንቶች በፊልሙ መካተታቸው ቀረጻው በቀላል የታለፈ እንዳልነበረ ይመሰክራሉ። እነዚህን ትዕይንቶች ምናልባት ተመልካች በራሱ አይቶ ቢዳኛቸው መልካም ነውና ይቆየን።

ከፊልም ሥራው በፊትስ? ሳምራዊት ከፊሊፕ ጋር የተገናኘችውና ለዚህ ፊልም ፕሮድዩሰርነት ዕድሉን ያገኘችው በጀርመን በርሊን በተካሔደ የፊልም ፌስቲቫል ተሳትፋ በነበረ ወቅት ነው። ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ይህ ሲሆን ጀርመናዊው ፊሊፕ ሊሠራው ስለሚፈልገው ፊልምና እየሠራ ስላለው ፕሮጀክት ከሰዎች ሰምታ ነው የተዋወቀችው። ታድያ የፊልሙን ታሪክና ፊሊፕም ለፊልም ቅድመ ጥናት በማድረግ ያሳለፈውን ሁሉ፤ አልፎም በፊልም ሥራ ያለውን ልምድ ስታይ ቡድኑን ተቀላቀለች፤ ለፕሮድዩሰርነትም ራሷን አዘጋጀች። እንደምታስታውሰው ፊልሙ ወደ ቀረጻ ከመግባቱ በፊት ቀደም ያለ የሰባት ዓመት ቆይታ ነበረው፤ በደራሲው ሐሳብና እቅድ ሲብላላ።

የኦስካር ሽልማት ተሳትፎ እንዴት?
ደራሲና ዳይሬክተሩ ጀርመናዊ የሆነው፤ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ የተሳተፉበትና የሌሎች አገራት ፊልም ባለሙያዎችም እውቀትና ልምዳቸውን ያሳረፉበት “የንፈሱ ፍልሚያ” ከአምስት ወራት በኋላ በሚካሔደው የኦስካር ሽልማት ላይ ልናየው ተስፋ አድርገን እንጠብቃለን። እያንዳንዱ አገር አንድ ፊልም በሚልክበት በዚህ የፊልም ውድድር ላይ አሸናፊነት ከተገኘ፤ የፊልሙ ባለሙያዎችና ሠሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የበለጠ ሥሟ ደምቆ የሚነሳው ኢትዮጵያ ናት፤ ለኢትዮጵያ ፊልም ዘርፍም ከፍታ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም።

ፊልሙ መጀመሪያም ሲሠራ ይህን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ሳምራዊት ትናገራለች። ለዚህም ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ቀረጻው እንደተከናወነ አንስታለች። የተለያዩ አገራት የፊልም ባለሙያዎች እንዲሳተፉ የሆነውም በአንድ በኩል በቁሳቁስ ደረጃ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ለመሥራት በማስፈለጉ ነው።
ታድያ ፊልሙን ለኦስካር በማቅረብ ሒደት የመጀመሪያው ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር መነጋገር ነበር፤ ይህም መሥሪያ ቤተ በቋሚነት ሲሠራው የቆየ ባለመሆኑ ወደ ሒደት ለመግባት ጊዜ ወስዷል። አሁን ላይ በሚኒስትርነት እያለገሉ ባሉት ሒሩት ካሳ (ዶ/ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመራርነት፤ የፊልም ሠሪዎቹ የሥራ እቅድ ወይም ፕሮፖዛል ገቢ ተደረገ፣ ፊልሙም ታይቶ አስተያየት ተሰጠበት።

ታድያ ይህ ፊልም ጥያቄውን እንዳቀረበ ፈቃዱን አላገኘም፤ ይልቁንም ለውድድር የሚመጡ ሌሎች ፊልሞች ካሉ እስኪመጡ ድረስ ተብሎ ለሦስት ወራት መጠበቅ ነበረባቸው። ጊዜው እንዳለፈም ፊልሙ ለኦስካር ውድድር ለመቅረብ ጥያቄ ያቀረበ ብቸኛ ፊልም በመሆኑ ሊላክ ችሏል።

