ከኢሕአዴግ እስከ ኢብፓ፡ አገራዊ አንድምታ

0
1103

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች ታሪክ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት አራት የብሔር ድርጅቶች ግንባር በመፍጠር ኢሕአዴግ በሚል ሥያሜ የሚንቀሳቀሰው ስብስብ ረጅም የግንባርነት ታሪክ አስመዝግቧል። ከአራቱ አባል ድርጅቶች ሦስቱን እንዲሁም ሌሎች አጋር የሚላቸውን አምስት ድርጅቶች ጨምሮ የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ በሚል የዳቦ ሥም በቅርቡ ብቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።

ለመሆኑ የእስካሁኑ የኢሕአዴግ ጉዞ ከጽንሰቱ ጀምሮ ምን ይመስላል? የውሕደቱ ሐሳብ ጅማሮና የእስካሁኑ አካሔድ እንዴት ይቃኛል? የውሕደቱስ ዘርፈ ብዙ አንድምታዎች ምንድን ናቸው? በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች አሰላለፍ ላይ ያለው ተጽዕኖስ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ መጻሕፍትን አገላብጦ፣ ፖለቲከኞችን አነጋግሮ እና ባለሙያዎችን አስተችቶ ይህንን የኢሕአዴግን ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት መለወጥ በተመለከተ የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ
በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) አማካኝነት ግንቦት 1981 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራስያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከተመሰረተ 30 ዓመታት አስቆጥሯል። ከግንቦት 20/1983 ጀምሮ ደግሞ ከፖለቲካ ግንባርነት አልፎ መንግሥት ሆኖ እየመራ ይገኛል።

የአራቱ ማለትም የሕወሓት፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ ግራ ዘመም (ሶሻሊስታዊ) የፖለቲካ መርህ ላይ አዘንብሎ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ቅኝት ሲመራ ቆይቷል። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነው “ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” ደግሞ አራቱን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እና ታዳጊ ተብለው በሚጠሩ ክልሎች በሚገኙ አጋር የፖለቲካ ኀይሎችን ሁሉ ተመሳስለው እንዲያስቡ አድርጎ በኢሕአዴግ ጥላ ሥር አቅፏቸው ቆይቷል።

የፖለቲካ ልኂቃን እንደሚሉት ኢሕአዴግ የብሔራዊ ፓርቲዎች ግንባር ሆኖ፣ ኢትዮጵያን በብሔረሰቦች የሚገልጽ፣ የብሔር ጭቆና አለ ብሎ የሚያምን እና ከመደብ ትግል ይልቅ የብሔር ነፃነት ላይ የሚያተኩር የብሔሮች ግንባር ነው። ለ27 ዓመታት በሕወሓት የበላይነት ሲመራ የነበረው የፓርቲው እንቅስቃሴ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በኦዴፓ የበላይነት እየተመራ ይገኛል የሚሉ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የኢትዮጵያን ፖለቲካ የእህት ድርጅቶች መቀያየር የታየበት ሲሉ ይተቹታል።
አሁን ግን በኢሕአዴግ ቤት የውሕደት እንቅስቃሴዎች በሰፊው እየተካሔዱ ነው። የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 4/2011 የሐረሪ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ ቤንሻጉል እና የጋምቤላን ወኪሎች ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት፣ “ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚነጋገሩበት፣ የሚወስኑበት፣ ድምጽ የሚሰጡበት፣… ኢሕአዴግ አንድ አገራዊ ውሕድ ፓርቲ ሆኖ ይወጣል” ብለው ነበር። ባለፈው ቅዳሜ፣ መስከረም 10 አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮቿ መስማቷን ዋቢ አድርጋ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ (አብፓ) በሚል ሥያሜ በመደመር ፍልስፍና ውሕድ ፓርቲ ሆኖ ብቅ ሊል እንደሆነ መዘገቧ ይታወሳል።
የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሳዳት ነሻን፣ ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውሕድ ፓርቲነት የመቀየር እሳቤው ያደረ እና የተፈፃሚነት ጉዳዩም የዘገየ ሐሳብ ሆኖ እንጂ ከተመከረበት ቆይቷል ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ኢሕአዴግ ወደ ውሕደት ለመምጣት በሐዋሳ በተካሄደው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ዘክሮ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ መገለጹም የሚታወስ ነው።

