ዜናው የማን ነው?

0
663

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በቅርቡ ያነበብኩት አንድ ጽሑፍ በ2010 የተደረገ ጥናትን ጠቅሶ በዓለም ከሚወጣው ዜና ውስጥ ሴቶች የተመለከተ 23 በመቶው ብቻ ነው ይላል። በአንጻሩ 76 በመቶ የዓለም ዜና የሚወራውና የሚሰማው ስለ ወንዶች ነው ማለት ነው። ይህ በገሀዱ ዓለም ያለውን የወንዶች የበላይነት ወይም በሌላ አባባል “የወንዶች ዓለም” የሚለውን እሳቤ እርግጥ የሚያደርግ ይመስላል።

በአንድ ጎን ይህ የእውነተኛውን የማኅበረሰብ አወቃቀር የሚያሳይ አይደለም የሚሉ አሉ። በምናውቀው በዓለም ላይ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ተመጣጣኝ እንደውም የሚበልጥ ነው። እናም ወደድንም ጠላንም በቁጥር የሚበዙ የበለጠ ድምጽ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃልና።

ይህ ከሆነ ችግሩ ያለው መገናኛ ብዙኀን፣ የዜና አውታሮች፣ ዘጋቢዎችና ዘገባዎች ላይ ነው ማለት ነው። ስለ ሴቶች ጉዳይ ዜናዎች አይሠሩም፤ አልያም ዜናዎች የሉም ተብሎ ይታሰባል እንዲሁም ለዜና እንደማይበቁ ይቆጠራል። በሌላ በኩል ደግሞ ዜናው በሚሠራበት መስክ ላይ ዘጋቢዎች ጥያቄ የሚያቀርቡት ለሴት ባለሙያዎች ሳይሆን ለወንዶቹ ነው። እዚህ ላይ የተናጋሪ ፈቃደኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ ማለት ነው።

የተናጋሪ ፈቃደኝነት ምንድን ነው? ለተለያዩ ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እውቀትና ልምድ ያላቸው ሴቶች አስተያየት ለመስጠት ሲጠየቁ ምን ያህል አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው የሚለው ነው፤ ብዙ ጊዜ ስለማይሆኑ። በእርግጠኝነት ብዙ ዘጋቢዎች ከሴቶች አስተያየት ለመቀበል ይቸገራሉ፤ እኔም በሥራ አጋጣሚ የምመለከተው ስለሆነ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታድያ በአንድ ሳምንት በወጡ ዜናዎች ላይ የስንት ሴቶች ድምጽ ገብቷል፣ ስንት ዜናዎች ወይም ዘገባዎች ስለሴቶች ተሠርተዋል የሚለውን ብናይ ምንም የማናገኝበት ሳምንት ሊኖር እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ከዛው ንባብ ላይ እንዳገኘሁት ታድያ በዜና ዘገባዎች ላይ ሴቶች ሽፋን ያገኙ ጊዜ እንደ ባለሙያ ወይም እንደ ቃል አቀባይ በውስን መንገድ ቢሳተፉ ነው።

በጽሑፉ መሠረት ጥናቱ እንዲህ ይላል፤ በ2010 በዓለም ዙሪያ ባሉ መገናኛ ብዙኀን ከተሠሩ ዘገባዎች ውስጥ 19 በመቶው ቃል አቀባይ፤ 20 በመቶው ደግሞ ሙያዊ አስተያየት ሰጪ የነበሩት ሴቶች ነበሩ። በአንጻሩ በመቶኛ ስሌት የወንዶቹ ምን ያህል እንደሚልቅ ሒሳቡን ማስላት ነው። ሴቶች እንደ መንገደኛ አስተያየት ሰጪዎች የሚሳተፉበት ጊዜ እንኳን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

እዚህ ላይ አንድ ነገር በእርግጥ ማለት ይቻላል፤ ዓለም የሴቶች ዕይታ አምልጧታል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኹለቱም ወገን የተሠራ ጥፋት ነው። ቀዳሚው መገናኛ ብዙኀን ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ምን ያህል ይሠራሉ የሚለው ነው። ይሔ የሴቶችን ድምጽ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውን መናገርንም ያካተተ ነው።

አካታችነትም እዚሁ ላይ ይነሳል፤ መገናኛ ብዙኀን ለሴቶች ብቻም ሳይሆን ለሕጻናትም ጭምር ምን ያህል የአየር ሰዓት፣ የስርጭት ቆይታ፣ የጋዜጣ ገጽ ሰጥተዋል።
ሌላው ደግሞ የሚመለከታቸው የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ራሳቸው ሴቶች ናቸው። ከላይ እንደተባለው በፈቃደኝነት አስተያየት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ሴቶች ናቸው፤ በየሙያው የተማሩና ብቁ የሆኑ ሴቶች ሳይጠፉ ለመውጣትና ሐሳባቸው ተጽዕኖ እንዲፈጥር ለማድረግ ግን ሲተጉ አይታዩም፤ ፈቃደኛም አይሆኑም። አቅማቸውን በጓዳ ስለሚያደርጉት በእነርሱ መንገድ ሌሎች እንዲሔዱ አረዓያ በመሆን በኩል ራሳቸውን ይሸሸጋል።

ተቋማትስ? በሴቶችን በሕጻናት ላይ የሚሠሩ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ ያሉት ሁሉ፤ የሰው ልጆች መብቶችና ተጠቃሚነት ላይ እንደሚሠሩ ተቋማት ተገቢውን ሽፋን አያገኙም፤ አስፈላጊው ድምጽም አያወጡም። አዲስ ነገር ስለማይሠሩ ከሆነ አናውቅም እንጂ አዲስ ነገርም በቶሎ አያቀብሉም። ይህም ሁሉ ተደራርቦ ሴቶችን ከመገናኛ ብዙኀን ሽፋን በርቀት አስቀምጧቸዋል። እና መናገር ያለብን እንናገር፣ እንምራ፣ እናስተጋባ፤ አይሻልም?
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here