በየዓመቱ በአገራችን አዳዲስ ፊልሞች ይሠራሉ፤ በእጅጉ በታሪካቸውና በጭብጣጨው የሚያስደምሙንም ከመሃል አይጠፉም። እነዚህ ፊልሞች ግን ይህን ዓይነት እድል ሲፈጥሩ፣ ሲያገኙ አልያም ሲፈጠርላቸው አናይም ወይም አንሰማም። ሳምራዊት እንደምትለው የፊልም ባለሙያው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን በማሰብ ደረጃውን ያሟላ ፊልም መሥራት ላይ ማተኮር አለበት። ይህም በፊልም ጭብጥ ብቻም ሳይሆን በፕሮዳክሽን ጥራትም የሚታይ በመሆኑ በዛም ላይ ችላ እንዳይባል ባይ ናት። ለፕሮዳክሽን አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውን ቢኖሩም አንዳንዴ በድፍረትና በተነሳሽት መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ ሐሳቧን አካፍላለች።

ከዚህ በተረፈ ደግሞ መንግሥትም እንደ ሌላው ዘርፍ ሁሉ ለፊልም ትኩረት እንዲሰጥ፤ የፊልም ዋጋና ጥቅምንም በመረዳት ተቋማት ቢንቀሳቀሱ ውጤታማ መሆን ይቻላል ባይ ናት። “ፊልም ቱሪዝም ጭምር ነው። አትሌቶች አገር እንደሚያስተዋውቁት ሁሉ ፊልምም ቱሪዝምን ወደ አገር ያመጣል፤ ድጋፍ ግን ያስፈልገዋል” ብላለች። ለዚህም ለካሜራና ለቁሳቁስ ቀረጥ ከመቀነስ ጀምሮ ድጋፍ ማድረጉም ይታሰብበት፤ የሳምራዊት መልዕክት ነው።

ስለፊልሙ ምን ተባለ?
“ፊልሙ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ባለፈው አንድ ወር ኢትዮጵያ አልነበርኩም፤ ስመጣ ወደ ቤቴ እንደመምጣት ነው የተሰማኝ። ፊልሙ ለዕይታ መብቃቱም ደስ የሚል ስሜትም አለው” ያለው ፊሊፕ፤ ከባሕልና ቱሪዝም ካገኘው መልካ ምላሽ ጀምሮ የተመለከቱትም ጥሩ አስተያየት እንደሰጡት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
“ፊልሙ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን እፈልግ ነበር፤ እንደዛም ነው። አንድ ፊልም በአገሩ ከተወደደ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሊወደድ ይችላል” ሲልም አክሏል። ይህም ጅማሬ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ የፊልሙ እንቅስቃሴ ላይ በዓመት ቢያንስ አንድ ፊልም በኦስካር ላይ እንድትልክ መንገድ የሚያሳይ ይሆናል ሲል ለዘርፉ የሚያመጣውን ጥቅምም ይገልጻል።

ፊሊፕ በበኩሉ “በዚህ ፊልም ለእኔ የምትታየኝን የእኔን ኢትዮጵያ አሳይቻለሁ ብዬ አስባለሁ” ይላል። በአንጻሩ በተለይ በማኅበራዊ ሚድያው በተለይም በፌስቡክ አስተያየት ሰጪዎች “ፊልሙ ኢትዮጵያን አይወክልም” ሲሉ ትችት አቅርበዋል። ይህንንም ለማለት መነሻ የሆነው አብዛኛው ምክንያት ፊልሙ ላይ የታዩ አንዳንድ ትዕይንቶች እንዲሁም የጎዳና ላይ ሕይወቱና የገጻ ባሕርያቱ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ አይደለም፤ ይህ ክፍላችን መታየት የለበትም የሚል ነው። በተጨማሪም ነጮች መሳተፋቸውና በፊልሙ ትርክት ውስጥ ድርሻቸው እነርሱን የበላይ የሚያደርግ ነው የሚል ዕይታም አለበት።