ሐሳቡ መቼና በማን ተነሳ?
ኢሕአዴግን ወደ ውህድ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ለመቀየር እንቅስቃሴ የተጀመረው በሕወሓት ክፍፍል ማግስት መሆኑ ይነገራል። ስለ ሒደቱ መጀመርም በሚያዝያ 1995 በወጣው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ ላይ ተዘግቧል። በወቅቱ ኢሕአዴግ የጠላቱን የኢትዮጵያን ሠራተኛ ፓርቲን (ኢሠፓ) አወቃቀር ለመኮረጅ በአማካሪነት የኢሠፓውን የርዕዮተ ዓለምና ድርጅታዊ መዋቅር ቁንጮ የነበሩትን ሽመልስ ማዘንጊያን ከእስር ፈትቶ በኮንትራት ማሠራት ጀምሮ እንደነበር መጋቢት 1996 በወጣው ጦቢያ መጽሔት ላይ ተዘግቦ ነበር። ሙሉ በሙሉ እውነተኛ እንደሆነ ማረጋገጥ ባይቻልም።

የቀድሞው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ” በተሰኘው መጻሕፋቸው (በ2006 ለንባብ የበቃው) እንደገለጹት፣ በእርግጥ በመለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው የሕወሓት ማዕከላዊ አመራር በዚያ ወቅት የግንባሩን ውሕደት የፈለገው በሕወሓት ክፍፍል ሳቢያ በትግራይ የነበረው ማኅበራዊ መሰረቱ እንደሳሳበት በማሰብ ወደ ሌሎች ክልሎች ለማስፋት አስቦ ስለነበር ነው የሚለው አንደኛው መላ ምት ነው። መለስ ራሳቸው በክፍፍሉ ወቅት በኹለት እግራቸው የቆሙት በኦሕዴድና ብአዴን ድጋፍ እንደነበር ኤርሚያስ ማስነበባቸው አይዘነጋም።

ያም ሆኖ የውሕደት አጀንዳው እንደገና በሌሎች አጋጣሚዎች በአለፍ ገደም መነሳቱ አልቀረም። ከምርጫው በኋላም በሌላ የኢሕአዴግ መድረክ ላይ በተፈራ ዋልዋ አማካኝነት በ2002 ሐዋሳ ላይ በመጠኑ ተቀንቅኗል። የድርጅቱ መሪዎች ጉዳዩ መሰረታዊ አለመሆኑን በመናገር አዳፍነውት እንዳላፉም መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ያወሳሉ።

ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና የተነሳው ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈት በኋላ የዛሬ አምስት ዓመት ጥር 2005 ባሕር ዳር ላይ በተካሔደው ጉባዔ ላይ የሕወሓት መሥራችና ከፍተኛ አመራር የነበሩ ሰው በድንገት “ድርጅታችን የሚዋሐደው መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ መሰንዘራቸው በኤርሚያስ መጽሐፍ ተጠቅሷል። መቼም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሠራር ቀደም ብሎ ያልተያዘና የበላይ አመራሩ ያልወሰነበት አጀንዳ በተለይም የድርጅቱ “የጡት አባት” መለስ በሌሉበት በድንገት መነሳቱ ለጉባዔተኞቹ ፈረንጆች “ቦምብ ሼል” (bomb shell) የሚሉት ዓይነት እንደሆነባቸው ኤርሚያስ ይናገራሉ። ስለሆነም የመድረኩ መሪዎች እንደ ድሮው ሁሉ “ይህን ጉዳይ በይደር እናቆየው” በማለት ለማዳፈን ተገደዱም ሲሉ አክለዋል።

ሳዳት በበኩላቸው ሐሳቡ በአንድ ጀምበር የተጠነሰሰ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ በድርጀቱ ሲብላላ ቆይቷል። የዘጠነኛውና የዐሥረኛው ጉባዔን ጨምሮ በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲነሳ የቆየ ሐሳብም ነው።

ነገር ግን ከግንባር ወደ ፓርቲ መሻገር ያስፈልጋል በሚል አፅንዖት ተሰጥቶ የተነሳው በ11ኛው መደበኛ ጉባዔ ላይ ነው። ታዲያ እስካሁን ለምን ዘገየ ተብለው የተጠየቁት ሳዳት፣ ጥያቄውን በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት ለመመለስ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል። ይኸው ጥናት በ2011 መጨረሻ ፍጸሜውን አግኝቶ ለውይይት ቀርቧል።
“ሁሉም የፓርቲ አባላት ሐሳቡን አንስተዋል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አራቱም ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አጋር ድርጅቶችም እኛም መካተት አለብን የሚል ጥያቄን ሲያርቡ ቆይተዋል” ብለዋል ኀላፊው።

