ኢዜማ እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወዛገቡ

0
384

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይና በሌሎችም ሕጎች ላይ የፓርቲው የሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል በሚል እውነታ አዛብቶ የሚያቀርብ ንግግር ላይ ማስተካከያ መስጠቱን ተከትሎ ኢዜማ አርብ መስከረም 16 ምላሽ ሰጥቷል።

የኢዜማ አባል ወይንም ደጋፊ የሆኑ የሕግ ባለሙያዎች በምክክር መድረኮች ላይ ግብዓት ከመስጠት ባሻገር፣ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም እና ሕጎችን በማሻሻል ሒደቱ ገለልተኛ በሆነ መንገድ እና ዘላቂ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመስረት በሚያስችል መልኩ እየተካሔደ እንደሆነ በመግለጫው ገለጾ ባለሙያዎቹ ፓርቲያችንን እንዲያማክሩ ኀላፊነት የተሰጣቸው ምሁራን መሆናቸውን ገልጿል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅራዊ ፍትሕ መሪ ብርሀኑ ነጋ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ጣቢያ ‘ኢሳት በዚህ ሳምንት’ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቆይታም ለማስረዳት የሞከሩት ይህንኑ ነው ሲል ከምርጫ ቦርድ ለተሰጠው እርማት ምላሽ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር ለመንግሥት ወይንም ለማንኛውም አንድ አካል ብቻ የሚተው ተግባር እንዳልሆነ እንገነዘባለን ያለው ፓርቲው፣ ይህ ሽግግር ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለምንም አድሎ የሚሳተፍበት ዕድል ማግኘታቸው ዋነኛ ግብዓት መሆኑን እንረዳልን ሲል ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ከዚህም በላይ የሕጎችን ክፍተት በመመርመር እና የማሻሻያ ረቂቆችን በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩት የሥራ ቡድኞች ሆነ የህግ ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ አባላት እንዲሁም፣ ሪፎርም እየተደረጉ ያሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው እናምናለን ብሏል። ለእነዚህ መርሆች የኢዜማ ተመሰረተ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ፍፁም ተገዢ ናቸው ሲል መግለጫውን አጠቃልሏል።

ኢዜማ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስማው እና የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ጨምሮ የተቋቋመ ሲሆን ግንቦት 1-2/2011 ባካሔደው የመመስረቻ ጉባኤ ከመላው ኢትዮጵያ 312 ወረዳዎችን የወከሉ መሥራች አባላት በተገኙበት በይፋ የተቋቀቋመ ፓርቲ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዳላገኘ ይታወቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here