ከዚህ በተቃራኒ የቆሙም አሉ። የደርሶ መልስ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ደራሲና ዳይሬክተር መዓዛ ወርቁ በማኅበራዊ ገጿ “ቆሻሻችንን ብቻ አይደለም፤ ብርታታችንንም አይቷል” ስትል ስለፊልሙ ሐሳቧንና ዕይታዋን አጋርታለች። በዛም ላይ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ጎልታ የምትታወቅበትን አትሌቲክስ በፊልሙ ጎላ ብሎ መታየቱንም በጠንካራ ጎን አንስታለች። “የዓለም ፊልም ተመልካች ኢትዮጵያ ሲባል ግር እንዳይለው የሚያስታውሰውን ‘ብራንድ’ ሸጦታል” ስትል፤ አክላም “ፊልሙ ኢትዮጵያዊ ነው” ብላለች።

ፕሮድዩሰሯ ሳምራዊት ፊልሙን መጀመሪያ በጽሑፍ ስታይ ወድዳው ነው ቡድኑን ለመቀላቀልና በፕሮድዩሰርነት ለመሳተፍ የፈቀደቸው። ኢትዮጵያዊት ነችና እንዴት ይህ ገጽታችን የሚያሳይ ፊልም ላይ ተሳትፎ አደረግሽ የሚል ጥያቄ ከአዲስ ማለዳ ቀርቦላታል። እርሷ የንፋሱ ፍልሚያ ይቆየኝ ብላ ዓይኔን ገልጦልኛል ያለችውን “አዱኛ” የተሰኘውን ፊልም አነሳች። አዲስ አበባ አውቶብስ ተራ በተካሔደው የዚህ ፊልም ቀረጻ ሊታመን የማይችል የኑሮ ሁኔታና ገጽታ ማየቷንም ታስታውሳለች።
“አዲስ አበባ ተወልጄ ሳድግ አውቶብስ ተራ አካባቢውን እንጂ ውስጥ ለውስጥ ያለውን አላውቅም ነበር። ለቀረጻ በዛ አካባቢ ስንሔድና ውስጥ ለውስጡን ሳይ ‘ይሔ ሁሉ የእኔ ጉድ…የእኔ ታሪክ ነው?’ ብያለሁ። ያኔ ለእኔም ሌላ ሰው ቢነግኝ ውሽት ነው ልል የምችለው ነው” ስትል ትገልጻለች። መንገድ ላይ ማስቲሽ እየሳቡ ረሃብና ጥማቱን ለመርሳት፣ ማታም ብርዱን ለመቋቋም የሚታገሉትን ልጆች ተከትለን ኑሯቸውን ብናይ የሚታየው እውነት በጣም አሳዛኝ መሆኑን አያይዛ ትናገራለች።
ከዚህ ባሻገር ግን የትኛውም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሊሠራ ስለማይችል በአንድ ጎን መስተካከል የሚኖርባቸው ነገሮች እንደሚኖሩ ለሠሪውም እንደሚታይ ስታነሳ፤ በሌላ በኩል የትኛውም ፊልም እንደተመልካቹ ሊዳኝ የሚችል በመሆኑ የሚወደውም የማይወደውም ሊኖር ስለመቻሉ ትገልጻለች።