ውሕደቱ እውን ሊሆን ይችላል?
ሐሳቡን “የምር ነው ወይስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍ ወለምታ?” ሲሉ በርካቶች መነጋጋሪያ አድርገውት ቆይተዋል ነበር። ሳዳት ነሻን፣ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ እሆናለሁ ማለቱ እውነት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

“ኢሕአዴግ በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ተመሥርቶ እንደ አንድ አገራዊ ፓርቲ እያገለገለ ነው” የሚሉት ሳዳት ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ ፕሮግራም ስላላቸው፣ በልማት፣ በዲሞክራሲና ሰላምን በማስፈን በጋራ ሲሠሩ በመቆየታቸው ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ላለመሸጋገር የሚያግዳቸው የለም ብለዋል።

የቀድሞው የኢሕዴን ታጋይ የነበሩት እና የሕግ ባለሙያው ቹቹ አለባቸው በአማራ ብሔራዊ ክልል ታትሞ ከሚሰራጨው በኩር ጋዜጣ ጋር መጋቢት 16/2011 ዕትም ላይ ባደረጉት ቆይታ፣ ከምኞት እና ከምናባዊነት የዘለለ ሊሆን እንደማይችል ጥርጣሬያቸውን ይገልፃሉ። ቹቹ እንደሚሉት የኢሕአዴግ መሰረት እና ማያያዣ የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጠፍቶ እህትማማች ወይም የግንባሩ ጥምረት ፓርቲዎች በግላቸው ከኢሕአዴግ በላይ ገነዋል። አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ሕወሓት በየራሳቸው ጐልብተው ኢሕአዴግ እንደ ግንባር ጉልበቱ ዝሏል የሚሉት ቹቹ፣ በአገሪቱ ዋና ከተማ ዙሪያ እንኳን ስምምነት በጠፋበት ሁኔታ ውሕደት ይኖራል ብሎ መጠበቅ የማይቻል መሆኑን ያሰምሩበታል።

ይሁንና ሳዳት ውሕደቱ የአራቱ አባል ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን አጋሮችን እንደሚያካትት በመጥቀስ የቹቹን ትችት ያጣጥሉታል። ኢሕአዴግ ከግንባር ወደ ወጥ ፓርቲነት መሸጋገር አለበት የሚል ጥያቄ ወደ ጉባዔም መጥቶ በተለይ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ አፅንዖት ተሰጥቶት አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር።

መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ግን በሳዳት ሐሳብ አይስማሙም። እህት ድርጅቶቹ በማንነት ፖለቲካ ላይ የተመሰረቱ እንደመሆናቸው በቀላሉ ውሕድ ፓርቲ ይመሰርታሉ ብሎ ማሰብ እንደማይታሰብ ነው የሚናገሩት። በአንድ ወቅት ተፈራ ዋልዋ ይሔንን አጀንዳ አንስቶ እየተጠና ነው የሚል መልስ ከበረከት ስምዖን እንደተሰጣቸው መረራ ተናግረው፣ ይህ ግን ከሙከራ ማለፍ አለመቻሉን በማውሳት፣ አሁንም ከፉከራ የዘለለ አይደለም ባይ ናቸው።

አባል ድርጅቶቹ ከተስማሙ ውሕደቱ ሊፈጸም እንደሚችል የሚናገሩት መረራ፣ ይሁን እንጂ እነሱ የሚሉትና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነት የተለያየ መሆኑን ያስረዳሉ። በሐሳብ የማይገናኙና የማይስማሙ ድርጅቶችን ማዋሐድ እንደሚከብድ በመናገር።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራር የሆኑት ግርማ ሰይፉ ግን በመራራ ሐሳብ አይስማሙም። ኢሕአዴግ ከውሕደት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ይናግራሉ። በቀጣዩ ምርጫ አጋር ድርጅቶቹን አጋር ናችሁ ቢላቸው አይሰሙትም የሚሉት ግርማ፣ ሁሉም በራሱ እንደቆመ እያሰበ በሚገኝበት ሰዓት አጋርነትን የሚፈልግ አለመኖሩን ያወሳሉ። ኢሕአዴግ ውሕደቱን ሲፈጽም አጋር የሚባሉት ድርጅቶች ከአጋርነት ወጥተው የእኩልነት መንፈስ እንዲሰማቸው ከተደረገ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ የመመስረቱ ሒደት ሊሳካ እንደሚችል ግርማ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ ሰንዝረዋል።