ፊሊፕ ስለፊልሙ ሲናገር፤ መጀመሪያም ግቡ መቶ በመቶ እውነተኛ ፊልም መሥራት ነበር ይላል። “እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ፊልም ነው መሥራት የምፈልገው። አሁን ራሴን እንደ ኢትዮጰያዊ ነው የምቆጥረው። የእነዛ ኹለት ልጆችን ሕይወት እውነት ለመረዳት ኢትዮጵያን ማወቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ።” ሲልም ቀድሞ ወደ ፊልም ሥራው ሳይገባ የሆነውን ለአዲስ ማለዳ አጫውቷታል። ታድያ “ሜትኸድ ራይቲንግ ዳይሬክቲንግ” ዘዴን ተጠቀምኩ አለ። ተዋንያን አንድን ገጸ ባሕሪ በሚገባ ለመረዳት ከታሪኩ እውነተኛ ባለቤቶች ጋር ጊዜ በማሳለፍ በተግባር እንደሚማሩ ሁሉ፤ ፊሊፕ ደግሞ ለመጻፍም ሆነ ዳይሬክት ለማድረግ ይህን ዘዴ ተጠቅሟል።
“የምጽፈውን ማወቅ አለብኝ፤ ዳይሬክት የማደርገውንም እንደዛው።” ያለው ፊሊፕ፤ ከዐሥር ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ለስድስት ሳምንት ጎዳና ላይ ቆይቷል። ቦሌ አካባቢ ቆሻሻ በማንሳት ሥራ ላይ ከተሠማሩ ልጆች ጋርም ያሳለፈውን ጊዜ ያስታውሳል። ያደረጉለትን እንክብካቤ፣ ቋንቋ እንዳስተማሩትም አስታውሶ በፈገግታ ይናገራል። ያም ብቻ አይደለም፤ ማራቶን ሩጫዎችን ሮጧል፤ እንጦጦም ልምምድ ያደርግ ነበር፤ ይህም ከኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር እንዲተዋወቅ አጋጣሚውን ፈጥሮለታል።

ፊሊፕ ደጋግሞ ይህን ሲል ነበር፤ “የትኛውም ፊልም አገሩ ውስጥ ካልተወደደ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሊወደድ አይችልም ብዬ አስባለሁ። መጀመሪያ አገራዊ ስኬት መኖር አለበት። እንደውጪ ዜጋ የኢትዮጵያን ፊልም ስሠራ በደንብ ኢትዮጵያዊ መሆን አለብኝ ብዬ ነው፤ አሁንም ሕይወቴ በዛው ውስጥ ነው። በዚህ ፊልም ኢትዮጵያን ለመወከል ስለተፈቀደልኝ ደስ ብሎኛል። ይዘን የምንሔደው የቡድን ሥራ እና የኢትዮጵያን ሥም ነው” ብሏል።

ጀርመናዊው ኢትዮጵያዊ ሰው – ጃን ፊሊፕ
“ከዚህ በኋላ እቅዴ በየዕለቱ ጠዋት ስነሳ ይህ ፊልም የበለጠ እንዲተዋወቅ ማድረግ ነው። ዋናው ግቤም ፊልሙን ኦስካር ላይ ማቅረብ ነው። ፌብሩዋሪ 10 ከሽልማቱ ማግስት ግን ቀጥሎ የምሠራውን ማሰብ እጀምራለሁ” ያለው ፊሊፕ ነው። ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ፊልም ይሥራ አይሥራ አሁን ምንም ያቀደው ነገር የለም፤ ነገር ግን ከኢትዮጵያዊነት ተዋድዶ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም። ታድያ ስለዚህ ሰው ጥቂት አለማለት አግባብ አይሆንም፤ አንባቢም በተወሰነ መልክ እንዲተዋወቀው ያስችል ከሆነ ለአዲስ ማለዳ ካካፈለው የተወሰኑትን እንጥቀስ።

ፊሊፕ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ገና የ18 ልጅ እያለ ነበር። የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሥራች የሆኑት በጎ አድራጊው ካርል ነበሩ ጥሪውን ያቀረቡለት። ከዛም በኋላ ወደ አገሩ ጀርመን ሲመለስ ከዕድሜ እኩዎቹ ጋር በመሆን ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን ሁሉ አሟጦ ተጠቀመ፤ በጀርመን በሚማርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀለል ያሉ ምግቦችን ከመሸጥ ጀምሮ የተለያዩ መዝናኛ ድግሶችን በማዘጋጀት ገቢ ማሰባሰቡን ከጓደኞቹ ጋር ተያያዙት። በዚህም መልክ የተሰበሰበውን 23 ሺሕ ዩሮ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ ላከ።

በተረፈ ከልጅነቱ ጀምሮ ፎቶ ያነሳ ነበር፤ ከእጁ የማትለየው ካሜሪውም ናት በእነዛ ኹለት ልጆች ምክንያት ለፊልሙ ታሪክ መጸነስ ምክንያት የሆነችው። ፊሊፕ ለፊልም ልዩ ፍላጎትና ፍቅር አለው፤ ችሎታም እንደዛው። ጉዳዩ ሁሉ ፊልም ብቻ እንደሆነም ይናገራል። መደበኛ ትምህርቱን በ2006 በአንትሮፖሎጂ ሲያጠናቅቅ ወደ ፊልም ትምህርት ቤት አቅንቷል፤ ወደ ሙኒክ የፊልም ትምህርት ተቋም። በፊልም ሙያ ሥልጠና ምስጉን በሆነችው ጀርመን ፊልም ተከፋፍሎ እንጂ እንደ አንድ መስክ ለብቻው የሚሰጥ ባለመሆኑ ፊሊፕ ስለ ፕሮድዩሰርነት ተምሯል። በተለያዩ በጀርመን በቀረቡ ፊልሞች ረዳት ዳይሬክተር ሆኖ መሥራት የጀመረው በኻያዎቹ

ዕድሜው መጀመሪያ ነው። ቀጥሎም በርካታ የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችንና አምስት አጫጭር ፊልሞችን ለዕይታ አቅርቧል።
ይህ ሰው ወደ ኢትዮጵያ አንዴ ከመጣ በኋላ ደጋግሞ መምጣቱን አልተወም፤ አሁንም ይህን ፊልም ሠርቷል። ራሱን ኢትዮጵያዊ ብሎ ይቆጥራል፤ ኢትዮጵያንም ይወዳል። በዚህ ፊልም የፊሊፕ ዓላማ አንድና አንድ ነው፤ ለኢትዮጵያ ፊልም ዘርፍ ማበርከት የሚፈልገው ብዙ አለና፤ እሱን ለማድረግ ኦስካርን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት፤ አበቃ!

ሙሉ ጊዜዋን ለፊልም ሥራ የሰጠችው የፊልሙ ፕሮድዩሰር ሳምራዊትም በበኩሏ፤ የፊልም ሥራ ሙያ እንጂ የቀለም ወይም የማንነት ጉዳይ አይደለም ትላለች። እናም ልምዳቸውን ሊያካፍሉ፣ ሊያግዙና በጎደለ ሊሞሉ የሚገኙ ሰዎች ጋር በትብብር መሥራት አስፈላጊ ነው፤ ከጎረቤት አገራትም ጋር ቢሆን ልምድ መለዋወጥ ይፈለግብናል ስትል ትገልጻለች። ከዚህ ተጋግዞ መሥራት ባለፈ ግን በኢትዮጵያ ልጆች በዚህ ጥንካሬና ጥራት የሚሠሩ ፊልሞች እንዲኖሩ ምኞቷ እንዲሁም እቅዷ እንደሆነ ጠቅሳች።
ፊሊፕ ደግሞ በሚያውቃቸው ኹለት ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች አመስግኗል፤ “አመሰግናለሁ፤ ገለቶማ” ሲል። ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ ዮሐንስ ጥላሁን፣ ይስማ ጽጌ በምስጋናው ጠቅሷል፤ አብረውት የሠሩትንም እንደዛው። “ያኔ መጀመሪያ ስመጣ አንድ ጀርመናዊ ብቻ ነበርኩ፤ በኋላ ፊልሙ ሲያልቅ የምፈልገው ኢትዮጵያን ማሳየት ነበር። ቀድሞ ስለኢትዮጵያ ስንሰማ ደሃ አገር መሆኗ ይነገራል፤ ስመጣ ግን ያንን አላየሁትም፤ የነገሩኝን ፈልጌ ነበር፤ አላገኘሁም። አዲሷ ኢትዮጵያ ለእኔ ይሔ ነች። ጠንካራውን ጎን ማየት ያስፈልጋል። ፊልሙ ለሕይወት ተስፋ የሚያሳይ ነው፤ እሺ የሚል። ኢትዮጵያ ስሆን የማየው ይህን ነው” ብሏል፤ ጃን ፊሊፕ።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here