ሳዳት ሁሉም አባል ፓርቲዎች ወደ አንድ ፓርቲ ለመሸጋገር ከዚህ በፊት ባደረጉት ስምምነት መሠረት እየሔደ እንዳለም ገልፀው የግንባሩ አባላትንም ሕዝብንም በውይይት ለማሳተፍ ተሞክሯል። ይህም የሁሉንም ባለድርሻዎች ፍላጎት ያማከለ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የቀድሞው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራችና ከፍተኛ አመራር የነበሩትና አሁን ከቀጥተኛ ፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን ያገለሉት ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች አደረጃጀታቸው የብሔር በመሆኑ አግላይ ሆኖ በመቆየቱና የራሱን ብሔር ጥቅም ብቻ ለማስፈጸም በመንቀሳቀሱ ብዙ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት መሆኑን በማውሳት አሁን ኢሕአዴግ የጀመረው የውሕደት እንቅስቃሴ አግባብ መሆኑን ይናገራሉ። ሙሼ፣ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሲመሰረት እንደ አገር እንጂ እንደ ብሔር የሚሠራ ነገር ባለመኖሩ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ ጥቅሙን ያስረዳሉ።

የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ሊቀ መንበር አብርሃ ደስታ፣ እንደኔ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ቢሆን ጥሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ፣ እንዲጠራጠር ያደረገው የእነሱ መከፋፈል ነው የሚሉት አብረሃ፣ ስለዚህ አንድ መሆኑ ለአገሪቱ ጥሩ ነው። ምንም እንኳን ኢሕአዴግ የኛ ተፎካካሪ ቢሆንም፣ አገር እንዳትከፋፈል የፓርቲውን አንድ መሆን እንሻለን ሲሉ ገልጸዋል።

የውሕደቱ ሥጋቶች
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ከመሆኗ ጋር ተዛምዶ በተለይም ኢትዮጵያዊነት በግንባር ሊቀ መንበር ጎልቶ በሚቀነቀንበት ወቅት የውሕደት ሐሳቡ ወደ ፊት መምጣቱ ለአንዳንዶች በብሔር አደረጃጀትና በፌዴራሊዝም ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሆኖ ታይቷቸዋል።

ፓርቲዎቹ በብሔር የተደራጁና ሥማቸውም ብሔርን የሚወክሉ በመሆናቸው ኢሕአዴግ ይዋሐዳል ሲባል ፓርቲዎቹ የነበራቸውን አጠቃላይ የብሔር ምንነትን ያጣሉ የሚል ሥጋት መፍጠሩም አልቀረም።

ሳዳት ግን “ሁሉም የጋራ አስተዋፅዖ የሚያደርጉበት እንዲሆን የታሰበ እንጂ ኢሕአዴግ በፌደራል ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ለውጥ የለም፤ ግምባሩን ወደ አንድ ፓርቲ ማምጣት ማለት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ይመጣል ከሚለው ሐሳብ ጋር አይገናኝም” ሲሉ ትችቱን አጣጥለውታል። የኢሕአዴግ ውሕደት በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን በጉባዔው ወስኖ ወጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኢሕአዴግ ውሕደት አይቀሬነት ደጋግመው መናገራቸው የሰጡትን አጽንዖት ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው። በተቃራኒው የኢሕአዴግ መስራቹ ሕወሓት ውሕደት ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለንም ሲል አቋሙን ይፋ ማድረጉ አሉታዊ ጫና ሊያሳርፍ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል።

መስከረም 14/2012 ከቢቢሲ አማርኛ ድህረ ገጽ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህወሓትና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፣ “በየእለቱ እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚውሉት አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር እርስ በእርሱ በሚጋጩበት ሁኔታ ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ህወሓት አያምንም” ብለዋል።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፍሰሐ ሐፍተ ጽዮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “ወደ ውሕደት ከመኬዱ በፊት ብዙ የቤት ሥራዎች መሠራት ይኖርበታል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ቢያንስ በዋና ዋና የፓርቲው ምሰሶዎች በሆኑት፤ የሕገ መንግሥት፣ የልማት ሁኔታዎች ላይ ተመሳሳይ አሊያም እጅግ ተቀራራቢ አረዳድ መኖር አለበት፤ እነዚህ ሳይሟሉ ወደ ውሕደት ለመሔድ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚመለከትም በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት እንደሌለ የአደባባይ ምስጢር ነው በማለትም ያስረዳሉ።

“የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላት ተቀራራቢ ወይም አንድ ዓይነት አቋም እንደሌላቸው ግልፅ ነው፤ ራሳቸውም በተለያየ ጊዜ የሚናገሩት ይህንኑ ነው” የሚሉት ፍሰሐ፣ ግንባሩም እንደ ግንባር ተቀራራቢ አቋም ሳይኖረው አንዳንዶቹ የግንባሩ ፓርቲዎች ከፍተኛ የሆነ የጎራ መደበላለቅ እያለ ‘እንዋሐድ’ ስለመባሉ ያላቸው ሐሳብ አዎንታዊ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 3/2011 ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ ሲያጠቃልል ባወጣው መግለጫ ላይ “…ኢሕአዴግ ጀምሮት የነበረውና ተኮላሽቶ የቀረው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመለስ ከማድረግ ይልቅ፣ በቅርብ ጊዜያት አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ ተብሎ እየቀረበ ያለው ጉዳይ፣ ኢሕአዴግ በማዋሐድ አንደ አገራዊ ፓርቲ ማድረግ የሚል ነው። በመሠረቱ የፓርቲ ውሕደት ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳ የነበረና በጥናት እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ግልፅ ነው። ይህ አቅጣጫ የተቀመጠው ደግሞ ኢሕአዴግ ጤናማ በነበረበት ወቅት፣ በመሠረታዊ የድርጅቱ እምነቶችና መስመር ላይ ፅኑ እምነት በነበረበት እና ምንም መሸራረፎች ባልነበረበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ የደፈረሰና ጉራማይሌ አመለካከትና እምነት የያዘ ኢሕአዴግ፣ አይደለም ለውሕደት ከዚህ ቀደም ለነበረው አደረጃጀቱም የሚሆን የአስተሳሰብና ተግባር አንድነት የሌለው ኢሕአዴግ ነው ያለው። በሁሉም መሠረታዊ ጥያቄዎች የፕሮግራም፣ ስትራቴጂ፣ መለያ እምነቶች በእህት ድርጅቶች መካከል አንድ የሚያደርግ አመለካከትና እምነት በሌለበት፣ ሁሉም ወደ ተለያየ አቅጣጫዎች በሚላጋበት ውሕድ አንድ ፓርቲ ሊታሰብ የሚችል አይደለም” ብሏል።

ውሕደቱ ፈጥኗል ወይስ ዘግይቷል?
የውሕደቱ ጊዜ ፈጥኗል በሚለው ሐሳብ የማይስማሙት ግርማ ሰይፉ፣ ኢሕአዴግ በሕይወት ለመቀጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ ውሕደቱ መሆኑን ተናግረው፣ በቀጣዩም ምርጫ አጋር ድርጅቶቹን አጋር አድርጎ ለምርጫ መቅረብ ስለማይችል መዋሐዱ ብቸኛ አማራጭ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ሙሼም በግርማ ሐሳብ ይስማማሉ። በብሔር ተደራጅቶ አገርን መምራት የሚያመጣውን ችግር ባለፉት 27 ዓመታት ውጤታማ ሆነው አለመታየታቸው ለዚህ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ እንደውም ዘግይቷል ብለዋል።

ቹቹ ቀደም ብሎ ከተጠቀሰው በኩር ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቆይታ እነ ሙሼ ከሚሉት ከሰነዘሩት ሐሳብ ጋር አይስማማም። ቹቹ በተለይ እንደ አማራ እና አማራውን እንደሚመራው አዴፓ በአጭር ጊዜ ውሕደት የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ከሆነ ግን ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ።

የኢሕአዴግ ግንባሮች ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ የዘውግ ብሔርተኝነትን አቀንቅነው የእኔ የሚሉትን ሕዝብ ችግር ለመፍታት ታግለዋል። በአንጻሩ የአማራ ብሔርተኝነት ለጋ በመሆኑ የእኔ የሚላቸው ጥያቄዎች ገና አልተፈቱም። መፈታት የሚችሉት ደግሞ በዳበረ ብሔርተኝነት እና የክልሉ መንግሥት መጐልበት ሲችል ነው። ውሕደት ከኖረ ግን የአማራ ጥያቄ በውሕደቱ ተዳፍኖ ሊቀር ይችላል ይላሉ ቹቹ።

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዳንኤል ሕገ መንግሥቱ ክልሎችን ሉዓላዊ ሥልጣን ሰጥቷል። ወደ ውሕደት ከመጣ ግን የብሔራዊ ክልሎች ሉዓላዊነት ወደ አገራዊ ሉዓላዊነት ስለሚለወጥ አንድ አማራ ኦሮሚያን፣ ሌላው ኦሮሞም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር ይችላል። ይህ ግን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መብት ለብሔራዊ ክልሎች የተሰጠ ነውና ሲሉ ያስረዳሉ። ከዚህም በላይ አገሪቱ አሁን ከገባችበት የብሔር ፖለቲካ ንብረት አንጻር ሲታይ ሁኔታውን ቀላል የሚያደርገው አይመስልም። ስለዚህ ከውሕደቱ በፊት በሰከነ መንፈስ መታየት ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ ባይ ናቸው።

የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ይኖር ይሆን?
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዳንኤል፣ “ኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለሙን ይመስላል” ይላሉ። ኢሕአዴግ የብሔር ጭቆና ነበር ብሎ የሚያምን ድርጅት ሆኖ 27 ዓመት ቀጥሎ ነበር የሚሉት ዳንኤል፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኦዴፓ በኩል የመደብ ጭቆና ወደሚል የዞረ ሲሆን፤ በአዴፓ በኩል ደግሞ አማራ ጨቋኝ መደብ ተደርጐ የታሰበው እሳቤ እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል። በዚህም የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች ከትናንቱ ጋር የተለያየ አሰላለፍ ላይ ናቸው። በዚህ የተለያየ ዕውነት ውስጥ ሆኖ የሚደረግ ውሕደት መዘዙ ብዙ መሆኑንም ያክላሉ።

እንደ ዳንኤል ገለጻ፣ ከርዕዮተ ዓለሙ ባሻገር አሁን ባለው የኢሕአዴግ ለውጥ ላይም ድርጅቶቹ የጋራ አተያይ የላቸውም፤ ሕወሓት አሁን ያለውን ሁኔታ ለውጥ ነው ብሎ እንደማይቀበለው አዝማሚያው አመላካች ነው፤ አዴፓ እና ኦዴፓም በለውጡ ቢያምኑም በለውጡ አካሔድ ላይ ግን በተቃርኖ የቆሙ ናቸው።
በሌላ በኩል ሕወሓት እና ከፊል የኦዴፓ አመራሮች በፌዴራሊዝም ስርዓቱ አንደራደርም ሲሉ፣ አዴፓ ደግሞ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎቹ እንዲፈቱ የፌዴራሊዝሙ አሠራር እና አተገባበር እንዲሻሻል ይሻል። በሌላ በኩል በኦዴፓ በኩል የሚነሱት የአዲስ አበባ ጥያቄ እና የአፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ ይሁንልኝ ጥያቄ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ካልተደረገ በቀር ሊፈታ አይችልም እንደ ቹቹ ገለጻ።

በዋና ከተማዋ ህልውና ላይ ሳይቀር፣ በታሪክ አረዳድ እና በፌዴራሊዝሙ አመሰራረት ሳይቀር በተቃርኖ የተሰለፉ ፓርቲዎች ከግንባርነት ወደ ውህድነት የመቀየር ተስፋ አይኖራቸውም፤ ቢኖራቸው እንኳን ለቀውስ ይዳረጋሉ ይላሉ ዳንኤል።

የኢሕአዴግን ውሕደት ከመሥራች ድርጅቶቹ ባሕሪይ አንጻር ተንተርሶ መመልከቱም ጠቃሚ ይሆናል፤ ኢሕአዴግ አንድ ወጥ ውሑድ ፓርቲ ሲሆን መሥራች ፓርቲዎቹ የሚኖራቸው ህልውና ምን ሊሆን እንደሚችል ስንመለከት፣ የኦሮሞን የዘውግ ፖለቲካ እና ብሔርተኝነት የፈጠረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የትግል አድማሱ ኦሮሞ እና ኦሮሞ ብቻ የሚል ነበር የሚሉት ቹቹ፣ የአሁኑ የከፊሉ ኦዴፓ ፖለቲካ ደግሞ ኦነግ ከተከተለው መንገድ በተቃርኖ የቆመ ነው።

ኦዴፓ ኢትዮጵያዊነትን ከኦነግ በተሻለ በማቀንቀን የመጠቅለል እና የወከለውን ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የተሻለ ለመጥቀም የሚፈልግ ይመስላል። ኦዴፓ ውሕደቱ ከተሳካ የመጠቅለል ሚና ሊኖረው ይችላል ይላሉ፤ ዳንኤል። ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ ውሕደት የብሔር ፌዴራሊዝሙን ቅርጽ እንደማይቀይረው እና ወደ አሃዳዊ አስተዳደር እንደማያመራ ግንባሩ በተለያየ ጊዜ አሳውቋል።

በ56 ብሔሮች እና ሕዝቦች የተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ድርጅት ውሕደቱ ብሔረሰባዊ ዞኖች የክልል ጥያቄ እና ሽኩቻ እንዲቀርለት ደኢሕዴን ውሕደቱን ሊፈልገው ይችላል። በሌላ በኩል ሕወሓት አገራዊ ፓርቲነቱን ባይጠላውም፤ ቀድሞ ራሱ ባሰመረው ኢሕአዴጋዊ ፌዴራሊዚም ያገኛቸውን ጥቅሞች ላለማጣት መሃል ላይ ሊቆም ይችላል ሲሉ ቹቹ ያስረዳሉ።

ኢሕአዴግ በጨቋኝ እና በተጨቋኝነት የፖለቲካ ትርክት መሰረቱን ሲጥል የአማራን ሕዝብ በገዥ መደብ ሥም አግልሏል። በማግለሉም የኢኮኖሚ ድቀት ደርሶበታል የሚሉት ዳንኤል አማራ በብሔራዊ ማንነቱ ቁሞ የደረሰበትን የሰብኣዊ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መገለል ማስታረቅ አለበትም ይላሉ። በመሆኑም እነዚህ ያልታረቁ ሐሳቦች ባሉበት ሁኔታ ወደ ውሕደት መግባቱ አገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ መውሰድ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

ውሕደቱ የማይቀበሉት እህት ድርጅት/ቶች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
አሁን በገዢው ግንባር ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት ከውሕደቱ በፊት እንዲጠብ ካልተደረገ የኢሕአዴግ ዋነኛ አስኳል ሆኖ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው ሕወሓት በሚመሰረተው ውሕድ ፓርቲ ውስጥ የመዝለቁ ነገር አጠያያቂ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። አንዳንዶች ሕወሓት በልዩነት ሐሳቡ የሚገፋበት ከሆነ ከኢሕአዴግ የመፋታት ዕጣ ሊገጥመው ይችላል ይላሉ። በኢሕአዴግ ሕገ ደንብ መሠረት ሕወሓት በማንኛውም ጊዜ ከግንባሩ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል አለው። ወይንም በሌሎች አባል ፓርቲዎች ከግንባሩ እንዲወጣ ሊወስኑበት ይችላሉ። በአጭሩ ሕወሓት እንደ አንድ ፓርቲ መቀጠል የሚከለክለው አይኖርም። የተቀሩት ሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ማለትም አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ደኢሕዴን ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን በመያዝ ወደ ውሕደት ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል ዝግ አለመሆኑን ያነሳሉ። አባል ፓርቲዎቹ ከግልና ከፓርቲ ጥቅሞቻቸውና ፍላጎቶቻቸው በበለጠ የአገር ጥቅምን በማስቀደም በሰለጠነ መንገድ፣ በስምምነት አገሪቷን ከቀውስ ይታደጓታል የሚለው ግን የብዙዎች ተስፋ ሆኗል።

ሳዳት፤ “ፓርቲ ለመሆን ውሕደት ለመፍጠር የአባል ድርጅት ፍላጎት ይጠይቃል። መሠረታዊ ፍላጎት አለ ብለን እናስባለን። ጥናቱም ያረጋገጠው እሱን ነው። ይህ ከሌለ ግን ወደ ፓርቲም ሳንሸጋገር ከግንባርም መውጣት የሚፈልግ መውጣት ይችላል” ሲሉ በውሕደት የማይስማማ አባል ድርጅት መውሰድ የሚገባውን እርምጃ ጠቁመዋል።

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኀላፊ ፍቃዱ ተሰማ ለዚህ መልስ አላቸው። “ውሕደቱ ለሕዝብ የሚበጅ እንደመሆኑ በስምምነት የሚፈጸም ነው። እስካሁንም የመጣነው የትኛውም ድርጅት ቢሆን ሙሉ በሙሉ በስምምነት ነው። ከአጋሮች ጋርም በዛው አግባብ የሚካሔድ ነው። የሚታረምና የሚስተካከል ነገር ሲኖርም በውይይት ነው የሚሆነው። ያም ሆነ ይህ ግን ማንኛውም ድርጅት በውሕደቱ አግባብ ላይ ነጻ ፍላጎቱ የሚጠየቅ እንደመሆኑ፤ መዋሐድም ሆነ አለመዋሐድ መብቱ ነው። ስለዚህ ውሕደቱን ከልብ በሚቀበሉት ተግባራዊ ይሆናል” ብለዋል።

የውሕደቱ ሕጋዊ አንድምታ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ብሩክ ኀይሌ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በ2000 የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ “ውሕደት” ማለት “ኹለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በሕግ መሠረት ተመዝግበው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተዋሕደው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሁኔታ ነው” በማለት ይገልፀዋል።

ስለሆነም ስለ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውሕደት ስናነሳ ድርጅቶቹ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አፍርሰው፣ አርማዎቻውንና ማኅተሞቻቸውን ለምርጫ ቦርድ አስረክበው አባሎቻቸውን በቀጥታ የአዲሱ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ አባል ያደርጋሉ ማለት ነው።

ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የኢሕአዴግ አንድ ወጥ ፓርቲ መሆን ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አንድምታ ሊኖረው ይችል ይሆን?›› በማለት አንዳንዶች ሲገልጹ ይሰማል። በተለይ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የሚገኘው እና “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች. . .” ብሎ የሚጀምረው አገላለጽ አንድን ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ሳይሆን በብሔሩ በኩል እውቅና እንደሚሰጠው የሚገልጹም አሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)፣ ሕገ መንግስታዊ አንድምታ ቢኖረውም የጎላ እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች. . .” ብሎ የሚጀምረው አገላለጽ፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች›› በሚል ሊገለጽ እንደሚችል አውስተው፣ ይሁን እንጂ ውህደት የፈጠረው ፓርቲ የብሔር ብሔረሰቦችን ሥራ አይሰራም ማለት አይደለም፤ የክልሎችም ቅርጽ ላይቀየር ይችላል፡፡ ፓርቲው በክልሎች የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ይኖሩትና በዛ አማካኝነት ክልሎችን እንደሚመራ ይገልጻሉ፡፡

ሲሳይ እንደሚሉት፣ ውህደቱ የክልሎችን ምንነት አይቀይረውም፡፡ ምናልባት በሂደት ቅርጻቸው ሊቀየር ይችል ይሆናል እንጂ፡፡ ክልሎቹ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች አሏቸው፤ እነዛ ፓርቲዎች በክልሉ በምርጫ ካሸነፉ ክልሉን ይመራሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ኦነግ በኦሮሚያ ክልል፣ አብን በአማራ ክልል ካሸነፉ ክልሉን የሚመሩ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክልላዊ መዋቅሮቹ ባሉበት የሚቀጥሉ ነው የሚሆነው፡፡

በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዳንኤል መሰለ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ወደ ውሕደት ለመምጣት ሕገ መንግሥቱ ከብሔሮች ባሻገር ስለ ዜግነት እና ስለአገር እውቅና እንዲሰጥ መሻሻል ይገባዋል። በተጨማሪም ዳንኤል መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያም የተቀራረበ ስምምነት እና ፍትሐዊነት መኖር በቅድመ ሁኔታነት አስፈላጊ የመሆኑ ነገር አያጠያይቅም። ከዚህ አንጻር ከሕገ መንግሥት እስከ ዋና ከተማ ጉዳይ ያላሰማማቸው ድርጅቶች ይዋኻዳሉ ብሎ መጠበቅ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ይናገራሉ።

መፍትሔ
ፖለቲከኛው ሙሼ፣ የኢሕዴግን የውሕደት ሐሳብ በኹለት አንጓዎች ከፍለው ይመለከቱታል። በመጀመሪያ የኢሕአዴግ የውሕደት ሐሳብ ከአሻጥር የፀዳ ከሆነ የተበታተነውን የሕዝብ እሳቤ እና የደቀቀውን አገራዊ ዓላማ ለመመለስ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው። በክልል ደረጃ ያሉ ብሔራዊ ፓርቲዎች ከክልላዊ ቅንፋቸው ወጥተው ስለ ዜግነታቸው፣ ስለ አገራቸው እንዲያስቡ የኢሕአዴግ የመዋኸድ እሳቤ በር ይከፍታል ይላሉ። ውሕደቱ በብሔራዊ ክልሎች ሥልጣኑን አሳልፎ የሰጠው ማዕከላዊ መንግሥት የተሻለ ኀይል ይኖረዋል በማለት።

ውሕደቱ አገሪቱን ተብትቦ የያዘውን ችግር የሚፈታ መሆኑን የሚናገሩት ፖለቲከኛው፣ የብሔርን መብት ማክበር ግድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ገደብ ካልተበጀለት ደግሞ አገር የሚያፈርስ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ቹቹ ወደ ውሕደት ከመገባቱ በፊት መጀመሪያ በእህት ድርጅቶቹ መካከል መግባባት ሊኖር ይገባል ይላሉ። በውስጣቸው በርካታ ችግሮች እንዳለባቸው ስለሚታወቅ፣ ቀድመው ያንን የመፍታት ኀላፊነት እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here